ከአፄ ቴዎድሮስ መንግሥት መውደቅ በኋላ፤ "እንግሊዞች እንዲህ በቀላሉ ኢትዮጵያ እምብርት መድረስ ከቻሉ እኛስ ምን ያቅተናል? አይበገሬ የተባለው የአበሻ ህዘብ ለካ እንዲህ በቀላሉ የሚንበረከክ ነው?"የሚል ከንቱ ሀሳብ በአንዳንድ የውጭ መንግሥታት ኃይሎች ውስጥ መስረፅ ጀመረ፡፡
ለዚህም ስሜት መፈጠር ጉልህ ድርሻ ያበረከተው በምፅዋ የፈረንሳይ ቆንስል (counseller) የነበረው ስዊዘርላንዳዊው ቅጠረኛ ቨርነር ሙዚንገር ነበር፡፡
ይህ ሰው በኢትዮጵያ ምድር ከረንን ከያዘ በኋላ የግብፅ የግዛት የመስፋፋት ፖሊሲ ቀያሽ በመሆን ሠርቷል፡፡
በዚህም መሠረት ሙዚንገር 2ሺህ ወታደሮቹን ይዞ ወደ ጎንደር ለመሄድ ሲያቀና፤ የሙዚንገር ጦር የኢትዮጵያን ድንበር መሻገሩን የሰሙ በአካባቢው ይኖሩ የነበሩ ኢትዮጵያውያን የሙዚንገርን ጦር ጥቅምት 29 ቀን 1867 ዓ.ም. ጠብቀው በደፈጣ ውጊያ ፈጁት፡፡
ሙዚንገር፣ ራስ ካሳ ምርጫ (በኋላ አፄ ዮሐንስ) የካቶሊኮችን እንቅስቀሴ ለማገድ የሚያደርጉትን ጥረት አስመልክቶ በጻፈው ደብዳቤ፤
“ካሣ ፀባዩን ያላሳመረ እንደሆነ የቴዎድሮስ ፅዋ ይጠብቀዋል::”
በመላት ማስጠንቀቂያ ሰጥቶ ነበር፡፡
የኦቶማን ቱርኮች፤ ግብፅን ለ350 ዓመታት በቅኝ ግዛትነት ተቆጣጥረው በነበረበት ወቅት ግብፅና ሱዳንን 16 ዓመት ገዝቶ የነበረው ቱርካዊው እስማኤል ፓሻ፣ የአያቱን የሙሀመድ ዓሊ ፓሻን የተስፋፊነት ፈለግ በመከተል፤
የግብፅ እድገትና ብልጽግና የተመሠረተው በአፍሪካ ላይ መሆኑን ተግንዘቦ የዓባይን ፈለግ ተከትሎ ወደ አፍሪካ ምድር መስፋፋት ቀጠለ፡፡ በዚህም መሠረት የዛሪዋን የደቡብ ሱዳንን ግዛት ወደ ክልሉ አስገባ፡፡ የእስማኤል እቅድ ባጭሩ ነጭ አባይንና ጥቁር ዓባይን ያቀፈ፣ ማለትም ሱዳንንና ኢትዮጵያን ከግብፅ ጋር በመደባለቅ "የግብፅ-አፍሪካ ግዛት" የተሰኘ ሰፊ የሰሜን ምስራቅ አፍሪካ ግዛት ለመፍጠር ነበር፡፡
በነገራችን ላይ ግብፆች በርካታ የቅኝ ገዥዎች ተፈራርቀውባታል፡፡
በግብፅ ላይ የተፈራረቁባት ቅኝ ገዥዎች
- በኦቶማን ቱርኮች ለ 350 ዓመታት፣
- በፈረንሳዮች ለ 3 ዓመት፣
- በኋለኛው ዘመን በተነሳው የኦቶማን ቱርክ በሞሀመድ ዓሊ ሥርዎ መነግሥት ለ 148 ዓመታት፤
- በኦቶማን ቱርክ ገባር መንግሥት ለ 47 ዓመታት፣
