እቴጌ ጣይቱ የውጫሌን ውል በተመለከተ ጠንካራ አመራር የሰጡና ወሳኝ ሚና የተጫወቱ መሪ ነበሩ፡፡ እቴጌ ጣይቱ፤ የውጫሌን ውል በተመለከተ ሲወያዩ የኢጣሊያ ተወካይ የሆነው የአንቶኒሊ ንግግር ስለአበሳጫቸው፣ ወዲያውኑ የእርሱን ንግግር አቋርጠው፤
“ያ አንቀጽ የሚለውን ነገር እኛም ለኃያላን መንግሥታት አሳውቀናል፡፡
…እንዳንተ ሁሉ እኛም ክብራችንን እንጠብቃለን፡፡
እናንተ የምትመኙት፤ ኢትዮጵያ በእናንተ ስልጣን ስር እንድትሆን ነው፡፡
ይህ ለምን ጊዜም የማይሆን ነገር ነው፡፡”
በማለት መልስ ሰጥተውታል፡፡
አንቶኒሊ፤ የውጫሌን ውል፤ የኢጣሊያ መንግሥት በጦር ኃይል እንደሚያስከብር በተናገረ ጊዜ፣ ይህን ንግግር የሰሙት እቴጌ ጣይቱ እየሳቁ፤
“የዛሬ ሳምንት አድርገው፡፡ በዚህ የሚደነግጥልህ የለም፡፡ ሂድ የፎከርክበትን አድርግ፡፡
እግሩን ለጠጠር፣ ደረቱን ለጦር ሰጥቶ አገሩን የሚያድን ሰው በዚህ የሌለ አይምሰልህ፡፡
የገዛ ደሙን ገበሮ ለገዛ አገሩ መሞት ጌጥ ነው እንጅ ሞት አይባልም፡፡
አሁንም ሂድ አይምሽብህ፤ የፎከርክበትን በፈቀድህ ጊዜ አድርገው፡፡
አኛም ከዚህ እንቆይሀለን፡፡”
ካሉት በኋላ፤
“…እኔ ሴት ነኝ፡፡ ጦርነት አልወድም፡፡ ግን እንዲህ መሳዩን ውል ከመቀበል፣ ጦርነትን እመርጣለሁ፡፡”
በማለት ቁርጥ ያለ የአገር ወዳድ የጀግና መልስ ሰጥተዉታል፡፡
በመጨረሻም በኢትዮጵያና በኢጣሊያ መንግሥት መካከል የነበረው ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት ሻክሮ ወደማይቀረው የአድዋ ጦርነት ሲያመራ በራሳቸው የሚመራ ጦር አደራጅተው ከባለቤታቸው ከምኒልክ ጎን ለውጊያ የተሰለፉ ቆራጥ ሴት ነበሩ፡፡
እቴጌ ጣይቱ ለማይቀረው የአድዋ ጦርነት ከአፄ ምኒልክ ጋር መቀሌ ከደረሱ በኋላ የጦር አለቆች የሆኑትን እነ ራስ መኮንንን ሰብስበው፤
“…አንድ የኢጣሊያ ሹም እናንተን ሁሉ ንቆ እስኪመሽግ ድረስ ዝም ብላችሁ በመቆየታችሁ አፈርኩባችሁ፡፡” ብለዋቸዋል፡፡
የመቀሌ የጠላት ምሽግ በወንዶች ጀግንነት አልፈታ ሲል በሴት ብልሀት ተተካ፡፡
እቴጌ ጣይቱ ከመቀሌ የጠላት ምሽግ በግምት 75 ሜትር ርቀት የሚገኘውን የውሀ ጉድጓድ፤ ጣሊያኖች ውሀ እንዳይቀዱ ለማድረግ 500 በሚሆኑ ኢትዮጵያውያን ወታደሮች እንዲያዝና እንዲጠበቅ አዘዙ፡፡
በዚህም መሠረት በምሽጉ ያሉት የኢጣሊያ ወታደሮችና እንስሳት ሳይቀሩ በውሀ እጦት እጅግ ተሰቃዩ፡፡
በኢጣሊያ ያሉ ጋዜጦችም፤
“…ታላቅ ምሽግ ነው የተባለውንም የመቀሌ ምሽጋችንን ደግሞ በውሀ እጦት ለቀቅን፡፡
ይህ የኢጣሊያን መንግሥት ውድቀት ስለሚያሳይ፤ መንግሥታችን ድል መደረጉን አምኖ ከአበሻ ምድር ለቆ መውጣት አለበት፡፡”
በማለት ጽፈዋል፡፡
በመጨረሻም በእኝህ ጀግና ሴት ብልሀት፤ ጠላት ውሀ ጥሙን መቋቋም ባለመቻሉ ምክንያት ጠንካራ ምሽጉን ለቆ ለመውጣት ተገዷል፡፡
የኒውዮርክ ታይምስ፣ የፈርንሳዩ ጋዜጣ ለፐቲት ጆርናል፣ እና ሐርፐርስ ዊክሊ የተባሉት ዓለም አቀፍ ጋዜጦች ስለአድዋ ድል ሲተርኩ፤ እቴጌ ጣይቱን በ3ኛው ክፍል ዘመን በኢጣሊያ የፓልምሪን ኢምፓየር ንግሥት ከነበረችው ከንግሥት ዜኖቢያ፣ ከክርስቶስ ልደት በፊት ከ51ኘው እስከ 30ኛው ዓመተ ዓለም፤ የግብፁ የፕቶሎሚክ ሥርወ መንግሥት የመጨረሻዋ
ንግሥት ከነበረችው ከክሊዎፓትራና እንዲሁም በ18ኛው ክፍለ ዘመን የሩሲያ ንግስት ከነበረችው ከታላቋ ካትሪን ጋር እያመሳሰሉ ኃያልነቷን በመግለፅ ዘግበዋል፡፡
ሐምሌ 8 ቀን 1888 ዓ.ም. ቴምፕስ የተባለው ጋዜጣ፤
“…ጣይቱ በግቢያቸው ውስጥ ባለው ሜዳ ላይ ምረኮኞቹን ይጋብዙ ነበር፡፡
…ከጀነራል አልቤርቶኒ ጀምሮ ሁሉም በአንድነት በአውሮፓውያን ደንብ መሠረት ይጋበዛሉ፡፡ ...በሚመገቡበት ጠረጴዛ ላይ፤ ሰሀን፣ ሹካ፤ ማንኪያ፤የአፍ መጥረጊያ ፎጣ፤ አበባና የሚጠጡት ቪኖ ሳይቀር ይደረገልቻው ነበር፡፡”
በማለት ሰለ እቴጌ ጣይቱ ትህትናና ጥበብ ዘርዝሮ ጽፏል፡፡
ከዚህ በታች የቀረበው ስዕል፤ ከአድዋ ድል በኋላ ‘የእቴጌ ጣይቱ መታሳቢያ ይሁን’ በማለት በኢጣሊያ አገር የሚገኝ አንድ የጣፋጭ ከረሜላ አምራች ፋብሪካ፤'VIVIDENT'
በተሰኘው የፋብሪካው ብራንድ ምርት ላይ የእቴጌ ጣይቱን ምስልና ስም በማውጣት ለ 60 ዓመታት ያህል በተከታታይ ለሽያጭ አቅርቦት እንደነበር ተረጋግጧል፡፡