የራስ አበበ አረጋይ አይበገሬነት ፈተና የሆነበት ፋሽስት ኢጣሊያ ለራስ አበበ አረጋይ የእርቅ ድርድር ማቅረብ ጀመረ፡፡
በዚህም መሠረት በራስ ኃይሉ ተክለ ሐይማኖት በኩል የእርቅ ድርድሩ እንዲደረግ ቀደም ብለው ሞክረው ነበር፡፡
ባቀረቡላቸውም የዕርቅ ደብዳቤ፤ ጣሊያኖች ለራስ አበበ አረጋይ ደመወዝ ቆርጦ፣ ያላቸውን ንብረት ሁሉ አስጠብቆ ሊያኖራቸው
መወሰኑን ገለፁላቸው፡፡
ራስ አበበ ከጠላት ጋር በሚያደርጉት ድርድር ጠላትን ግራ በማጋባት ምንም ሊጨበጡለት አልቻሉም፡፡
በኋላም ጣሊያኖች ሌላ አካባቢ የሚገኙትን አርበኞችን በመግደላቸው ድርድሩ መቅረቱን ራስ አበበ ቢያስረዷቸውም ቅሉ እነርሱ ግን በአርበኞች ዘንድ ዝነኛ አርበኛ ወደ እነርሱ አሳምኖ ለማስገባት ጓጉተው ስለነበረ ጥረታቸውን ሳያቋርጡ ቀጠሉበት፡፡
በሌላ ጊዜ ደግሞ ጣሊያናዊው የደብረ ብርሃን አገረ ገዥ የሆነው ኮሎኔል ማሊቲ ለራስ አበበ አረጋይ የላከው የጽሁፍ መልዕክት፤
“---ባለቤትህና ልጅህ በክብር ተቀምጠዋል፡፡ ለሀገሬ እንዳትል አስካሁን የደከምከው የሚያኮራህና በቂም ነው፡፡
ምንም ትርፍ ላታገኝበት ለሸዋ ብለህ አትድከም፡፡
ይልቅስ ምክሬን ተቀብለህ ወደእኛ ብትገባ ይሻለሀል፡፡”
የሚል ነበር፡፡
ራስ አበበ አረጋይም ለተላከላቸው መልዕት ምላሹን ሲሰጡ፤
“...የባለቤቴና የልጄ በደህና መያዝ ከተቀደሰ ተግባሬ የሚያስተጓጉለኝ አይሆንም፡፡
እኔም ሆንኩ ሌሎቹ የኢትዮጰያ አርበኞች ከናንተ ጋር የምንታገለው ለውድ ሀገራችን ነፃነትና ክብር፤ እንዲሁም ለሕዝቧ ደህንነት መሆኑን እወቀው፡፡
ማንኛውም ኢትዮጵያዊ በኢጣሊያ ፋሽስት ኮቴ ሲረገጥ እንደማይኖር አረጋግጥልሀለሁ፡፡”
የሚል ቁርጥ ያለ መልስ ላኩለት፡፡
በደብረ ብርሃን እስር ቤት ምንም ህክምና ሳያገኝ ይሰቃይ የነበረው የራስ አበበ አረጋይ ልጅ ዳንኤል አበበም በኢጣሊያ አለቆች አማካይነት ወደ አዲስ አበባ ተወስዶ ሕክምና ከተደረገለት በኋላ ወደ ትምህረት ቤት ገብቶ እንዲማር ተደርጎ ነበር፡፡
ነገር ግን ራስ አበበ አረጋይ ለኢጣሊያ አልገባም በማለታቸው የተበሳጩት የኢጣሊያ ሹማምንቶች፤ ዳንኤልን ከትምህርት ቤቱ አቋርጠው አባቱን እንዲያሳምን ወደ አባቱ ላኩት፡፡
ዳንኤል፤ የአባቱ አቋም ምንም የማይለወጥ መሆኑን ሲረዳ እዚያው ቀርቶ ከአባቱ ጋር ሆኖ መታገሉን መረጠ፡፡
የኢጣሊያ ጦር አዛዥ ጀነራል ሲሮ ናሲ ከራስ አበበ አረጋይ ጋር እንደገና አዲስ ድርድር ለማድረግ፤ ወሰነ፡፡
በዚህም የድርደር መንፈስ መሠረት፤ አርበኞችን ለማግባባት ሲባል የኢጣሊያ ጦር በተጉለት፣ በቡልጋና ከአካባቢው ካሉት ምሽጎች እንዲነሳ ጀነራል ሲሮ ናሲ አዘዘ፡፡