- በእንግሊዞች ለ 40 ዓመታት፤
በጠቅላላው ለ 588 ዓመታት በቅኝ ገዥዎች ተገዝተዋል፡፡
ግብፅ ከቅኝ ግዛትነት ወጥታ ራሷን በነፃነት ማስተዳደር የጀመረችው በ 1945 ዓ.ም ጀምሮ ነው፡፡
አፄ ዮሐንስ የክርስቲያን መንግሥት በእስላም ሲጠቃ ያውሮፓ ክርስቲያን መነግሥታት አጋርነታቸውን እንዲገልጹ ቢጥሩም ውጤት አላመጡም፡፡ በአውሮፓ የወዳጅነት መመዘኛው ሐይማኖት ሳይሆን ቁሳዊ ጥቅም ነው፡፡ ከኢትዮጵያ ይልቅ ግብፅ ለአውሮፓ ኢኮኖሚያዊና ስትራተጅካዊ ጠቀሜታ ሰላላት አውሮፓውያን ግብፅን የመርዳት ዝንባሌ ማሳየት ጀመሩ፡፡
ግብፆች በሰሜን በኩል ምጽዋ፣ ዙላና አንፈላ የተባሉ የቀይ ባሕር ወደቦችን ከተቆጣጠሩ በኋላ ወደ ደቡብ ኢትዮጵያ በማምራት ወደ ተሟላ አገራዊ ወረራ ተሸጋገሩ፡፡
ይህ ሁሉ ሲሆን በመስከረም ወር 1868 ዓ.ም. የግብጽ ጦር እየገፋ ሲመጣ ከግብፆች ጋር ሰላም ለመፍጠር በማለት አፄ ዮሐንስ የሐማሴንና የሠራዬ አውራጃ ሠራዊታቸው ወደ አድዋ እንዲያፈገፍግ ትዕዛዝ ሰጡ፡፡
አፄ ዮሐንስ በግብፅ ወራሪ ጦር ላይ የክተት አዋጅ ያወጁት የግብጽ ጦር ሐማሴን ከደረሰ በኋላ ነው፡፡
ንጉሠ ነገሥት አፄ ዮሐንስ የግብፅን ወራሪ ጦር ለመግጠም 20 ሺህ ጦር አሰልፈው የክተት አዋጅ አወጁ፡፡
አፄ ዮሐንስ ያወጁት የክተት አዋጅ፤
“ክርሰቲያን የሆንክ ሁሉ ቄሶች ጭምር ወደመጣው ጠላት እንድትዘምቱና እስላሞችን እንድታጠፉ፡፡” የሚል ነበር፡፡
አፄ ዮሐንስ ኤርትራ በሚገኘው ጉንደት ላይ የገጠሙት ጦርነት ወሳኝ ጦርነት ነበር፡፡
የግብፅ ጦር ከኢትዮጵያ ጋር ሲዋጋ ብቻውን አልተዋጋም፡፡
የግብፅ ጦር፤ ግብፅን በቀኝ ግዛትነት ተቆጣጥሮ ይገዛ የነበረ የኦቶማን ቱርክ ተስፋፊ ኃይል ሲሆን፤
በአሜሪካ የእርስ በርስ ጦርነት ወቀት የተሳተፉ በርካታ ቁጥር ያላቸው የአሜሪካ የጦር መኮንኖችና እነዲሁም ከአውሮፓ ከተላኩ ቅጠረኛ የጦር መኮንኖችና ወታደሮች ጋር ቅንጅት በመፍጠር የተካሄደ ጦርነት ነበር፡፡
አፄ ዮሐንስ ጉንደት በተባለው ሥፍራ በተካሄደው ውጊያ በግብፆች ላይ ድል ተቀዳጅተዋል፡፡
ጉንደት ላይ በተካሄደው ጦርነት፤ በኢትዮጵያ በኩል፤ በአፄ ዮሐንስ፣ በራስ አሉላ እንግዳ እና በራስ ወልደ ሚካኤል ሰለሞን የጦር መሪነት፤ 50 ሺህ ጦር ሲሰለፍ፤
