Content-Language: am ቢተወደድ አያሌው መኮንን
header image




ቢተወደድ አያሌው መኮንን


1. ትውልድ፣ ዕድገት፣ ትምህርትና የልጅነት ዘመን

Zerai Deres
ክቡር ቢተወደድ አያሌው መኮንን
ክቡር ቢትወደድ አያሌው መኰንን በ1891 (፲፰፻፺፩) ዓ.ም ሕዳር 27 (፳፯) ቀን በቀድሞው ጎጃም ጠቅላይ ግዛት በባሕር ዳር አውራጃ በአቸፈር ወረዳ አሹዳ አቦ በተባለች ቀበሌ ከአባታቸው ከፊታውራሪ መኰንን ዋሴና ከእናታቸው ከወይዘሮ የውብዳር ንጉሤ የተወለዱ ጀግና አርበኛ ናቸው፡፡
በትምህርት ቤት ቆይታቸው የሥነ መንግሥት ትምሕርታቸውን በቅልጥፍናና በከፍተኛ ውጤት ካጠናቀቁ በኋላ አገራቸው ማገልገል የጀመሩት ገና የ፲፰ ዓመት ወጣት ሳሉ ልጅ ተብለው በጉልተ ገዥነት ሲሾሙ ነበር፡፡
በ1913 (፲፱፻፲፫) ዓ.ም. ልዑል ራስ ኃይሉ ተክለ ሃይማኖት የጎጃምን ጦር ይዘው ወደ ሰገሌ በዘመቱ ጊዜ ልጅ አያሌው መኰንንም በአባታቸው በፊታውራሪ መኰንን ዋሴ ስር ዘምተው ባሳዩት ብቃት ወደ ግዛታቸው ሲመለሱ ልዑል ራስ ኃይሉ ተክለሃይማኖት የግራዝማችነት ማዕረግ ሰጥተዋቸዋል፡፡
ከዚያው ልዑል ራስ እምሩ ኃይለ ሥላሴ ጐጃምን ያስተዳድሩ በነበሩበት ጊዜ የግራዝማች አያሌውን አግልግሎትና ብቃት ተመልክተው አስቀድሞ ከሚያስረዳድሩት አድቤ ከተባለው ግዛት ሌላ በአቸፈር ወንድየና አሥራ ደብር ውስጥ የባሕር ዳር ሚካኤል አስተዳደር ተጨመሮላቸዋል፡፡

2. በ1928 (፲፱፻፳፰) ዓ.ም. የፋሽት ኢጣሊያ ወረራ ወቅት የክቡር ቢትወደድ አያሌው የአርበኝነት ተግባር

በ1928 (፲፱፻፳፰) ዓ.ም. የፋሽት ኢጣሊያ ኢትዮጵያ በግፍ በወረረች ጊዜ በልዑል ራስ እምሩ አዝማችነት ወደ ማይጨው ሲዘምቱ አባታቸው በሽምግልና ምክንያት በልዑልነታቸው ፈቃድ ግዛታቸውን እንዲጠብቁ ስለቀሩ ፣ ግራዝማች አያሌው ከራሳቸው ጦር ሌላ የአባታቸው እንደራሴ በመሆን ዘምተው ሽሬ ላይ 3 ቀን ሙሉ በጀግንነት ተዋግተው ከፍተኛ ጀብድ ፈጽመዋል፡፡

3. ከአርበኝነት መልስ የገጠማቸው እስር


Zerai Deres
ከቀኝ ወደ ግራ፤ ልጃቸው ዳኝነት አያሌው፣
ክቡር ቢተወደድ አያሌው መኮንን፣
ባለቤታቸው ክብርት ወይዘሮ ደጊቱ ላቀው እና
ከህፃንነቱ ጀምሮ አብሯቸው ያደገው አቶ ቁምላቸው አለኸኝ
ምስጋና ለ፤ አቻምየለህ ታምሩ ethioreference.com
ከማይጨው ጦርነት መልስ ከልዑል ራስ እምሩ ጋር በመሆን ልዑልነታቸውን ወደ ጎሬ ሸኝተው ከተሰናበቱ በኋላ ወደ ትውልድ ቦታቸው ተመለሱ። አቸፈር እንደደረሱም ለአርበኝነት የሚያደርጉትን ዝግጅት ጠላት ስለደረሰበት ፋሽስቶች ከአባታቸው ከፊታውራሪ መኰንን እና ከሌሎች ቤተሰቦቻቸው ጋር በአቸፈር ወረዳ ውስጥ ይስማላ ጊዩርጊስ አሰሯቸው።

