Content-Language: am ራስ ቢትወደድ መንገሻ አቲከም
header image




የሴት አርበኛ ወይዘሮ ልክየለሽ በያን



የሴት አርበኛ ወይዘሮ ልክየለሽ በያንን
የአርበኝነት ዘመን ታሪክ ያዳምጡ














1. ትውልድና ዕድገት

Woyzero Likyelesh Beyan
የሴት አርበኛ ወይዘሮ ልክየለሽ በያን
የወይዘሮ ልኬለሽ በያን አባት፣ በያን ኢብሳ ሲሆኑ እናታቸው ወይዘሮ ይጎዝጎዙ ሽብሩ ይባላሉ፡፡
ልክየለሽ በያን በድሮው አጠራር በከንባታ አውራጃ በሆሳዕና ከተማ በ 1902 ዓ.ም ተወለዱ:: በአካባቢው ወግና ባህል ያደጉት አርበኛ ልክየለሽ የአብነት ትምህርት ተከታትለው ዳዊት እስከመድገም ደርሰዋል:: በነበራቸውም የማንበብና የመጻፍ እውቀት ተጠቅመው፣ የሚፈልጉትን መልእክት ማስተላለፍ ይችሉ ነበር::
አርበኛ ልክየለሽ ለአቅመ ሄዋን ሲደርሱ እንዳደጉበት ማህበረሰብ ባህልና ወግ ትዳር የመሠረቱት በልጅነታቸው ነበር::

2. የወይዘሮ ልኬለሽ በያን የአርበኝነት ዘመን

አርበኛ ልክየለሽ በያን፤ ፋሽስት ኢጣሊያ በ1928 ዓ.ም ኢትዮጵያን ለሁለተኛ ጊዜ በወረረችበት ወቅት የአያታቸውን የአቶ ሽብሩ ጤናውን ጠመንጃ ይዘው የከምባታ አውራጃን ጦር አስከትለው ከዘመቱት በደጃዝማች መሸሻ ወልዴ አዝማችነት እና በፊትአውራሪ ወልደፃድቅ ሻምበል አዛዥነት ወደ ሰሜን የጦር ግንባር ተንቤን አቢ አዲን፣ ከረን ወርቅ ግዛ ወንዝ መዝመታቸውንና ብሎም ከማይጨው ከታላቁ ጦርነት ውለው በአራስ ሴት አቅም ለመስራት የሚከብዱ ልዩ ልዩ ጀብዶችን ፈጽመዋል፡፡
አርበኛዋ የአገራቸውን ነፃነት በማስቀደም በወቅቱ የአራት ወር ተኩል ህፃን ልጃቸውን ትተው በመሄድ ሀገር ከሚስት ፣ ከልጅ ፣ ከባልና ከቤት ጭምር ሁሉ እንደሚበልጥ በተግባር ያሳዩ ሀሞተ መራራ፣ ጀግና እናት አርበኛ መሆናቸውን በተግባር አስመስክረዋል::
የሰሜኑ ጦርነት በኢጣሊያ የበላይነት ከተጠናቀቀ በኋላም አርበኛ ልክየለሽ በያን እንደሌሎች አርበኞች ሁሉ ወደ ትውልድ አካባቢያቸው ተመልሰዋል::
በኋላም 1930 ዓ.ም ቀንደኛ የፋሽስት ባንዳ የነበሩትን ቀኝአዝማች ኩንቢን በመግደል ናስማሰር ጠመንጃቸውን በመማረክ ጫካ ገቡ:: በተመሳሳይ ዓመትም ከባለቤታቸው ከበቀለ ካሳየ ጋር በመሆን በድንገት ተኩስ በመክፈት በርካታ የፋሽስት ወታደሮችን ከገደሉና ካቆሰሉ በኋላ በጊዜው አጠራር አንድ በውሃ የሚቀዘቅዝ መትረየስ ከጠላት ማርከዋል:: መትረየሱንም በወቅቱ የተሻለ እንቅስቃሴ ለነበረው ለራስ አበበ አረጋይ በማስረከባቸው ታሪካቸውን የበለጠ እንዲጎላ አድርጎታል::
Patriot Likyelsh Beyan
ከግራ ወደቀኝ፤ የአርበኛ ልክየለሽ በያን
ሴት ልጅ በቀለች መኮንን፣
አርበኛ ልክየለሽ በያን እና፣ መትረየስ ተኳሽ አርበኛ
 Photo Link

