
ልጅ እያሱ በልጅነት እድሜ
ልጅ እያሱ ከአባታቸው ከወሎው ገዥ ከንጉሥ ሚካኤል እና የዳግማዊ አፄ ምኒልክ ልጅ ከሆኑት ከእናቱ ከወይዘሮ ሸዋረጋ ምኒልክ በወሎ ጠቅላይ ግዛት ተወለዱ፡፡
ልጅ እያሱ የተወለዱበት ቀን በትክክል ባይታወቅም ጥር 28 ቀን 1887 ዓ.ም እንደሆነ ይገመታል፡፡
ዳግማዊ አፄ ምኒልክ በሕመም እየተዳከሙ በመጡበት ሰዓት፤ ከእርሳቸው የተወለደ ወንድ ልጅ ባለመኖሩና፤ የዙፋን ውርስ ለሴት ልጅ ማስተላለፍ በነበረው ባላባታዊ ሥርዓት የተለመደ ባለመሆኑ፤ ዙፋናቸውን ማን እንደሚወርሰው ለመወሰን ተቸግረው ነበር፡፡
በመጨረሻም ዳግማዊ አፄ ምኒልክ ሕመማቸው ፀንቶ ወደ ደብረ ሊባኖስ ለመሄድ በተዘጋጁበት ወቅት፤ ልጅ እያሱ አልጋ ወራሻቸው መሆናቸውን ለሚኒስትሮቻቸው ነገሯቸው፡፡
ልጅ እያሱም፤ በሞግዚታቸው በራስ ተሰማና በቤተ ክርስያን ልቃውንት ምክር አማካኝነት፤ እድሜአቸው በሰል እስኪልና ከባለቤታቸው ጋር ያለው ጋብቻ በቤተ ክርስቲያን ሥርዓት መሠረት እስኪፈጸም ድረስ ንግሥናቸው ላልተወሰነ ጊዜ እንዲተላላፍ ተወሰነ፡፡
ይሁን እንጅ ልጅ እያሱ፤ ንግሥናቸው እንዲተላለፍ የተወሰነባቸውን ውሳኔ ችላ በማለት በራሳቸው መንገድ መጓዛቸው፤ የሚያሳዩት ያለተረጋጋ ባሕርይና ወደ እስልምናውም ሐይማኖት ያደላሉ ተብለው ይወቀሱ ስለነበረ፤ በመኳንንቱና በመሳፍንቱ ዘንድ ተግባራቸው ሁሉ አልተወደደላቸውም ነበር፡፡
ዳግማዊ አፄ ምኒልክ በታመሙባቸው የመጀመሪያዎቹ አመታትም፤ የእቴጌ ጣይቱ
ሥልጣን እያደገ በመምጣቱ፤ የሸዋንና የትግራይን ንጉሣዊ ቤተሰብ ለማስተሳሰር ይረዳል በሚል እምነት፤ ከእቴጌ ጣይቱ ጋር ዝምድና የነበራትን የራስ መንገሻ ዮሐንስ የሰባት ዓመት ህፃን ልጅ የሆነችውን ሮማነወርቅ መንገሻን፤ ልጅ እያሱ እነዲያገቡ ተደርጎ ነበር፡፡ ግን ጋብቻው ብዙም ሊዘልቅ አልቻለም፡፡
እቴጌ ጣይቱ ግን፤ የራሳቸውን የፖለቲካ መስመር ለማስተካከል ያመቻቸው ዘንድ፤ ለምኒልክ አልጋ ወራሽነት ያጩት ልጅ እያሱን ሳይሆን የዳግማዊ አፄ ምንሊክን ሴት ልጅ ዘውዲቱን ነበር፡፡
በሸዋ መኳንንቶችና መሳፍንቶች ዘንድ፤ በእቴጌ ጣይቱ ላይ ቅሬታውና ማጉረምረሙ እየበረታ መጥቶ በካቲት ወር 1902 ዓ.ም. ይፋ ወጣ፡፡
በዚህም በተነሳው ተቃውሞ ምክንያት፤ እቴጌ ጣይቱ ወደ እንጦጦ ማርያም ቤተ ክርስቲያን እንዲሄዱና በዚያ በግዞት መልክ እስከ ዕለተሞታቸው ድረስ እንዲቆዩ ተገደዱ፡፡
የልጅ እያሱ ሞግዚት የነበሩት፤ ቢተወደድ ራስ ተሰማ ናደው ሲሞቱ ደግሞ የ16 ዓመቱን ወጣቱን ልዑል የሚገስፀው ሰው ጠፋ፡፡
እቴጌ ጣይቱ ከሥልጣን ሲገለሉ፤ ለወጣቱ አልጋ ወራሽ ለልጅ እያሱ የተመቸ ሁኔታን ፈጠረላቸው፡፡
ልጅ እያሱን ሙሉ ስልጣን እንዳይዙ ያገዳቸው፤ የዳግማዊ አፄ ምኒልክ አስትንፋስ ለሁለት ዓመት ያህል ሳይቋረጥ መቆየቱ ነበር፡፡
ይሁን እንጅ ልጅ እያሱ ንጉሠ ነገሥት ባይባሉም፤ የሥልጣን ዘመናቸው ለአራት ዓመታት ያህል ቆይቷል፡፡