4. ከፋሽስት እስር ቤት ስለማምለጥ

ፊታውራሪ አያሌው ለሰባት ወር ያህል በጥብቅ ከታሰሩ በኋላ በ1929 (፲፱፻፳፱) ዓ.ም በሐምሌ ወር በባሕር ዳር ከተማ የታሰሩት አባታቸውና የእኅታቸው ባል በግፍ መገደላቸውን እንደሰሙ ወዲያውኑ አብረዋቸው የታሠሩትን ወንድሞቻቸውን ይዘው በሚያስደንቅ ሁኔታ ከፋሽስት እስር ቤት ሰብረው አመለጡ።

5. ከእስር ቤት ካመለጡ በኋላ በአርበኝነት ዘመናቸው በተከታታይ ያደረጓቸው ተጋድሎዎች


ክቡር ቢተወደድ አያሌው መኮንን ከመታሰራቸው በፊት ደብቀውት የነበረውን የጦር መሣሪያ ከየቦታው በማሰባሰብ፤ መውጫ መግቢያውን አጥርተው ወደሚያውቁት ዝብስት ተብሎ ወደሚጠራው በረሃ ከገቡ በኋላ ከፋሽስት ጋር ስለሚያደርጉት ከጣይ ተጋድሎ ከወንድሞቻቸውና ከግብረ አበሮቻቸው ጋር ሲመካከሩ ለጥቂት ሳምንቶች ያህል ቆዩ፡፡
  1. ጠላትም ከወሕኒ ቤት ሰብረው ማምለጣቸው እንደተረዳ እሹዳ አቦ በሚበለው ቀበሌ የነበረውን የእርሳቸውንና የአባታቸውን ንብረት በሙሉ ዘርፎ ካቃጠለው በኋላ፤ ግራዝማች አያሌውም ወዲያውኑ ጦር ካሰባሰቡ በኋላ፣ ለሰባት ወር ታስረው ከነበሩበት ይስማላ ከሚባለው አገር ላይ የነበረውን የጠላት ጦር መስከረም 3 (፫) ቀን 1930 (፲፱፻፴) ዓ.ም ገጥመው ጠላትን መግቢያና መውጫ በማሳጣት የጠላትን ካምፕ በማፈራረስ ጠላት ያከማቸውን የጦር መሣሪያና ማንኛውንም ንብረት በሙሉ ማርከው መውሰድ ችለዋል።
  2. ቀጥሉም መስከረም 5 (፭) ቀን 1930 (፲፱፻፴) ዓ.ም ዳንግላ ከተማ በነበረው የፋሽስት ኢጣሊያ ማእከል ላይ የተደረገውና ብዙ ፋሽቶችና ባንዶች ለመጀመሪያ ጊዜ ክፉኛ ያለቁበትን ታላቅ ጦርነት የመሩት ግራዝማች አያሌው መኮንን ናቸው። በዚሁ ዓመት ያቸፈር ሕዝብ ተሰብስቦ በግፍ ለተገደሉባቸው አባታቸው ሙት ዓመትና ስለእርሳቸውም አገልግሎት ያቸፈር ገዥና ጦር መሪ እንዲሆኑ በሙሉ ድምጽ መርጧቸዋል፡፡ በዚያን ወቅት አቸፈር ይባል የነበረው ግዛት 114 ደብሮችን ያጠቃልል እንደነበር ተዘግቧል።

