Content-Language: am ክቡር ቢትወደድ አዳነ መኮንን (አባ ደፋር)
header image

ክቡር ቢትወደድ አዳነ መኮንን (አባ ደፋር)




  የክቡር ቢትወደድ አዳነ መኮንን
(አባ ደፋር)ን የሕይዎት ታሪክ ያዳምጡ














1. ትውልድ፤ እድገትና የነበራቸው የሥራ ድርሻ


Biteweded Adane Mekonen
ጀግናው አርበኛ ክቡር
ቢትወደድ አዳነ መኮነን
አቶ አዳነ መኮንን በወልቃይት-ጠገዴ ልዩ ስሙ ዓዴት በምትባል ቦታ ከአባታቸው ከልጅ መኮንን መንገሻ እና ከእናታቸው ከወ/ሮ ብዙነሽ አበበ በሚያዝያ ወር 1888 ዓ.ም ተወለዱ፡፡
ቢትወደድ አዳነ መኮንን በልጅነት ዕድሜያቸው በአደን የታወቁና ፈጣን አነጣጥሮ ተኳሽ በመሆናቸው የተነሳ በአከባቢው (በወልቃይት-ጠገዴ) ባህል መሰረት ዝናና ታዋቂነትን አትርፎላቸዋል፡፡
አቶ አዳነ መኮንን በ1918 ዓ.ም የበጌምድር አውራጃ ገዥ የነበሩት የራስ ጉግሳ ወሌ ወታደር በመሆን በደብረ-ታቦር መኖር ጀመሩ፡፡
በ1923 ዓ.ም. በልዑል አልጋ ወራሽ ተፈሪ መኮንን እና በራስ ጉግሳ ወሌ መካከል አንችም ተብሎ በሚጠራው ስፍራ በተካሄደው ጦርነት ተካፍለው ከራስ ጉግሳ ሞት በኋላ በአዲሱ የበጌምድር ገዥ በደጃዝማች ወንድወሰን ካሣ አማካኝነት የቀኛዝማችነት ማእረግ ተሰጧቸው የአርማጭሆና የያይራ አስተዳዳሪ ሆነው ተሸሙ፡፡

2. በአርበኝነት ዘመን የፈፀሟቸው ተጋድሎዎች

በ1928 ዓ.ም. ፋሽስት ኢጣሊያ አገራችንን በወረረችበት ጊዜ ቀኛዝማች አዳነ መኮነን፤
  1. ከፊታውራሪ ኃይሉ ፋሪስ
  2. ከቀኛዝማች ዓባይ
  3. ከወልደ ማርያም
  4. ከቀኛዝማች መስፍን ረዳ እና
  5. ከቀኛዝማች ገብሩ ገ/መስቀል
ጋር በመሆን የወልቃይት-ጠገዴን ህዝብ በማስተባበርና በመምራት የሠቲት ሁመራንና የመተማን በር እንዲጠብቁ በልዑል ራስ ካሣ ኃይሉ ልጅ በደጃዝማች ወንደወሰን ካሳ ታዘዙ፡፡
አርበኞቹ ጠላትን በመከላከል ተግባር ላይ እንዳሉ ጠላት በዘመናዊ ጦር መሣሪያና በግዙፍ ሠራዊት በመታገዝ በኢጣሊያው ጀነራል አቼሌ እየተመራ ሁመራ የሚገኘውን የአርበኞቹን ምሽግ ጥሶ ጎንደር ከተማ ገባ፡፡
የፋሽስት ኢጣሊያ ጦር ጎንደር ከገባ በኃላ ጀግናው የወልቃይት-ጠገዴው ተወላጅ ኢትዮጵያዊ አርበኛ ቀኛዝማች አዳነ መኮነን ከወንድሞቻቸውና ከጓደኞቻቸው ጋር ሆነው በረሃ ገቡ፡፡
ፋሽስት ኢጣሊያ ጎንደርን ከአሥመራ ጋር ለማገናኘት በአርማጭሆ፣ በሠሮቃ፣ በዳንሻ፣ በወይእናት፣ በበኻከር፣ በሁመራ፣ በኦም-ሓጀር፣ ወ.ዘ.ተ አድርጎ የመኪና መንገድ በመጥረግ የጦር ካምፑ በዓዲ-ረመጥ፣ በቃብትያ፣ በመሠፌንቶና በ 'ስፍራ-ጣልያን' በሚባሉ ቦታዎች ላይ የጦር ሠፈር አቋቋመ፡፡
ቀኛዝማች አዳነ መኮንን የወራሪውን ጦር ለመመከት የወልቃይት-ጠገዴ አርበኞችን በማሰባሰብ የሽምቅ ጦር በማቋቋም ለዕብሪተኛው የኢጣሊያ ጦር መቅሰፍት ሆኑበት፡፡
በዚህም መሠረት ሚያዝያ 23 ቀን 1928 ዓ.ም በቀኛዝማች አዳነ መኮንን የሚመራው ጦር ደብዛ ላይ የደፈጣ ውጊያ በማድረግ በኢጣሊያ ጦር ላይ ከፍተኛ ጉዳት በማድረስ በርካታ ጠብመንጃና ጥይቶችን ማርከዋል፡፡
ከዚህም በመቀጠል በህዳር ወር 1929 ዓ.ም 'ስፍራ-ጣልያን' በተባለ ቦታ የነበረውን የጠላት የጦር ሠፈር ሳይታሰብ በማጥቃት ብዙ የኢጣሊያ መኮንኖችንና ወታደሮችን በመግደል ወደ ፊት ለሚያደርጉት ጦርነት አጋዥ የሚሆን ጠብመንጃና ጥይት ማርከዋል፡፡
በዚህ ሁኔታ እንዳለ የኢጣሊያ ወራሪ ጦር ትጥቅ ለማስፈታት በሚያደርገው ጭፍጨፋ ህዝቡ እየተማረረ በረሃ በመግባት ያርበኞቹን የነቀኛዝማች አዳነ መኮንንን ጦር ማጠናከር ጀመረ፡፡

