ልዑል ራስ ተፈሪ መኮንን በ7 ዓመት የህፃንነት እድሜያቸው
ለፎቶው ምስጋና፤
Getish Ras Teferi
ልጅ ተፈሪ መኮንን፤ ሐምሌ 16 ቀን 1884 ዓ.ም. ሐረር ጠቅላይ ግዛት ውስጥ በሚገኘው ኤጀርሳ ጐሮ በሚባል ሥፍራ ተወለዱ፡፡
አባታቸው፤ ልዑል ራስ መኮንን ወልደ ሚካኤል ይባላሉ፡፡
31 ዓመት በንግሥና የቆዩትና የዳግማዊ አፄ ምንይልክ አባት የሆኑት የሸዋው ንጉሥ ኃይለ መለኮት ሳህለ ሥላሴ፤ የራስ መኮንን ወልደ ሚካኤል አጎታቸው (የእናታቸው ወንድም) ናቸው፡፡
የራስ መኮንን ወልደ ሚካኤል እናት ልዕልት ተናኘ ወርቅ ደግሞ፤ የንጉሥ ኃይለ መለኮት እህት ሲሆኑ፤ የዳግማዊ ምኒልክም አክስት ናቸው፡፡
በሌላ በኩል ልጅ ተፈሪ መኮንን ደግሞ፤ የዳግማዊ አፄ ምኒልክ የአክስታቸው የልጅ ልጅ ናቸው፡፡
የልጅ ተፈሪ መኮንን እናት፤ ወይዘሮ የሽእመቤት ይባላሉ፡፡
ልጅ ተፈሪ መኮንን በተወለዱ በአራተኛው ወር፤ የአባታቸው የእህት ልጅ ከሆኑት ከራስ ዕምሩ ጋር በአንድነት አደጉ፡፡ ሁለቱም እድሜአቸው 7 ዓመት ሲሞላቸው፤ አስተማሪ እቤታቸው ድረስ እየመጣላቸው መማር ጀመሩ፡፡
ልጅ ተፈሪ መኮንን፤ በተወለዱ በ10 ዓመታቸው በአማርኛና በግዝ ማንበብና መፃፍ ቻሉ፡፡
የልጅ ተፈሪ መኮንን እናት ወይዘሮ የሽእመቤት፤ ገና የ30 ዓመት እድሜ ሳሉ በህመም ምክንያት ከዚህ ዓለም በሞት ተለዩ፡፡
ልጅ ተፈሪ መኮንን፤ ከአባታቸው ጋር የነበራቸው ፍቅር ጠንካራና ለአባታቸውም ታዛዥ ስለነበሩ ዘወትር ይመርቋቸው ነበር፡፡
ልጅ ተፈሪ መኮንን በ10 ዓመት እድሜያቸው
Photo Credit to:
image link
ፊታውራሪ ተክለ ሐዋርያት ተክለ ማርያም ስለ ህጻኑ ተፈሪ ሲጽፉ፤
“ተፈሪ በባሕሪው ገና ከሕፃንነቱ ጀምሮ እንደ ዐዋቂ ሰው ነው:: እንደ ልጅ አይደለም። ጭምት፣ አስተዋይና ዝምተኛ ነው። ሁል ጊዜ ከንፈሮቹን ፈልቀቅ ያደርጋል እንጅ ከትከት ብሎ አይስቅም፡፡ መቅበጥ፣ መጮህ አይፈቅድም።” በማለት ገልፀዋቸዋል፡፡...(የበለጠ ለማንበብ➝ Getish Ras Teferi)
ልጅ ተፈሪ መኮንን፤ በተወለዱ በ13 ዓመታቸው ለማዕረጉ ሲባል ብቻ የደጃዝማችነት ሹመት ተሰጣቸው፡፡
ደጃዝማች ተፈሪ መኮንን የፈረንሣይኛ ቋንቋ ተከታትለዋል፡፡
ደጃዝማች ተፈሪ መኮንን፤ የአባታቸውን ንግግርና ምክር ስለሚሰሙና በእድሜያቸው ትንሽነት የተነሳ የሚያስከትለውን ማናቸውንም ሥራ በጥንቃቄ በመሥራታቸው፤ አባታቸውም ሆኑ ሌሎች ሹማምንቶችና መኳንንቶች ይወዷቸው ነበር፡፡
ደጃዝማች ተፈሪ መኮንን የ14 ዓመት ልጅ ሳሉ፤ አባታቸው ልዑል ራስ መኮንን ወልደ ሚካኤል፤ ባደረባቸው ሕመም ምክንያት ከዚህ ዓለም በሞት ተለዩ፡፡ ቀብራቸውም እርሳቸው ባሰሩት በቁልቢ ቅዱስ ሚካኤል ቤተ ክርስቲያን ተፈፀሟል፡፡
ዳግማዊ ምኒልክ ለኢትዮጵያ ልጆች የውጭ አገር ቋንቋ የሚማሩበት ትምህርት ቤት ከፍተው ስለነበር፤ ደጃዝማች ተፈሪ መኮንንም እንዲማሩ ጥያቄ አቅርበው ስለተፈቀደላቸው ትምህርታቸውን ጀመሩ፡፡
የደጃዝማች ተፈሪ መኮንን አባት ራስ መኮንን ሲሞቱ፤ የልጅ ተፈሪ መኮንን የአባታቸው ልጅ የሆኑት ወንድማቸው ደጃዝማች ይልማ፤ የሐረር አስተዳዳሪ ሆነው ተሾሙ፡፡
ደጃዝማች ተፈሪ መኮንን ደግሞ የሰላሌ ገዥነትን ተሾሙ። ነገር ግን በቤተ መንግሥት ፖለቲካ ምክንያት፣ አዲስ አበባ በሚገኘው የአፄ ምኒልክ ቤተ መንግሥት ውስጥ ተወስነው በመቅረታቸው፣ የቤተ መንግሥቱን ፖለቲካዊ እንቅስቃሴንና ጥበብን መማር ቻሉ፡፡
ከደጃዝማች ተፈሪ ደጋፊዎች መካከል አንዱ የሆኑት ዳግማዊ አፄ ምኒልክ ሲታመሙ፤ (ተፈሪን ከቤተ መንግሥት ለማራቅ ይመስላል) "በግዞት" ደቡብ ኢትዮጵያ ወደሚገኘው ወደ ሲዳሞ ጠቅላይ ግዛት ተዛውረው አስተዳዳሪ ሆነው እንዲሠሩ ወደሥፍራው ተላኩ።
ሲዳሞ በነበሩበትም ወቅት ቁጥሩ 3 ሺህ የሚደርስ ሠራዊት ነበራቸው።
የሐረር አስተዳዳሪ ሆነው የተሾሙት ደጃዝማች ይልማም ሥልጣን እንደያዙ ብዙም ሳይቆዩ ከዚህ ዓለም በሞት ተለዩ።
በኋላም ደጃዝማች ተፈሪ የአባታቸውን ግዛት ሐረርን እንዲያሰተዳድሩ በአቴጌ ጣይቱ ሹመት ተሰጣቸው፡፡
ለፎቶው ምስጋና፤ Getish Ras Teferi
Photo Credit to: image link