  3. ከዚህ በኋላ ግራዝማች አያሌው የሕዝቡን ድጋፍና መተባበር በማግኘታቸው በየጊዜው ከጠላት ጋር መግጠምና ጠላት አቸፈር እየመጣ የጦር ሰፈር ለመሥራት ከሚሞክረው ወራሪ ጋር ሁሉ ያለዕረፍት በመዋጋት ያርበኝነት ትግላቸውን ቀጠሉ፡፡
  4. በ 1930 (፲፱፻፴) ዓ.ም በታህሳስ ወር፤ ዝብስት ውስጥ የሚኖሩት ግራዝማች አያሌው በወታደርና በመሣሪያ መደርጀታቸውን ጠላት ስለአወቀ ከዳንግላ፤ ከቁንዝላና ከወተት ዓባይ የነበረውን ጦር ይዞ በአይሮኘላይ እየተረዳ ግራዝማች አያሌውን ገጠማቸው፡፡
  5. ግራዝማች አያሌው ከአቸፈር ጀግኖች ወንድሞቻቸው ጋር በመሆን በተፈጥሮዋ ለጠላት በማትመቸው በዝብስት ተራራና ሸንተረር ላይ በማድፈጥ በአይሮኘላን እየተረዳ የመጣውን የጠላት ጦር መድረሻ በማሳጣት ወደ መጣበት መልሰውታል።
    በዚህን ጊዜ ጠላት የወሰደው ርምጃ ውጤት እንዳላስገኘለት ስለተረዳው ሽማግሌዎችን በመላክ ለመታረቅ ሞክሮ ነበር፡፡ ሆኖም ግራዝማች አያሌው ለፉሺስት ስብከት ሳይታለሉ ውጊያቸውን ቀጠሉበት።
  6. ግራዝማች አያሌው ከንጉሠ ነገሥት ግርማዊ ቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ ጋር መላላካቸውና የእርሳቸው መልከተኛ የሆኑትን ደጃዝማች ከበደ ተሰማን እየተቀበሉ ማስተናገዳቸውን ጠላት ይሰማ ስለነበረ ጠላት በጠቋሚ ተመርቶ ሌሊቱን ሲጓዝ አድሮ ሠራዊታቸውን ለዕረፍት አሰናብተው ሳለ ጥቂት ሆነው በሰፈሩበት መንደር አምባ ጊዩርጊስ ላይ ደርሶ ሳይታሰብ አደጋ ጣለባቸው፡፡ በዚህ ወቀት በተደረገው የጨበጣ ውጊያ እርሳቸውና ሁለቱ ወንድሞቻቸው ቢቆስሉም እጃቸውን ለጠላት ሳይሰጡ በሚያስደንቅ የመከላከል ጀግንነት ወደዝብስት በረሃ መግባት ችለዋል።
  7. ከጠላት በተወረወረው ቦምብና በተተኰሰው ጥይት እግራቸውን የተመቱት ግራዝማች አያሌውና ወንድሞቻቸው በበረሃ ሆነው ቁስላቸው እስኪያገግም ድረስ ከቆዩ በኋላ በየካቲት ወር 1930 (፲፱፻፴) ዓ.ም እርሳቸውን አድኖ ለመያዝ ከተላከው የጠላት ጦር ጋር አዳምና ከተባለው መንደር ላይ ተጋጥመው ብዙ ጀግኖች ወንድሞቻቸው በጦሩ ሜዳ በጀግንነት ተነባብረው ወድቀዋል።
    ግራዝማች አያሌው ተቀምጠውባት የነበረችው በቅሎ በጥይት ተመትታ ስትወድቅ እርሳቸው ግን ምንም ሳይሆኑ በጠላት ላይ ብዙ ጉዳት አድርሰው ፋሽስትን ወደ መጣበት መልሰውታል፡፡
  8. ግራዝማች አያሌው ምንም እረፍት ሳያገኙ ጦርነት ቀጥሎ በሚያዝያ ወር 1931 (፲፱፻፴፩) ዓ.ም እርሳቸውን ለማሳደድ ከተላከው ጦር ጋር ጭቃ ወንዝ የተባለውስፍራ ላይ ተጋጥመው ብዙ ሰዓት ከተዋጉ በኋላ ጠላት ሽንፈትን ተከናንቦ ወደ ጦር ሰፈሩ ወደ ዳንግላ ለመመለስ ተገዷል፡፡

