ዳግማዊ ምኒልክ በ 1900 ዓ.ም. መጨረሻ ላይ ታመው በነበረበት ወቅት ወይዘሮ ዘውዲቱ፤ ንግሥት ከመሆናቸው በፊት ከ እቴጌ ጣይቱ ጋር ሆነው አባታቸውን በማስታመም ላይ ነበሩ፡፡
ሆኖም የመንግሥቱን የወራሽነት ሥልጣን ከተሰጣቸው፤ የእህታቸው የወይዘሮ ሸዋረጋ ምኒልክ ልጅ ከሆኑት ከ ልጅ እያሱ ጋር ባለመስማማታቸውና፤ ልጅ እያሱም ዘውዲቱ የሥልጣን ተቀናቃኛቸው አድርገው ስለወሰዷቸው፤ እቴጌ ጣይቱንና ወይዘሮ ዘውዲቱን ከአዲስ አበባ ቤተ መንግሥት አሶጧቸው፡፡
ዳግማዊ ምኒልክ ካረፉ በኋላ በሕዝቡ ዘንድ ያለመረጋጋት አንዳይፈጠር በማሰብ መሞታቸው ለሕዝብ ሳይገለጽ እንደዲቆይ የካቢኔ ሚኒስትሮቻቸው ወሰኑ፡፡
በዚህም ምክንያት ዳግማዊ ምኒልክ አልጋቸውን እንዲወርስ የተናዘዙላቸው ልጅ እያሱም፤ በሞግዚታቸው በራስ ተሰማና በቤተ ክርስያን ልቃውንት ምክር አማክኝነት፤ እድሜአቸው በሰል እስኪልና ከባለቤታቸው ጋር ያለው ጋብቻ በቤተ ክርስቲያን ሥርዓት መሠረት እስኪፈጸም ድረስ ንግሥናቸው ላልተወሰነ ጊዜ እንዲተላላፍ ተወሰነ፡፡
ይሁን እንጅ ልጅ እያሱ የተላለፈባቸውን ውሳኔ ችላ በማለት በራሳቸው መንገድ መጓዛቸው፤ የሚያሳዩት ያልተረጋጋ ባሕርይና ወደ እስልምናው ሐይማኖት ያደላሉ ተበለውም ይታሙ ስለነበረ፤ በመኳንንቱና በመሳፍንቱ ዘንድ ተግባራቸው ሁሉ አልተወደደላቸውም፡፡
ከጥቂት አስቸጋሪ ዓመታት በኋላም፤ የመንግሥት ምክር ቤቱ፤ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተ ክርስቲያን እና ሕዝቡም ተሰብስቦ፤ የዳግማዊ ምኒልክን የልጅ ልጅ የሆኑትን ልጅ እያሱን ከመንግሥት ሥልጣናቸው ሽሮ ካሰናበታቸው በኋላ ወይዘሮ ዘውዲቱ በግዞት ከነበሩበት ቦታ ወደ አዲስ አበባ ተጠሩ፡፡
ከዚህ በኋላ ወይዘሮ ዘውዲቱ፤ ንግሥተ ነገሥታት ዘውዲቱ ተብለው በተወለዱ በ40 ዓመታቸው መስከረም 17 ቀን 1909 ዓ.ም የአባታቸውን ዙፋን እንዲወርሱ ተደረገ፡፡
በኋላም፤ የካቲት 4 ቀን 1909 ዓ.ም. አራዳ በሚገኘው በመናገሻ ቅዱስ ጊዮርጊስ ቤተ ክርስቲያን ከግብፅ በመጡት የኮፕቲክ ጳጳስ አቡነ ማቴዎስ እጅ ቅብዐ መንግሥት ተቀብለው ዘውድ ጫኑ፡፡
በዚያው እለትም፤ ልዑል ራስ ተፈሪም ታላቁን የሰለሞን ኒሻን ተሸልመው ፀሎት ከተደረገላቸው በኋላ ለአልጋ ወራሽነትና ለእንደራሴነት የሚገባውን ክብር በ24 ዓመታቸው ተቀብለዋል፡፡