በግብፅ በኩል ደግሞ፤ በዴንማርኩ አዛዥ በኮሎኔል አረንድሩፕና በአሜሪካ የጦር መኮንኖች የሚመራ 5 ሺህ ጦር ተሰልፎ ህዳር 8 ቀን 1869 ዓ.ም. ጦርነት ተካሂዶ በአራትና በአምስት ሰዓታት ውስጥ እጅግ በሚደንቅ ሁኔታ የኢትዮጵያ ሠራዊት የግብፅን ጦር ሙሉ በሙሉ በመደምሰስ ከፍተኛ ድልን ተቀዳጅቷል፡፡
የግብፅ ጦር አዛዥ የነበረው ኮሎኔል አረንድሩፕም በዚሁ ቀን ተገሏል፡፡
በጉንደት ጦርነት የግብፅ ጦር አዝማች ሆኖ ተሰልፎ የነበረው አሜሪካዊው ኮሎኔል ስለ ግብፆች መሸነፍ ሲጽፍ፤
በጦር ተወግተው የተጋደሙ፣ እጃቸው የተቆረጠ፣ አንገታቸው የተቀነጠሰ አካላት፣ ድል አድራጊውን ጠላት ማረኝ ማረኝ ይላሉ፡፡ ግን ማን ሊሰማ፡፡ ጭፍጨፋውን የሚያቆም ምንም ኃይል አልነበረም፡፡
በመላት ምስክርነቱን ሰቷል፡፡
ይህን በግብፅ ጦርና በቅጥረኛ ወታደሮች የደረሰውን ከፍተኛ ሽንፈት የግብፅ ሕዝብ ቢሰማው የኦቶማን ቱርክ የገዥነትን ክብር ያዋርዳል ብለው ስላሰቡ ወሬው ሳይነገር ተዳፍኖ ቀርቷል፡፡
እንግሊዞች የአፄ ዮሐንስን የነፃ የባሕር ወደብ ጥያቄን ለማስተናገድ አልፈለጉም፡፡ እንግሊዞች፣ ቀይ ባሕር በግብፆች፤ ካልሆነም በሌላ በእንግሊዝ ወዳጅ በሆነ መንግሥት ቁጥጥር ስር መቆየት አለበት ብለው ወስነዋል፡፡ በዚህም መሰረት የግብፅ መንግስት እየተዳከመ ሲሄድ እንግሊዞችም ግብፅን በቁጥጥር ስር አደረጉ፡፡
ቀደም ብላ የአሰብ ወደብን ይዛ ለነበረችው ኢጣሊያም፣ እንግሊዞች የምጽዋን ወደብን እንድትቆጣጠር ፈቀዱላት፡፡ በዚያን ወቅትም የአሰብ ወደብ የኢጣሊያ መንግስት ንብረት እንዲሆን ተወስኖ ነበር፡፡
ጣሊያንም አንድ ጥይት ሳትተኩስ ወደ መሀል ኢትዮጵያ የምትንደረደርበትን የምጽዋን ወደብን በእንግሊዝ ቡራኬነት በነፃ አገኘች፡፡
እንግሊዝ የምፅዋን ወደብ ለኢጣሊያኖች ስትሰጥ የራሷ ስሌት ነበራት፡፡ ምክንያቱም፣ ኢጣሊያ ኢትዮጵያን ከተቆጣጠረች፣ የቅኝ ግዛቱን በአፍሪካ ምድር ለማስፋፋት ያሰፈሰፈው የፈረንሳይ መንግሥት ወደ አባይ ድርሽ እንዳይል ኢጣሊያ ትከላከልልኛለች በሚል ስሌት ነበር፡፡
አፄ ዮሐንስ በየዋህነት በገቡት ውልና ቃል መሰረት እንግሊዞች የሚሰሩትን ሸፍጥ ባለመረዳት ከልክ ያለፈ ትብብር በማድረግ ሁለት ጊዜ በጦርነት ድል ባደረጓቸው ደካማ የግብፅ መንግስት ምትክ ሁለት ጠንካራ ጠላቶችን (ኢጣሊያ እና መሀዲስቶችን) ተክተው አረፉት፡፡