  9. በዚህ ወቅት የማረኩትን የፋሽስት ወታደር መሬት ለመሬት እየጎተቱ ወደ አምባ ጊዮርጊስ ሲወስዱ የተመለከተ የራሳቸው ወታደር የሚከተለውን ግጥም ገጥሞላቸዋል።

ቤልጅግህ ዘበኛ ጓንዴህም ዘበኛ፣
የመጣውን ጠላት አንጥፎ ሲያስተኛ፤

ይህን የግራዝማች አያሌውን ተከታታይ የጀግንነት ገድል የተመለከተው የአገራቸው ሕዝብ የጦር መሪ አድርጎ የሾማቸውን መሪውን ቅጠል በመበጠስ በጭንቅላታቸው ላይ እየጣለ “ፊታውራሪ ብለን ሾመንዎታል” ብለው የፊታውራሪነት ማዕረግ የሰጣቸው በዚሁ በ1930 ዓ.ም ነበር።

6. ፊታውራሪ አያሌው ከጠላት ጋር በተከታታይ ውጊያ ገጥመው ድል የተቀዳጁባቸው የውጊያ አዉዶች

  1. በጥር ወርና እንዲሁም ግንቦት 1 (፩) ቀን 1930 (፲፱፻፴) ዓ.ም፤ ከየጦር ሰፈሩ ማለትም፤ ከቁንዝላ፣ ከይስማላ፣ ከወተት ዓባይ፣ ከዳንግላና ከባሕር ዳር የተውጣጣ፤ በመትረየስና በቦምብ እንደሁም በከባድ መሳሪያ የታገዘ የጠላት ጦር፤ ፊታውራሪ አያሌው ባገኙት የተፈጥሮ ጀግንነት ተጠቅመው ሲገሰግስ በመጣው ወራሪ ጠላትላይ ብዙ ጉዳት በማድረስ ወደ የጦር ሰፈሩ እንዲመለስ አድርገውታል፡፡
  2. ኮሎኔል ቶሌሬ የተባለው የፋሽስት ጦር መሪ በ1932 (፲፱፻፴፪) ዓ.ም. ዝብስት በተባለው ስፍራ ለ3ኛ ጊዜ ፊታውራሪ አየሌውን ገጥሟቸው የብዙ ወታደሩን ሬሣ ጥሎ ተመልሷል፡፡
  3. ንጉሠ ነገሥቱ ቀዳማዊ ኃይለሥላሴ ለመምጣት በተቃረቡበት ሰዓት ሞራላቸው የበለጠ የጠነከረበት ጊዜ ስለነበር ፊታውራሪ አያሌው ጠላትን ንፉሳ ጊዩርጊስ ላይ ተጋጥመው ድል አድርገው መልሰውታል፡፡
  4. በ1932 (፲፱፻፴፪) ዓ.ም በጷጉሜ ወር ፊታውራሪ አያሌው መኮንን፤ እነክቡር ደጃዝማች ከበደ ተሰማንና ኰሎኔል እስታንፈርድን ዝብስት በተባለው ስፍራ ለመቀበል በሚዘጋጁበት ሰዓት፤ የእንግዶችን ከግርማዊ ጃንሆይ ተልኰ መምጣት ጠላት ሰምቶ ኖሮ ከየጦሩ ሰፈሩ ያለውን ጦር ሰብስቦ ዝብስት ላይ ለአራተኛ ጊዜ ገጥሞ ከባድ ውጊያ ከተደረገ በኋላ ጊዜያዊ የጫካ ቤታቸውን ብቻ በጣለው የአውሮፕላን ቦንብ አቃጥሎ ተመለሷል።
  5. ይስማላ የተባለው ስፍራ ላይ መጥቶ የሰፈረው የጠላት ጦር በቀኛዝማች አያሌው ጦር ዕረፍት ስላጣ ካምቱን ለቆ ወደ በጌምድር ጠቅላይ ግዛት ሲሄድ፤ ፊታውራሪ ተከታትለው ድኩልካን ከተባለው ቀበሌ ላይ ጠላትት ውጊያ ገጥመው እስከ ምሽጉ ድረስ ተዋግተው ጠላትን አውድመው ተመልሰዋል።
  6. በ1933 (፲፱፻፴፫) ዓ.ም አለፋ ሻሁራ ላይ የሰፈረውን የጠላት ጦር ውጊያ በመግጠም የጠላትን ምሽግ በማፍረስ ድል አድርገው ካባረሩ በኋላ ነጻ አድርገው ያስተዳድሩት በነበረው የአቸፈር ግዛታቸው ላይ በተጨማሪ በሻሁራው ጦርነት ነጻ ያወጡትን አለፉን ደርበው ማስተዳድር ጀመሩ።
  7. ባሕር ዳርን ለማስለቀቀ በተደረገው ዘመቻም ትልቁን ድርሻ የተወጣው የቢትወደድ መንገሻ ጀምበሬና የፊታውራሪ አያሌው መኮንን ጦር ነበር።