3. በጠላት ላይ የተቀዳጇቸው ድሎች

Biteweded Adane Mekonen
(ፎቶው በዌብማስተሩ ታርሟል)

ምስግና፤ ለ፤  ዝናው ዘ ባይህ
ኢጣሊያዊው የወልቃይት-ጠገዴ ገዥ ካርዴሌ፤ የአርበኞችን አመፅ ለማጥፋትና ለመደምሰስ ብዙ የባንዳ ጦር በማሰማራት ላይ እንዳለ ጥቅምት 5 ቀን 1930 ዓ.ም በቀኛዝማች አዳነ መኮንን የሚመራው የወልቃይት-ጠገዴ የአርበኞች ጦር ቡራዩ በሚባል ወንዝ ፈጣን የሆነ የደፈጣ ጥቃት አድርሶ ብዙ የኢጣሊያን ወታደሮችን ደምስሷል፡፡
በዚሁ ቁጭት የተነሳ፤ ጠላት ጥቅምት 22 ቀን 1930 ዓ.ም ከፍተኛ ጦር አሰባስቦ ዓዴት ላይ ከአርበኞች ጦር ጋር ውጊያ ገጥሞ የነበረ ቢሆንም፤ ያርበኛው ጦር ቀደም ብሎ በማረከው የጦር መሣሪያ ተዘጋጅቶ ስለነበረና፤ የወልቃይት-ጠገዴን ህዝብ ድጋፍም ስላገኘ በጠላት ላይ ድልን ተጎናጸፈ፡፡
ቁጭት የተሞላው የፋሽስት ጦር እንደገና ለሶስተኛ ጊዜ፤ ህዳር 21 ቀን 1930 ዓ.ም 'ስፍራ-አለቃ' በተባለ ቦታ ከአርበኞቹ ጋር ገጥሞ የተለመደውን ሽንፈት ተከናነበ፡፡
ከዚህ ቀደም ብለው በተደረጉ ጦርነቶች ያልተሳካለት የጠላት ጦር ሽንፈቱ እጅግ ስላስቆጣው ከግዜ ወደ ጊዜ እየተጠናከረ የመጣውን የአርበኞች እንቅስቃሴ ለመደምሰስ በሁለት አቅጣጫ ማለትም በዓዲ-ረመጥና በወገራ በኩል ኢጣሊያዊው የወልቃይት-ጠገዴ ገዥ ካርዴሌ ወደ አርበኞቹ መናኸሪያ ወደነበረችው ዓዴት ዘለቀ፡፡
በዚህም ማይገና በሚባል ስፍራ ጦርነት ተካሂዶ በሁለቱም በኩል ከፍተኛ እልቂት ቢደርስም ምን ግዜም ድሉ የአርበኞቹ ሆነ።
ይህ ድል በቀኛዝማች አዳነ መኮንን የሚመራውን የአርበኞቹ ግንባር ትልቅ ዝናና ክብር ሰጠው፡፡
የጠላት ጦርም ሽንፈቱን አውቆ ይዟቸው የነበሩትን፤ ዓዴት፣ ማይገና፣ ቀራቅር፣ ጨጓርኩዶ እና ሌሎች አከባቢዎችን ለቆ ወጣ፡፡
በጀግናው ቀኛዝማች አዳነ መኮንን የሚመራው ጦር በዚህ ሳያቆም ትግሉን በመቀጠል፤ በጥር ወር 1930 ዓ.ም ጠለሎ ላይ መሽጎ የነበረውን የጠላት ጦር በአከባቢው ተወላጅ በሆኑት በደጃዝማች ደስታ ማሩ መሪነትና አስተባባሪነት እንዲደመሰስ አደረጉ፡፡
ይህን የአርበኝነት ትግል የመሠረተ የጦር አመራር፣ ችሎታና ብቃት ያለው መሪ፣ አርበኛውን ድል በድል ያጎናፀፈ መሆኑን የወልቃይት-ጠገዴ ህዝብ አምኖበት በጥር 21 ቀን 1930 ዓ.ም በአንድ ድምፅ ጨጓርኩዶ ማርያም በተደረገው የህዝብ ስብሰባ የወልቃይት-ጠገዴ ህዝብ ለክቡር አዳነ መኮነን የደጃዝማችነት ማዕረግ በመስጠት የወልቃይት-ጠገዴ የአርበኞች መሪ አድርጎ ሾሟቸዋል፡፡
ክቡር አዳነ መኮንን ይህንኑ አደራ ካሳደጋቸው የወልቃይት-ጠገዴ ህዝብ በመቀበል ለብዙ ተከታታይ አመታት ለአርበኞች ማዕረግ በመስጠት አርበኛውን አጠናክረውታል፡፡