በዚህም መሠረት አርበኞቹ እምሽጉ ድረስ መሄድ ስለቻሉ፤ የውስጥ አርበኞች በድብቅ ብዙ ጥይትና ቦምብ ሊሰጧቸው ቻሉ፡፡
ራስ አበበ የኢጣሊያ መልዕክተኞችን የሚቀበሉት ካሉበት ስፍራ ሆነው የኢትዮጵያን ሠንደቅ ዓላማ ከፍ አድርገው ሰቅለው በማውለብለብ ሲሆን፤ ጣሊያኖች ግን አርበኞች ጦር ሠፈር ድረስ ለመድረስ ሰባት የፍተሻ ኬላወችን ማለፍ ይጠበቅባቸው ነበር፡፡
የደብረ ብርሃን አገረ ገዥ የሆነው የኢጣሊያ ኮሎኔል ማሊቲ ግን፤ ከራስ አበበ አረጋይ ጋር ለመገናኘት ያን ሁሉ የፍተሻ ጣቢያ ተፈትሾ ማለፍ ነበረበት፡፡
የእርቁ ድርደር ቀጥሎ ሳለ በኢትዮጵያ የኢጣሊያ ንጉስ እንደራሴ የሆነው ባለሥልጣን ለጉብኝት ወደ ሰሜን ሸዋ ሸኖ ሄዶ በነበረበት ወቅት፤ የራስ አበበ ባለቤት ምርኮኛዋ ወይዘሮ ቆንጅት አብነት በእስር ላይ መሆናቸውን አወቀ፡፡
ወደ እርሳቸውም ቀርቦ፤
“አንችን ያየሁባትን የዛሬን ቀን በጣም አከብራታለሁ፡፡ ለመሆኑ ምን እንዳደርግልሽ ትፈልጊያለሽ” ብሎ ሲጠይቃቸው ከእስር እንዲያስፈታቸው ጠየቁት፡፡
ባለሥልጣኑም ጥያቄአቸውን ተቀብሎ
“ከአሁን ጀምሮ ነፃ ናት ወደ ፈለገችበት መሄድ ትችላለች፡፡ ብቸኛ ሴት ናት፡፡ ምን ልታደርገን ትችላለች፡፡” በማለት ከእስር ቤት እንዲወጡ ፈቀደላቸው፡፡
ወይዘሮ ቆንጅት ከሰባት ወራት የእስር ቆይታ በኋላ አዲስ አበባ መግባት ቻሉ፡፡
አዲስ አበባም እንደደረሱ በመጀመሪያ የባለቤታቸው አክስት ከሆኑት ከወይዘሮ አዛለች ጎበና ቤት ካረፉ በኋላ በእንጦጦ ኪዳነ ምሕረት እና በመጨረሻም በቀጨኔ መድሐኔዓለም አካባቢ ቆይተዋል፡፡
ከዚያም በኋላ በታህሳስ ወር 1932 ዓ.ም. ባለቤታቸው ወደሚገኙበት ሥፍራ ሄደው ከባለቤታቸው ጋር ለመገናኘት ቻሉ፡፡
በእርቁ ድርድር ሳቢያ ባለቤታቸው ከእስር መፈታታቸው፤ በአርበኞች ዘንድ ራስ አበበ አረጋይ ከጠላት ጋር እርቅ እንደፈፀሙ ተደርጎ በመወሰዱ ይህን ጥርጣሬ ለማሶገድ ራስ አበበ ለአርበኞች መሪወች በጻፉት ደብዳቤ፤
“ያደረኩት እርቅ ፍጹም ዕርቅ መስሏችሁ እንዳትታለሉ፡፡
አበበ ለጠላት ሊገባ ነው ብላችሁ የምታስቡ ብትኖሩ በእግዚአብሔር ስም እምልላችኋለሁ፡፡
የእኔ ሀሳብ በጦር ሜዳ የቆሰሉትን ቁስላቸው እስኪሽር፣ በበሽታ የተጎዱት አርበኞች እንዲያገግሙ፣ የታረዙት ልብስ እንዲያገኙና በቆላውና በደጋው ሲንከራተቱ የተጎዱት ከብቶቻችን እንዲያገግሙ ነው ድርድሩን የጀመርኩት፡፡” በማለት ለአርበኞች መልዕክት ላኩ፡፡