  8. ግርማዊ ቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ ከስደት ተመልሰው የኢትዮጵያን ምድር ሲረግጡ የኢትዮጵያን ሰንደቅ ዓላማ ለመጀመሪያ ጊዜ በኢትዮጵያ ምድር የሰቀሉበት ጎጃም ውስጥ የሚገኘው በላያ ከፋሽስት ነጻ የወጣው በፊታውራሪ አያሌው መኮንን ጦር ተጋድሎ ነበር።
    ንጉሡም በሱዳን በኩል አድርገው ጎጃም እንደገቡ ወደ ደብረ ማርቆስ ሲያልፉ ቡሬ ድረስ የሸኟቸው ፊታውራሪ አየሌው መኮንን ነበሩ።

7. ፊታውራሪ አያሌው የተሰጣቸው ሹመትና ያገኟቸው ሽልማቶች

ጠላት አገራችንን ለቆ ከወጣ በኋላ፤
  • በግንቦት ወር 1933 (፲፱፻፴፫) ዓ.ም ተመስርቶ የአገር አስተዳደር ሲደለደል ፊታውራሪ አያሌው መኮንን ያገውምድር አውራጃ ገዥና የአቸፈር ወረዳ የበላይ አስተዳዳሪ ሆነው ተሾሙ፡፡
  • በ1935 (፲፱፻፴፭) ዓ.ም ደግሞ ደጃዝማች ተብለው ወደ አቸፈር ግዛታቸው ተመልሰው ከቆዩ በኋላ በ1942 (፲፱፻፵፪)ዓ.ም እንደገና ያገው ምድርና የባሕር ዳር አውራጃ አስተዳዳሪ ሆነው ተሾሙ።
  • በ1943 (፲፱፻፵፫) ዓ.ም የቆላ ደጋ ዳሞት አውራጃ አስተዳዳሪ ሆነው በመሾም 18 (፲፰) ዓመት ሙሉ በመልካም መግባባት ከማስተዳደራቸውም በላይ በዚሁ ዓመትም ደግሞ የቢትወደድነት ማዕረግ አግኝተዋል፡፡
  • በ1961 (፲፱፻፷፩) ዓ.ም ለ3ኛ (፫ኛ) ጊዜ ያገው ምድር አውራጃ ገዥ ሆነው በመሾም እስከ 1962 (፲፱፻፷፪) ዓ.ም መጨረሻ ድረስ አገልግለዋል፡፡

