Content-Language: am ቢትወደድ መንገሻ ጀንበሬ
header image




ቢትወደድ መንገሻ ጀንበሬ



የቢትወደድ መንገሻ ጀንበሬን
የአርበኝነት ዘመን ታሪክ ያዳምጡ














1. ትውልድና ዕድገት

Lij-Hailemariam Mamo
ቢትወደድ መንገሻ ጀንበሬ
ቢተወደድ መንገሻ ጀምበሬ ግንቦት 13 ቀን 1884 ዓ.ም በጎጃም ጠቅላይ ግዛት በሜጫ አውራጃ አጉንታ ተወለዱ። የቢተወደድ መንገሻ ጀምበሬ አባት ጀምበሬ እምሩ የሜጫ፣ የዴንሳ፣ አጉንታ፣ የአገው ምድር ባላባት በመሆን ለብዙ ዘመናት አካባቢውን አስተዳድረዋል፡፡
የቢተወደድ መንገሻ ጀምበሬ ቤተሰቦች ከአባታቸው እስከ ቅድመ አያቶቻቸው ድረስ ሁሉም የደጃዝማችነት ማዕረግ የነበራቸው ነበሩ።
ቢትወድድ መንገሻ፤ ብልህ ፣ አስተዋይ ፣ በልጅነት ዘመናቸው በአልሞ ተኳሽነታቸው ተወዳዳሪ የማይገኝላቸው ፣ በበገና ድርደራ እና በፈረስ ግልቢያ የሚታወቁ ነበሩ፡፡ ለአደንና ውኃ ዋናም ልዩ ፍቅር ያላቸው ትልቅ አርበኛ ነበሩ፡፡
የትውልድ ሐረጋቸዉ ከጐጃም የሚመዘዘዉ ራስ ቢትወደድ መንገሻ አቲከም፣ በሦስቱ ነገሥታት ማለትም፤ በአፄ ቴዎድሮስ፣ በአፄ ዮሀንስ እና በአፄ ምኒሊክ ዘመን ከነገሥታቱ ጋር አብረው ኖረዋል::
ቢተወደድ መንገሻ ጀምበሬ በተወለዱ በዘጠኝ ዓመታቸው አባታቸው ከዚህ ዓለም በሞት ሲለዩ ከአያታቸው ደጃዝማች እምሩ ቤት ኾነው የቤተ ክህነት ትምሕርት እየተከታተሉ አደጉ፡፡ ከዚያ በኋላም አያታቸው ደጃዝማች እምሩ ሲሞቱ ከአጎታቸው ከደጃአዝማች ሽፈራው እምሩ ጋር በመሆን የተለያዩ ወታደራዊ ስልጠናዎችን እየወሰዱ አደጉ፡፡ በእድገት ዘመናቸው ቢትወደድ መንገሻ ጀምበሬን ጀግንነት የተመለከቱት ደጃዝማች ሽፈራው እምሩ ከሚያሥተዳድሩት ግዛት በመቀነስ ቆላ አቦሌ የሚባለውን ግዛት እንዲያስተዳድሩ ሰጧቸው፡፡

2. የጉልምስና እድሜና ኃላፊነት መቀበል

ቢትወደድ መንገሻ ጀምበሬ በተወለዱ በ 32 ዓመታቸው የደጃዝማችነት ማዕረግ በማግኘታቸው የቡሬ ዳሞት አውራጃንና ሰከላ አካባቢዎችን ማሥተዳደር ጀመሩ፡፡ በመልካም ፀባያቸው ፣ በአስተዋይነታቸው እና ለሀገራቸው ባላቸው ልዩ ክብር ምሥጉን ሆኑ፡፡ በሚያሥተዳድሩት አካባቢ የፀጥታው ችግር የሌለበት ፣ በትንሹም በትልቁም የሚወደድ ባሕርይ እንዳላቸው በመታወቁ ሜጫን እንዲያሥተዳድሩ ትልቅ ኃላፊነት ተሰጧቸዋል፡፡ በወቅቱ እሳቸው በሚያሥተዳድሩት ግዛት ፍርድ የሚያጓድል፣ ድሃን የሚበድል፣ መንገደኛን የሚዘርፍና በአጠቃላይ ሕገ ወጥ ተግባር የሚፈጽም ሰው ሲኖር በፍጥነት ፍርድ በመስጠት የሚታወቁ ናቸው፡፡