በ19ኛው እና በ20ኛው ክፍለ ዘመን በዓለም እውቅና ከተሰጣቸው አገሮች መካከከል ኢትዮጵያ አንዷ ስትሆን፤ ንግሥተ ነገሥታት ዘውዲቱ፤ ይህን ከፍተኛ የአገር መሪነት ሥልጣን መጨበጣቸው፤ በአፍሪካ የሥርዓተ መንግሥት የመሪነት ታሪክ ብቸኛዋ ሴት ያደርጋቸዋል፡፡
ልጅ እያሱ ከሥልጣን ወርደው ንግሥተ ነገሥታት ዘውዲቱ ዘውዱን ከጫኑ በኋላ፤ የራስ ጉግሣ ወሌ ወደ ማዕከላዊ ሥልጣን እየቀረቡ መምጣትና የራስ ተፈሪ መኮንን አልጋ የመውረስ ጽኑ ፍላጎት መካከል የስልጣን ሽኩቻው ተጋግሎ ብዙ ውጣ ውረዶች ተከስተዋል፡፡
ንግሥተ ነገሥታት ዘውዲቱ ምኒልክ በሕይዎት በቆዩባቸው ዘመናት፤ እግዚአብሔርን የሚፈሩ፣ ሕግን አክባሪ፣ ለሐይማኖታቸው እጅግ ቀናኢ የነበሩና በጾም በጸሎት ተወስነው የሚኖሩ ቸርና እርኅርኅት ነበሩ፡፡
በንግሥት ዘውዲቱ የአልጋ ወራሽነት ሥልጣን የተሰጣቸው ራስ ተፈሪ መኮንን፤ በጀመሩት ተራማጅ አስተሳሰብ የተነሣ ከንግሥት ዘውዲቱ ጋር የነበራቸው የአመለካከት ልዩነት ከጊዜ ወደ ጊዜ እየሰፋ መጣ፡፡
ንግሥት ዘውዲቱ፤ የነበረው የቀድሞ ሥርዓትና ባሕል ሳይበረዝ ተጠብቆ እንዲቆይ የሚፈልጉ ወግ አጥባቂ አስተሳሰብ ስለነበራቸው የኦርቶዶክስ ቤተ ክርስቲያንን ሙሉ ድጋፍ አግኝተው ነበር፡፡
አልጋ ወራሽ ራስ ተፈሪ መኮንን ድግሞ፤ ከውጭው ዓለም ጋር ግንኙነት በመፍጠር፤ ኢትዮጵያ አስተዳደሯ ዘመናዊ እንዲሆንና ከሌሎች ታዳጊ አገራት ጋር እንድትስተካከል የሚፈልጉ በመሆኑ፤ በወጣት መኳንንቶች ዘንድ ተቀባይነት እያገኙ መጡ፡፡
በመካከሉም፤ አልጋ ወራሽ ተፈሪ መኮንን ንጉሥ ሆነው ይሾሙልን የሚል የአድማ ጥያቄ ለንግስቲቱ በመቅረቡ፤ ንግሥቲቱ በጥያቄው ደስተኛ ባይሆኑም ቅሉ አልጋ ወረሹን ጠርተው ካነጋገሩ በኋላ፤ የጎንደር ንጉሥና ባለሙሉ ሥልጣን እንደራሴ ብለው ሾሟቸው፡፡
እየቆየም በንግሥተ ነገሥታት ዘውዲቱና በአልጋ ወራሽ ተፈሪ መኮንን የነበረው ግንኙነት ቀስ በቀስ እየላላ መምጣት ጀመረ፡፡
ንግሥቲቱ፤ በየጊዜው በሚፈጠረው የፖለቲካ መጠላለፍና ውዠንብር የነበራቸውን አስተያየትና ሀሳብ፤ ክቡር ደጃዝማች ከበደ ተሰማ በመጽሐፋቸው እንደገለጹት፤