ጠላት በኢትዮጵያ ምድር በቆየበት አምስት አመታት ውስጥ ደጃዝማች አዳነ መኮንን 56 ግዜ ጦርነት በመግጠም በዓዴት፣ በማይገና፣ በቀራቅር፣ በጨጓርኩዶ፣ በጠለሎ፣ በደጀና፣ በዓዲ-ረመጥ፣ በቤተ-ሙሉ፣ በአርማጭሆ፣ በጃናሞራ፣ በአጅሬ፣ በጭልጋና በወገራ ከፋሽስት ጋር ግብግብ በመግጠም ለመጨረሻ ድል በቅተዋል፡፡

4. ለክቡር ደጃዝማች አዳነ መኮንን የተሰጧቸው ሹመቶች

  1. ፋሽስት ኢጣሊያ ድል ሆኖ ከተሸነፈ በኃላ በ1934 ዓ.ም ደጃዝማች አዳነ መኮነን ከሰሜን ባምብሎ እስከ ተከዜ ጦር አዝማችና አበጋዝ ተብለው በአዋጅ ሹመት ተሰቷቸዋል፡፡
  2. በ1938 ዓ.ም በንጉሠ ነገሥቱ ፈቃድ የወገራ አውራጃ ገዥ ሆነው ተሹመዋል፡፡
  3. በ1939 ዓ.ም ህዝብ የሠጣቸው የደጃዝማችነት ማዕረግ በንጉሠ ነገሥቱ ፀድቆላቸዋል፡፡
  4. በ1944 ዓ.ም ከወገራ አውራጃ አስተዳዳሪነት ወደ ጭልጋ አውራጃ ተዛውረው አስተዳድረዋል፡፡
  5. እንደገናም በ1945 ዓ.ም ወደ ወገራ ተመልሰው እስከ 1966 ዓ.ም ሲያስተዳድሩ ቆይተዋል፡፡
  6. በ1959 ዓ.ም በንጉሠ ነገሥቱ ፈቃድ የቢትወደድነት ማዕረግ ተሰጥቷቸዋል፡፡
ክቡር ቢትወደድ አዳነ መኮንን ያገራቸውን ልማት ለማፋጠን ባደረጉት ልባዊ ጥረት ከሰቲት ሁመራ ወደ ጎንደር የተዘረጋውን መንገድና የአከባቢው ልማት ህዝቡን በማሰባሰብና በማበረታታት ልማቱን መርተዋል።

5. ቢትወደድ አዳነ መኮንን የተሸለሟቸው ሜዳሊያዎች

  1. የአምስት ዓመት አገለግሎት የአርበኝነት ሜዳሊያ
  2. የቅዱስ ጊዮርጊስ የጀብዱ ሜዳሊያ
  3. የአፍሪካ ኮከብ የወርቅ ሜዳሊያ ከታላቋ ብሪታንያ
  4. የቅዱስ ጊዮርጊስ ንሻን የፈረሰኛ ደረጃ ያንገት ኮርዶን
  5. የዳግማዊ ምኒልክ የክብር ኮከብ የወርቅ ሜዳሊያ
  6. የሠለሞን የክብር ኮከብ ባለ አምበል
  7. የቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ የክብር ኮከብ የወርቅ ሜዳሊያ
  8. የኢትዮጵያ የክብር ኮከብ የወርቅ ሜዳሊያ


african-star-medal
3. የአፍሪካ ኮከብ የወርቅ
ሜዳሊያ ከታላቋ ብሪታንያ
gold-star-menlik
5. የዳግማዊ ምኒልክ የክብር
ኮከብ የወርቅ ሜዳሊያ
gold-medal-haile-selassie
7. የቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ
የክብር ኮከብ የወርቅ ሜዳሊያ
gold-star-of-ethiopia
8. የኢትዮጵያ የክብር
ኮከብ የወርቅ ሜዳሊያ



ምንጭ፤
  1. ምስግና፤ ለዝናው ዘ ባይህ እና ለመምህር ታማኝ መብራቱ፤ “የወልቃይት ጠገዴ ህዝብ፣ ታሪክና ማንነት ፩ኛ ዕትም”   ሊንክ
  2. ምስግና፤ ለ ኢትዮፓኖራማ   ethiopanorama.com
  3. የትረካው አጃቢ ሙዚቃ፣ ዋሽንት - በአንሙት ክንዴ   ዩቲውብ