መስከረም 1931 ዓ.ም ሮቤ ወንዝ አጠገብ ሲዋጉ ባለቤታቸው ውጊያው ላይ በመገደላቸው፣ የባለቤታቸውን አንገት ቆርጠው ለመውሰድ የመጡትን ባንዳዎች፣ ከባለቤታቸው ወገብ የነበረውን ቦንብ በመወርወር፣ አራቱንም በመግደል ሬሳው እንዳይማረክና በአግባቡ እንዲቀበሩ አድርገዋል፡፡ ባለቤታቸው ይመሩት የነበረውን አንድ ሻምበል መትረየስ ተኳሽ ጦር መሪነት በመረከብም በሚገባ አዋግተዋል፡፡
አርበኛዋ በአንድ ወቅት ከጠላት ጋር በመዋጋት ላይ እያሉ የጦሩ ሚዛን ወደ ጠላት ሲያመዝን ቦታቸውን ለቀው አፈገፈጉ:: በወቅቱም ወይዘሮ ልክየለሽ በያን በጦር ሜዳ ውሏቸው ሁልጊዜም የኢትዮጵያ ሰንደቅ ዓላማ አይለያቸውም ነበር:: ያን ቀን ግን ትግል ላይ እያሉ ድንገት ሳያዩት በመውደቁ ጥለውት ሄዱ:: መንገድ ላይ እያሉም ሰንደቅ ዓላማ አለማያዛቸው ትዝ ሲላቸው፤
“ወይኔ ኢትዮጵያ… እረስቸሻለሁ፤ ከሞትሁም ልሙት እንጂ ሰንደቅ ዓላማዬን በፍጹም ለኢጣሊያ አላስረክብም!”
ብለው ወደ ኋላ ተመልሰው ሲሄዱ ውጊያ ውስጥ በመግባታቸው በጠላት ጥይት ቆሰሉ:: አርበኛዋ ቆስለው ከወደቁበት ቦታ ላይ እንዳሉ በጠላት ወታደሮች ተማረኩ:: የጠላት ወታደሮችም ከፍተኛ እንግልትና ስቃይ አድርሶባቸዋል፡፡
በወቅቱም ጣሊያኖች ኢትዮጵያንውያን ምርኮኞችን የኢጣሊያን አገዛዝ “አሜን!” ብለው እንዲቀበሉ በተለያዩ ጥቅማ ጥቅም ይደልሏቸው ነበር:: ወይዘሮ ልክየለሽ በያን ግን በጠላት ጥቅማ ጥቅም ፈጽሞ ሊደለሉ አልቻሉም::
ጣሊያን ኢትዮጵያን ከተቆጣጠረ በኋላ ወይዘሮ ልክየለሽ በያን ሴቶችን በማሰባሰብና በማደራጀት ለውስጥ አርበኞች ስንቅ እንዲያዘጋጁ ያደርጉ ነበር:: ጥጥ በማስፈተል ልብስ አሠርተው ያለብሳሉ፤ በየዱር ገደሉ ቆስለው ለወደቁትም የሀገር በቀል የህክምና ዘዴን በመጠቀም እንዲታከሙና በምግብ እንዲያገግሙ ያደርጉ ነበር::