በዚህም መካከል በእርቅ ድርድሩ ምክንያት በተፈጠረው የተረጋጋ ሁኔታ የተወሰኑት የጅሩ የአርበኞች መሪዎች ከራስ አበበ ጋር ለመመካከር ሲጓዙ በጠላት ምሽግ በኩል ሲያልፉ በምሽጉ የሚገኘው የኢጣሊያ ጦር ኃላፊ ነገ እሸኛችኋለሁ ብሎ በሰላም የሚያስተናግድ መስሎ ወስዶ የጦር መሣሪያቸውን ተቀብሎ ካሳደራቸው በኋላ ከአለቃው ጋር ተነጋግሮ የያዛቸውን አርበኞች በሞት እንዲቀጡ አደረገ፡፡
የህን ዘግናኝ ወሬ የሰሙት ራስ አበበ፤ በአካባቢው የሚገኙትን አርበኞች ጥር 21 ቀን 1932 ዓ.ም. ሰብስበው ከተመካከሩ በኋላ አርበኞችን አታሎ በሞት እንዲቀጡ ያደረገው የኢጣሊያ ጦር ኃላፊ ለእነርሱ ተላልፎ እንዲሰጥ ጥያቄ እንዲቀርብ ተወሰነ፡፡
በዚህም መሠረት በአርበኞች አሟሟት ውሳኔ ለመስጠትና የእርቁንም ድርድር ፍጻሜ ለማድረስ የካቲት 30 ቀን 1932 ዓ.ም. ጀነራል ናሲ አርበኞቹ ድረስ እንደሚመጣ ራስ አበበ ለአርበኞቹ አስረዱ፡፡
በዚህን ጊዜ ጀነራሉ ከሚመጣበት ከሁለት ቀን በፊት ሰምምነት ተደርጎ ጀነራሉ በሚመጣበት ዕለት በደፈጣ ውጊያ እርምጃ እንዲወሰድበት ሰምምነት ላይ ተደረሰ፡፡
ይሁን እንጅ ጀነራል ናሲ ሀሳቡን ቀይሮ ሌሎችን ተወካዮችን ልኮ ዕርቃችን የፀና ይሁን የሚል መልዕክት በመላኩ የታቀደው ሁሉ ሳይሳካ ስለቀረ በዚህ የተበሳጩት ራስ አበበ፤ አርበኞቹን በግፍ በመግደላችሁ ዕርቁን ለመቀጠል ሌላ ቀጠሮ አልሰጥም፤ እርቁ እንዳይፈረስ ከፈለክ ወንጀለኞቹን አሳልፈህ ስጠኝ በማለት የተፈፀመውን የአርበኞች ግድያ ለእርቁ ማፍረሻ አድርገው በማቅረብ ቁርጥ ያለ መልስ ላኩለት፡፡
ይሁን እንጅ ጣሊያኖች የአበበ አረጋይን ሀሳብ ስላልተቀበሉት የዕርቅ ድርድሩ ፈርሶ ሁኔታዎች ሁሉ ወደቀድሞ ቦታቸው በመመለሳቸው አርበኞች እንደገና ተወያይተው ጠላትን በተለያዬ አቅጣጫ ተሰማርተው ለመውጋት በመስማማት የቀድሞ የአርበኝነት ተግባራቸውን ቀጠሉ፡፡
ንጉሠ ነገሥቱ ከስደት በመመለስ ከሱዳን ተነስተው ጎጃም ከሰነበቱ በኋላ በፍቼ በኩል አድርገው ወደ አዲስ አበባ ለመምጣት ሚያዝያ 22 ቀን 1933 ዓ.ም. ፍቼ ሲገቡ፤ ራስ አበበ አረጋይ ፍቼ ድረስ በመሄድ በሰልፍ ተቀበሏቸው፡፡
ራስ አበበ ከልጃቸው ከዳንኤል አበበ ጋር ሆነው ንጉሠ ነገሠቱ ጋ በመቅረብ ለጥ ብለው እጅ ከነሱ በኋላ፤
“እኔ የእርስዎ ታማኝ አሽከርዎ ለጠላት ሳልገዛ ቆይቻለሁ፡፡ ዳግመኛ በሕይወት አገኝዎታለሁ ብዬ ተስፋ አላደረኩም ነበር፡፡ እናም ፀሐይ ወጥታለን ለዚህ ቀን ስላደረሰን እግዚአብሔርን አመሰግናለሁ።”
በማለት ንግግር አሰምተዋል፡፡