3. የቢተወደድ መንገሻ ጀምበሬ የአርበኝነት ዘመን

Ras Bitewoded-Mengesha Atikum High School
በ 1928 ዓ.ም የፋሺስት ኢጣሊያን ወራሪ ጦር በመጣ ጊዜ በግዛታቸው ማለትም በሜጫ አውራጃ አካባቢ የሚገኘውን ጦር አስከትለው ከራስ እምሩ ጋር በመሆን በትግራይ በኩል ዘምተው ለእናት ሀገር የሚከፈለውን መስዋትእነት ከፍለዋል፡፡
በወቅቱ በነበረው ጦርነት አርበኞች ከፍተኛ ጀብዱ ቢፈጽሙም ቅሉ መርዛማ ጋዝ በሚያዘንቡ አውሮፕላኖች የሚታገዘው የኢጣሊያ ጦር ድል ሆነ፡፡ የኢትዮጵያ አርበኞችም ትግራይን ለቀው ወደ ኋላ በማፈግፈግና እንደገና በየአካባቢው የሚገኘውን የጎበዝ አለቃ እያስተባበሩ የደፈጣ ውጊያ በማድርግ የጠላትን ጦር በመፋለም ድል የተቀዳጁ አርበኛ ነበሩ፡፡
ከትግራዩ ጦርነት በተጨማሪ የጎጃም አርበኞች የጣሊያን ወራሪዎችን በአራት አቅጣጫ ተከፋፈለው ሲፋለሙ ቢትወደድ መንገሻ ጀምበሬ በአገው ምድር፣ በሠከላ፣ በሜጫ፣ በጉታ፣ በአቸፈርና፣ በአለፋ ጣቁሳ የነበረውን የፋሽት ጦር በአርበኝት ተፋልመዋል።
ቢተወደድ መንገሻ ጀምበሬ ከደጃዝማች በላይ ዘለቀና ከሌሎች የውስጥ አርበኞች ጋር በመሆን የጋራ ጠላትን የተዋጉና በሀገር ጉዳይ እጅግ ከፍተኛ መናበብ ነበራቸው። በዚህም መሠረት፤ ደጃዝማች በላይ ዘለቀና ወንድሞቹ ብቸናን ፣ ራስ ኃይሉ በለው ደብረ ማርቆስንና ሞጣን፣ እንዲሁም ራስ በዛብህ ዳሞት አካባቢን በማካለል በደፈጣ ውጊያ የጠላት ጦርን እረፍት ይነሱት ነበር፡፡ እኝህ ተዋቂ የአርበኞች መሪዎች በውጊያ ወቅትም አርስ በርስ መረጃ ይለዋወጡ እንደነበረም ስለ እሳቸው የተጻፈ መረጃ ያመላክታል፡፡
በጀግንነታቸው ጠላት እጅግ የሚፈራቸው ቢትወደድ መንገሻ ጀምበሬ፤ በአንድ ወቅት በባሕር ዳር አካባቢ በወራሪው ጠላት ተማርከው በነበረበት ወቅት ድነቅ ዘዴዎችን በመጠቀም ከጠላት መንጋጋ ፈልቅቀው መውጣታቸውን ታሪካቸው ያስረዳል፡፡
በ 1929 ዓ.ም ኮርቦ የተሰኘው ጣሊያናዊው ካፒቴን ባህርዳርን ያስተዳድር በነበረበት ወቅት፤
  1. ቢተወደድ መንገሻ ጀምበሬን
  2. ደጃዝማች ስብሀቱ ይግዛው፣ የይልማና ዴንሳ ጦር አዝማች
  3. ፊታዉራሪ መኮነን ዋሴና
ሌሎችንም አርበኞች ወደ ባህርዳር ካስጠራ በኋላ ፣ ሌሎችን ለቆ ቢተወደድ መንገሻ ጀምበሬን ግን እዚያዉ ባህርዳር ከተማ ውስጥ የቁም እስረኛ አድርጎ አስቀመጣቸው።
የመንገሻ ጀምበሬን በጠላት መታሰር የሰማው የሰከላ፣ የፋግታ፣ የሜጫ፣ የአገዉ ምድርና የአቸፈር ህዝብ በደብቅ ተሰባስበው የፋሽስት ኢጣሊያን ጦር ለማጥቃት መመካከር ጀመሩ።
በመጨረሻም የተሰበሰበው ሕዝብ ቢተወደድ መንገሻ ጀምበሬን የጦር መሪው አድርጎ ለመዋጋት ከወሰኑ በኋላ ከመካከላቸው ሽማግሌዎችን መርጠው መንገሻ ጀምበሬን እንዲያነጋግሩ ተደረገ። ቢተወደድ መንገሻ ጀምበሬም በሀሳቡ ከተስማሙ በኋላ ጣሊያናዊው ካፒቴን ኮርቦን “ስላመመኝ ሄጀ ፀበል እንድጠመቅ ፍቀድልኝ” በማለት ካነጋገሩት በኋላ በዋስ ተለቀው ወደ ሀገራቸው ተመለሱ።
ከዚያም ውስጥ ለውስጥ በድብቅ ጦራቸውን ካደራጁ በኋላ በግልፅ ሽፍትነታቸውን ጀምረው የጠላት ጦርን መግቢያ መውጫ ያሳጡት ጀመር።