ቢትወደድ አያሌው ከዚህ በላይ ከተጠቀሰው አገግሎታቸው በተጨማሪ ከግርማዊ ንጉሠ ነገሥት ቀዳማዊ ኃይለ ሥላሰ የሚከተሉትን ሽልማቶች ተሸልመዋል፤
  1. የአርበኝነት ሜዳይ ባለ 4 ዘንባባ
  2. የድል ኰከብ ሜዳይ
  3. የኦሜድላ መታሰቢያ ሜዳይ
  4. የቅዱስ ጊዮርጊስ የጦር ሜዳ ሜዳይ ባለ፫ ዘንባባ
  5. የኢትዩጽያ የክቡር ኰከብ አዛዥ መኰንን ኒሻን
  6. የኢትዩጽያ የክቡር ኰከብ ታላቅ መኰንን ኒሻን
  7. የዳግማዊ ምኒልክ ታላቅ መኰንን ኒሻን

8.የክቡር ቢተወደድ አያሌው መኮንን ሕልፈተ ሕይወትና የቀብር ሥነ ሥነስርዓት

ሰው ሆኖ ተፈጥሮ ምንም ጀግና፣ ደግ፣ አዋቂ፣ በሰውም ዘንድ የተወደደና የተከበረው ቢሆን ቅሉ ከመሞት የሚቀር የለምና ፣ ቢተወደድ አያሌው መኮንን ባደረባቸው ሕመም ምክንያት ባሕር ዳር በፈለገ ሕይመት ሆስፒታል በሕክምና ሲረዱ ቆይተው በተወለዱ በ72 (፸፪) ዓመታቸው ሐምሌ 20 (፳) ቀን 1963 (፲፱፻፷፫) ዓ.ም ከዚህ ዓለም በሞት ተለይተዋል፡፡
እስከሬናቸው ዳንግላ ከተማ ወደሚገኘው መኖሪያ ቤታቸው ተወስዶ ጸሎተ ፍትሐት ሲደረግለት አድሮ ሐምሌ 21 (፳፩) ቀን 1963 (፲፱፻፷፫) ዓ.ም የጐጃም ጠቅላይ ግዛት እንደራሴ ክብር ደጃዝማች ደረጃ መኰንንና ምክትል እንደራሲው ክቡር ደጃዝማች ደረሰ ሽፈራው፣ የጠቅላይ ግዛቱ ሊቀ ጻጻስ ብፁዕ አቡነ ማርቆስ ፣ ያውራጃው ገዥዎችና ከፍተኛ ሹማምንት፤ በየጦሩ ሜዳ ያልተለያቸው በብዙ ሺህ የሚቆጠሩ የቢትወደድን የጀግንነት ሞያና የጦር ሜዳ ውሎ የሚያውቁ የአቸፈር አርበኞች እና በተጨማሪም ለኀዘኑ ተካፉይ ለመሆኑ ከተለያዩ አካባቢዎች የተሰባሰቡ ቁጥራቸው ከ10 (፲) ሺህ በላይ አዘንተኞች በተገኙበት እስከሬኑ ከቤት ወጥቶ የጦር መሣሪያ በያዙ አርበኞች ታጅቦ ጥቂት እንደተጓዘ ከደብረ ማርቆስ የተላከው የክብር ዘበኛ ሠራዊት የክብር ሰላምታ ሰጥቶ ከተረከበው በኋላ ጉዞው ወደ አጉንታ ማርያም ቀጥሎ ከቤተ ክርስቲያኑ እንደደረሰ ጸሎተ ፍትሐቱ ተፈጽሞ የክብር ዘቡ በጀኔራልነት ማዕረግ የመጨረሻ የክብር ሰላምታ ከሰጠ በኋላ የኀዘን ማርሽ አሰምቶ ሲያበቃ አጭር የሕይወት ታሪካቸው ተነቦ አስከሬኑ በተዘጋጀለት የአርበኞች ሥፍራ በክብር አርፏል።
በመጨረሻም አስከሬኑ በክብር ካረፈ በኋላ የጐጃም ጠቅላይ ግዛት እንደራሴ ክብር ደጃዝማች ደረጃ መኰንን ከግርማዊ ንጉሠ ነገሥት የተላከውን የኀዘን መግለጫ ቴሌግራም ለክብርት ባለቤታቸው እስረከበዋል፡፡







ምንጭ፤
  1. ምስጋና ለ፤ አቻምየለህ ታምሩ  ethioreference.com  May 30, 2020