ጉዞውም ከፍቼ ወደ አዲስ አበባ ቀጥሎ ሚያዝያ 27 ቀን 1933 ዓ.ም. ጧት ንጉሠ ነገሥቱ እጦጦ ማርያም ቤተ ክርስቲያን በር ላይ ሲደርሱ ስመ ጥሩው ጀግና ክቡር ራስ አበበ አረጋይ ቁጥራቸው 10 ሺህ የሚደርስ አርበኞቻቸውን አሰልፈው እጅግ የደመቀና የጋለ አቀባበል አደረጉላቸው፡፡
ንጉሠ ነገሥቱ ከእንጦጦ ማርያም ተነስተው በግልጽ አውቶሞቢል ላይ ሆነው በነጭ ፈረስ ላይ በተቀመጠው በእንግሊዛዊው ኮሎኔል ዊንጌት፤ በጌድዮን ጦር እና በአርበኞች ታጅበው ወደ አዲስ አበባ ጉዞ ለመቀጠል ተዘጋጁ፡፡
በዚህን ጊዜ በእንግሊዛዊው ጀነራል ካኒንገሃም አማካይነት በሞተር ብስክሌቶችና በቀላል ታንኮች ላይ በመሆንና፤ በተጨማሪም ንጉሠ ነገሥቱን የሚያጅቡ ከደቡብ አፍሪካ የመጡ ወታደሮችና የፖሊስ ሠራዊት ፈረሰኞች ወደ እንጦጦ ተልከው ንጉሠ ነገሥቱን እንዲያጅቡ ከተደረገ በኋላ ንጉሠ ነገሥቱ በደማቅ ንጉሣዊ ክብር ታጅበው ወደ አዲስ አበባ ለመጓዝ ዝግጅቱ ተጠናቀቀ፡፡
የጉዞውም ዝግጅት እንደተጠናቀቀም ከጀነራል ካኒንግሃም አንድ መልዕክት ለራስ አበበ አረጋይ ደረሰ፡፡
መልእክቱም፤ ቁጥራቸው 10 ሺህ የሚደርሰው የራስ አበበ አረጋይ የአርበኞች ጦር ንጉሠ ነገሥቱን አጅቦ ከሚሄድ ይልቅ እንጦጦ ላይ ሠፍረው ለ48 ሰዓት እንዲቆይ የሚል ነበር፡፡
ይህም የካኒንገሃም ሀሳብ ለራስ አበበ አረጋይ ተተርጉሞ ሲነገራቸው፤
“አልቀበልም! ንጉሠ ነገሥታችን በአገራችን በኢትዮጵያ ላይ የፋሽስት መንግሥት የሚፈጽመውን ግፍ ለዓለም መንግሥታት ማህበር ለማመልከት ወደ አውሮፓ ሲሄዱ፤ እኛም አዲስ አበባን ለቀን በየጫካውና በየገደሉ በመሰማራት ከጠላታችን ጋራ ለነፃነታችን ስንዋጋ አምስቱን ዓመታት አሳልፈናል፡፡
ዛሬ የእግዚአብሔር ፈቃድ ሆኖ የወዳጅ አገር የእንግሊዝ መንግሥት እርዳታ ተጨምሮበት ንጉሠ ነገሥታችን የነፃነታችንን ችቦ እያበሩ ወደ መናገሻ ከተማቸው ሲያመሩ እኛ ተነጥለን እዚህ እንጦጦ እንድንቆይ የምንጠየቀውን አልቀበልም፡፡
አሁን የቆምነው ነፃ በሆነችው አገራችን መሬት ላይ ነው፡፡ ዛሬም ለመጓዝ የተዘጋጀነው ነፃ ወደሆነችው ወደ አዲስ አበባ ከተማችን ነው፡፡
ምናልባት የአዲስ አበባ ፀጥታ አስግቷችሁ እንደሆነ እኛ በቂ የሆነ ኃይል ሰላለን በቶሎ ደርሰን እንጋፈጥላችኋለን፡፡
ከዚህ ሌላ ባታስቸግሩን ይሻላል፡፡ እኛ ውለታችሁን ማሰብ፤ እናንተም ምስጋናችንን መቀበል የሚገባ ነው፡፡
ከዚህ ውጭ የምንጠይቃችሁ ነገር የለም፡፡”
የሚል መልስ ሰጡ፡፡
ዊንጌትም በራስ አበበ መልስ ተማረከ፡፡ ወዲያውኑም ዊንጌት ለካኒንግሃም ባስተላለፈው ቃል፤
የታወቀው የአርበኞች መሪ አበበ አረጋይ፤ ከጃንሆይ ተለይተን እንጦጦ ለመቆየት ጨርