ካሣ ኃይሉ በጀግንነታቸው ምክንያት ሁሉም ሰው ይፈራቸዋል፣ ይጠላቸዋል፡፡ መሄጃ አጡ፡፡ የሚያስጠጋቸው ሰው በማጣታቸው ለመኖር ሲሉ ሽፍትነት ጀመሩ፡፡
የካሣ ኃይሉ ገዥዎች ማለትም፤ የሰሎሞናዊው ሥርዎ መንግሥት ተወላጅ የሆኑት አፄ ዮሃንስ 3ኛ፣ ባለቤታቸው እቴጌ መነን ሊበን አመዴ እና ልጃቻው የቤገምድሩ ገዥ የሆኑት መስፍኑ ራስ ዓሊ 2ኛ ምንም ሳይፈይዱ ቁጭ ብለው፤ ካሣ ኃይሉ ግን በሽፍትነታቸው ዘመን በሱዳን በኩል ድንበር እያለፉ ወደ ኢትዮጵያ ግዛት ውስጥ በመግባት በተደጋጋሚ ቤት በማቃጠል፣ በመዝረፍና በመግደል የሚያስቸግረውን የአረቦች ማለትም የግብፅን ሠራዊት እየደጋገሙ በመምታት በርካታ ድሎችን አስመዝግበዋል፡፡
በጊዜው ዘመናዊ የተባለውን የጦር መሣሪያ ከታጠቀው የግብፅ ጦር ጋር የካሣ ሠራዊት ተጋጥሞ በጦር እየወጋ፣ በጎራዴ እየመታ ከፍተኛ ውጊያ ከማካሄዳቸውም ሌላ ወሰን አልፈው በመሄድ ግብጾችን ድል አድርገው ምሽጋቸውንም በማፈራረስ በርካታ የጦር መሣሪያዎችን ማርከዋል፡፡
የካሣን ዝና በኢትዮጵያም ሆነ በሱዳን በኩል እጅግ ከፍ እንዲል ያደረገው ይሄው በሱዳን በኩል ያስገኙት ተደጋጋሚ የጀግንነት ድል ነው፡፡
በዚህ ረገድ በቆራጡ የጦር መሪ በካሣ ኃይሉ ጥበብና ጀግንነት የተሞላው አመራር ሰጭነት፤ ደፋሮቹና ጀግኖቹ የካሣ ኃይሉ የጦር ወታደሮች የሀገራቸውን ዳር ድንበር ለማስከበር አጥንታቸውንና ደማቸውን በመገበር ብዙ መስዋዕትነት ከፍለዋል፡፡
ከዚህ በፊት በተደጋጋሚ እንዳደረጉት ሁሉ ፣ ካሣ ኃይሉ በጊዜው ዘመናዊ የተባለውን የጦር መሣሪያ ከታጠቀው የግብፅ ጦር ጋር ውጊያ ገጥመው ድል ካደረጉ በኋላ ቆስለው ነበር፡፡ ቁስላቸው የበረታ ስለነበር ማገገም እንዲችሉ አፄ ዮሃንስ ሳልሳዊ አንድ ሰንጋ ልከውላቸው ነበር፡፡ እቴጌ መነን ግን ሰንጋ ሳይሆን የላኩላቸው፣
አንድ ብልት ሥጋ ብቻ ነበር፡፡ የካሣ ኃይሉ ባለቤት ወይዘሮ ተዋበች አንድ ብልት ሥጋ ብቻ በመላኩ ይህን ድርጊት የንቀት ያህል ስለቆጠሩትና በአያታቸው ድርጊት ስለተበሳጩ የተላከው ብልት ሥጋ ሳይበላ በአገልግል ውስጥ እንዲቀመጥ ከአዘዙ በኋላ፤
እንዴት ብንናቅ ነው አንድ ብልት ሥጋ ብቻ የተላከልን? ጀግና ሰው እወዳለሁ፡፡ ፈሪ ወንድ ግን እንቃለሁ፡፡ ከፈሪ ሰው ጋርም አብሬ መኖር አልፈቅድም፡፡
ብለው ለአፄ ቴዎድሮስ ነገሯቸው:: ይህን የሚስታቸውን የቁጣ ንግግር የሰሙት ካሣም ቁጭት ስለተሰማቸው እንደገና ለመሸፈት ተገደዱ፡፡