4. ቢተወደድ መንገሻ ጀምበሬ ከድል በኋላ

Ras Bitewoded-Mengesha Atikum High School
በዳንግላ ከተማ የሚገኘውን በቢተወደድ መንገሻ
ጀንበሬ ስም የተሰየመውን
ት/ቤት የቀድሞ ተማሪዎች ሲጎበኙ
 Photo Link
ኢትዮጵያ በ 1933 ዓ.ም. ድል ከተቀዳጀች በኋላ በንጉሠ ነገሥት ግርማዊ ቀዳማዊ ሀይለ ሥላሴ ጥሪ ተደርጎላቸው ወደ ዐዲሰ አበባ ከሄዱ በኋላ የቢትወደድነት ማዕረግ ተሰጣቸው።
የቢትወደድነት ማዕረግ ከተሰጣቸው በኋላ የጎጃም ጠቅላይ ግዛት እንደራሴ ሆነው ጥቂት ጊዚያት ካስተዳደሩ በኋላ ወደ አዲስአበባ ተዛውረው የህግ መወሰኛ ምክርቤት ሰብሳቢ ሆነው ተሸሙ። ከዚያም በኋላ የወለጋ ጠቅላይ ግዛት አስተዳዳሪ ሆነው በመስራት ላይ እያሉ ባደረባቸው ህመም ምክንያት በ 1942 ዓ.ም. በተወለዱ በ 58 ዓመታቸው ከዚህ ዓለም በሞት ተለይተዋል።
ቢትወደድ መንገሻ ጀምበሬ በተለያዩ ኃላፊነቶች አገራቸውን ያገለገሉ ሲሆን የአርበኝነት ውለታቸውን ለመዘከርም በዳንግላ ከተማ አንድ ሁለተኛ ደረጃ እና አንድ የመጀመሪያ ደረጃ ትምህርት ቤቶች በስማቸው ተሰይመውላቸዋል።








ምንጭ፤
  1. "የታሪክ ማስታወሻ - 19262 ዓ.ም." ደራሲ፤ ደጃዝማች ከበደ ተሰማ
  2. ከበይነመረብ መጣጥፍ የተወሰደ   ethiopanorama
  3. የትረካው አጃቢ ሙዚቃ፣ ዋሽንት - በአንሙት ክንዴ   ዩቲውብ