3. ወይዘሮ ልኬለሽ በያን የተሰጣቸው ሽልማት

Woyzero Likyelesh Beyan
አርበኛ ልክየለሽ በያን ከሴት
ልጃቸው ከበቀለች መኮንን ጋር
አርበኛዋ ከጠላት ጋር ፊት ለፊት ባደረጉት ተጋድሎና የኋላ ደጀን ሆነው ባደረጉት ያልተቋረጠ ከፍተኛ ድጋፍ፤ በ1942 ዓ.ም ከድል በኋላ ግርማዊ ቀዳማዊ ኃይለሥላሴ ለኢትዮጵያ አርበኞች ባከናወኑት የሽልማት ሥነ ስርዓት ላይ ወይዘሮ ልክየለሽ በያን በመገኘት በአርበኝነት ያደረጉት ተጋድሎና የከፈሉት መስዋእትነት እጅግ ከፍተኛ ስለነበር አምስት የተለያዩ የአርበኝነትና የጀግንነት ኒሻኖች ተሸልመዋቸዋል::

4. የወይዘሮ ልኬለሽ በያን ህልፈተ ሕይዎት

ቆራጧ የሴት አርበኛ ወይዘሮ ልክየለሽ በያን፤ ባደረባቸው ህመም ምክንያት በጥቅምት ወር 1964 ዓ.ም ከዚህ ዓለም በሞት ተለይተዋል:: የቀብር ስነስርአታቸውም በአዲስ አበባ በመንበረ ጸባዖት ቅድስት ሥላሴ ቤተ ክርስቲያን ከፍተኛ የመንግስት ባለስልጣናት በተገኙበት ተፈጽሟል::

5. የታሪኩ አጥኝ አስተያት

እንደ አጥኝው አስተያየት ለአሁኑ ትውልድ ተምሳሌት የሚሆኑ የሴት አርበኞች ታሪክ ጐልቶ እንዳልወጣ ይናገራሉ:: የወ/ሮ ልክየለሽን ታሪክ ለማጥናት የተነሳሱትም ያገኙት መረጃም ሌሎች ሰዎችን የሚያነሳሳና በተለይ አሁን ላለው ትውልድ ጥንካሬን የሚያጋራ በመሆኑ ነው ይላሉ::
ዳር ድንበርን ለማስከበር በተከፈለው መስዋእትነት ብዙዉን ጊዜ የወንዶች ሚና ጎልቶ ቢጻፍም ለስኬታማነቱ ከፊትና ከኋላ ሆነው በመዋጋትና ጦርነቱ በድል እንዲጠናቀቅ ምክንያት የሆኑ በርካታ ሴቶች እንደነበሩም አጥኝው ይናገራሉ:: ነገር ግን ታሪካቸው ትኩረት ተሰጥቶት እንዳልተጠና ይናገራሉ:: ::
ስለዚህ ትናንት የነበሩ ብርቱ ሴቶችን ታሪክ መሻት የአሁኑ ትውልድ ግዴታም እንደሆነ አጥኝው አስገንዝበዋል፡፡::






ምንጭ፤
  1. የካቲት 26 ቀን 2010 ዓ.ም ከተጻፈ ከአብይበኩር ጋዜጣ ዕትም የተወሰደ  ሊንክ
  2. ምስጋና፤ ለታሪኩ አቅራቢ፤ ለአቶ አለማየሁ እርቅይሁን (በ 2010 ዓ.ም በባህርዳር ዩኒቨርሲቲ የታሪክና የቅርስ ትምህርት ክፍል የሦስተኛ አመት የሦስተኛ ዲግሪ ተማሪ የነበሩትና የአርበኛዋን ታሪክ ያጠኑ)  የየካቲት 26 ቀን 2010 ዓ.ም የአብይበኩር ጋዜጣ ዕትም
  3. ምስጋና፤ ለአያሌው አስረስ  addisadmassnews
  4. የትረካው አጃቢ ሙዚቃ፣ ዋሽንት - በአንሙት ክንዴ   ዩቲውብ