“(ሕዝቡ) እኔን ሳያውቀኝና ሳልጠቅመው የአባቴን ውለታ ለመመለስ ሲል፤ የኢትዮጵያ መሳፍንትና መኳንንት፤ ሕዝቡም በፈቃደ እገዚአብሔር ታዞ ለአባቴ ዙፋን ቢያበቃኝ፤ ከእኔ አስተዳደር አለማወቅ የተነሳ ሕዝቡ እርስ በርሱ ተፋጅቶ ከሚያልቅና እራሳቸውን አልቻሉም ተብሎ በዘመነ መንግሥቴ፤ የባዕድ መንግሥትና ገዥ ወደ ኢትዮጵያ ከሚገባ፤ እኔ የተጠየኩትን ስልጣን ለቀቄ ነገሩን ማብረድ ይሻላል፡፡“
በማለት ለጊዜው የሚገጥማቸውን ችግር ሁሉ ከፍ ባለ ትዕግሥት ያሳልፉት እንደነበረ ያስረዳሉ፡፡
ይህም የንግሥቲቱ ተግባር ምቹ ሁኔታን በመፍጠሩ፤ የጎንደር ንጉሥና ባለሙሉ ሥልጣን እንደራሴ የሆኑት አልጋ ወራሽ ተፈሪ መኮንን፤ ተራማጅ የፖለቲካ አስተሳሰብ በነበራቸው የፖለቲካ ባለሥልጣናትና ደጋፊዎቻቸው ዘንድ ይበልጥ ተቀባይነት እያገኙና የመሪነት ሥልጣኑንም እያጠናከሩ ሊመጡ ችለዋል፡፡
ራስ ተፈሪ መኮንንም፤ ኢትዮጵያ የዓለም መንግሥታት ማህበር አባል እንድትሆን ሲያደርጉ፤ እንዲሁም የባሪያ አሳዳሪ ሥርዓትን እንዲወገድ ማድረግ ችለዋል፡፡
ንግሥት ዘውዲቱም በተፈጠረው የሥልጣን ሽኩቻ ምክንያት ቀስ በቀስ ከሥልጣናቸው እነዲገለሉ በመደረጉ፤ ፖለቲካውን ትተው ወደ ሐይማኖታቸው በማዘንበል ቤተ ክርስቲያናትንና ገደማትን ማሠራት ጀመሩ፡፡
የቤገምድር ገዥ የነበሩት፤ የ
እቴጌ ጣይቱ የወንድም ልጅ የሆኑትና የንግሥተ ነገሥታት ዘውዲቱ ባለቤት ራስ ጉግሳ ወሌ፤ በራስ ተፈሪ መኮንን ላይ የተቃውሞ እንቅስቃሴ አስነስተው ራስ ተፈሪ መኮንንን የእንደራሴነት ሥልጣናቸውን ነጥቆ የንግሥቲቱን ሙሉ ሥልጣን ለማስከበር በማሰብ፤ በሁለቱ ወገን መካከል ጦርነት ተካሂዶ በመጨረሻም ራስ ጉግሣ በጦር ምኒስትሩ በራስ ተፈሪ መኮንን ዘመናዊ ጦር ድል ሆነው ሊገደሉ ችለዋል፡፡
ንግሥተ ነገሥታት ዘውዲቱም፤ የነበረባቸው የስኳር በሽታ በመወሳሰቡ ምክንያት ሕመሙ በርትቶባቸው ስለነበረ፤ ራስ ጉግሣ ድል መሆናቸውን ከሰሙ በኋላ ረቡዕ መጋቢት 24 ቀን 1922 ዓ.ም. ምንም ዘር ሳይተኩ በተወለዱ በ56 ዓመታቸው ሕይወታቸው ሊያልፍ ችሏል፡፡
ሥርዓተ ቀብራቸውም ለአባታቸው ለዳግማዊ ምኒልክ መታሰቢያ ባሠሩት በታዕካ ነገሥት ባዓታ ለማሪያም ገዳም እንዲያርፍ ተደርጓል፡፡
አልጋ ወራሽ ተፈሪ መኮንንም ንግሥቲቱ ካረፉ ከ7 ወራት በኋላ ዕሁድ ጥቅምት 23 ቀን 1923 ዓ.ም.
“ቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ ንጉሠ ነገሥት ዘኢትዮጵያ” ተብለው በንግሥቲቱ ዙፋን ተተክተው በትረ ስልጣኑን ሙሉ ለሙሉ ተረክበው ነገሡ፡፡