ጣሊያኖች በአሰብና በምፅዋ ወደብ ብቻ ተወስነው መቅረት ስላልፈለጉ ይልቁንም ወደ መሀል ኢትዮጵያ ዘልቀው ለማያዝ ከፍተኛ ፍላጎት አደረባቸው፡፡
የመረብ ምላሽ ገዥ የሆኑት ራስ አሉላ ጣሊያኖች የያዙትን የእትዮጵያ ምድር እንዲለቁ በደብዳቤ ትዕዛዝ ቢሰጡም ጣሊያኖች ስላልተቀበሉት ጀግናው ራስ አሉላ ፈረሳቸውን ጭነው ጥር 20 ቀን 1879 ዓ.ም. መሽጎ በተቀመጠው የኢጣሊያ ጦር ላይ ዘምተው ውጊያ ከፈቱባቸው፡፡ የኢጣሊያ ጦር ውጊያውን ስለመከተ፣ ራስ አሉላ ወደኋላ በማፈግፈግ እነደገና የጦራቸውን ኃይል አሰባስበው በመዋጋት፤ ዶግአሊ በተባለው ስፍራ ላይ መሽጎ የነበረውን 500 የኢጣሊያ ጦር ገድለው ድልን በመቀዳጀት ስፍራውን ከጠላት ለማስለቀቅ ችለዋል፡፡በዚህም ሽንፈት የተነሳ በኢጣሊያ አገር ታላቅ ሽብር ሆነ፡፡
ይህን የተፈጠረውን ጠብ በሰላማዊ መንገድ ለመፍታት አፄ ዮሐንስ እና ኢጣሊያ በየግላቸው የእንግሊዝን እርዳታ ጠየቁ፡፡ እንግሊዞች የላኩት አስታራቂም በምላሹ ዮሐንስ በዶግአሊ ላደረሰው እልቂት ኢጣሊያ ይቅርታ እንዲጠይቁ፤ ጣሊያኖች የያዙዋቸውም የኢትዮጵያ ግዛቶች ፀንተው እንዲቀጥሉና ይህንኑ እንዲቀበል የሚል ሆኖ አረፈው፡፡
ይሁን እንጅ እነደዚህ ዓይነቱን ሀሳብ ማንም የተቀበለው አልነበረም፡፡
በዚህን ወቅት ነበር ጀግናው ራስ አሉላ፣ ለተላከው አስታራቂ መልክተኛ፤
“ጣሊያኖች ኢትዮጵያ ምድር ላይ የሚሰፍሩት፤ እኔ የሮማ አገረ ገዥ መሆን የቻልኩ እንደሆነ ብቻ ነው፡፡”
በማለት በታሪክ ሲታወስ የሚኖረውን ድንቅ ንግግር የተናገሩት፡፡
ለጥቂት ዓመታት በርትቶ የነበረው የአፄ ዮሐንስ ኃይል ከ 1877 ዓ.ም. በኋላ መዳከም ጀመረ፡፡
አፄ ዮሐንስ ለአንዴና ለመጨረሻ ጊዜ በመጋቢት ወር 1880 ዓ.ም. 80 ሺህ ጦር አሰልፈው ጣሊያኖች ላይ ቢዘምቱም የጣሊያኖችን ምሽግ ማስለቀቅ አልቻሉም፡፡
የጦራቸውም ደጀን (ከኋላ የተሰለፈ ተጠባባቂ ጦር) የሳሳ እንደነበር ይነገራል፡፡
ከቀድሞ ምሁራን አንዱ የሆኑት ብላታ ገብረ እግዚአብሔር ጊላ የተባሉ ፀሀፊ አፄ ዮሐንስ የተናገሩትን ሲጠቅሱ፤
“እንግዲህስ የሰው አገር እንገዛለን ብለው መጥተው ከምሽግ መሀል ከተሸሸጉ እኔ ምን አደርጋለሁ ብለው ተመለሱ፡፡”
በማለት ጽፈዋል፡፡