ሲቨን ሮቢንሰን የተባለው ፀሐፊ ፤
እቴጌ መነን ኢትዮጵያን እየከፋፈሉ ሊሸጡ ካስማሙ ባላባቶች አንደኛይቱ ናቸው፡፡ በአሌክሳንድርያ የቤልጅዬም መንግሥት ቆንስላ (ካውንስለር) የነበረው ኤድዋርድ ብሎንዲል ከእቴጌ መነን ጋር በመነጋገር አጋሜንና እንጣሎን በ 15 ሺህ ማርትሬዛና በ 3 ሺህ ጠመንጃ ለመግዛት ተስማምቶ ነበር፡፡ ለዚህም ጉዳይ ኢትዮጵያዊው አባ ገብረ ማሪያም ለኢትዮጵያ መንግሥት ኃላፊ ሆነው ለሽያጭ ተግባር ዋና ደላላና ተዋዋይ ነበሩ፡፡
በማለት ጽፏል፡፡
አባ ገብረ ማርያም ካይሮ ውስጥ ከቤልጅጉ (Belgium) ቆንስል (Counselor) ከብሎንዲል ጋር የተዋዋሉት ውል እነደሚከተለው ይነበባል፡፡
በአብ በወልድ በመንፈስ ቅዱስ ስም፡፡ እኔ ገብረ ማርያም የኢትዮጵያ እጨጌ፣ በኢትዮጵያ ገዥ በራስ ዓሊ ስም የሚከተለውን ተስማምቻለሁ፡፡
ለቤልጅግ ንጉሥ ግርማዊ ቀዳማዊ ሊዎፖልድና ለእርሳቸው ወራሾች ሁሉ እንዲሆን የአጋሜን አውራጃ በሙሉ ከአዲግራት እስከ ባሕሩ ድረስ ሰተናል፡፡
አባ ገብረ ማርያም በመስፍኑ በራስ ዓሊ ስም ከላይ የተጠቀሰውን ውል ይዋዋሉ እንጅ ጉዳዩን የፈጸሙት የራስ ዓሊ እናት እቴጌ መነን ነበሩ ተብሏል፡፡
ይሁን እንጅ የእቴጌ መነንንም ሆነ የአባ ገብረማሪያምን የሀገርን መሬት ቆርሶ ለውጭ ኃይል የመሸጭን ሀሳብ የአፄ ቴዎድሮስ መነሳት አጨናግፎታል፡፡
ካሣ ኃይሉ ያስመዘገቧቸው የመጀመሪያዎቹ የውጊያ ድሎች፤ በዘመነ መሳፍንት አውራዎች ላይ የተቀዳጇቸው ተከታታይ ድሎችን የሚያበስሩ ነበሩ፡፡
የካሣን የውጊያ ችሎታና ጥበብ አጉልተው ባሳዩት በነዚህ ድሎች አማካኝነትም የዘመኑ የመሳፍንት መሪ ተዋንያን በሚያስገርም ፍጥነት አንድ ባንድ ድል ሆኑ፡፡
በዚሀም መሰረት በውጊያ ድል ካደረጓቸው ወይም ካንበረከኳቸው መሳፍንቶች ውስጥ ከብዙ በጥቂቱ የሚከተሉት ይገኙበታል፡፡
- የጎጃሙ ገዥ ደጃዝማች ጎሹ ዘውዴ
- የጎጃሙ ገዥ ብሩ ጎሹ (የደጃዝማች ጎሹ ዘውዴ ልጅ)
- እቴጌ መነን (የአፄ ዮሐንስ 3ኛ ባለቤት)
- ትንሹ ራስ ዓሊ አሉላ (የእቴጌ መነን ልጅ ወይም የአፄ ቴዎድሮስ ባለቤት የወ/ሮ ምንትዋብ አባት)
- የሰሜን ኢትዮጵያና የትግራይ ገዥ ደጃዝማች ውቤ ኃይለማሪያም፤ (የእቴጌ ጣይቱ የአባታቸው ወንድም)
- የሸዋዉ ገዥ ንጉሥ ኃይለ መለኮት
የትንሹ ራስ ዓሊ አሉላ የጦር መሪዎች የነበሩ
- ደጃዝማች ብሩ አሊጋዝ
- ደጃዝማች በለው
- ደጃዝማች አቤ
- ደጃዝማች ያዘው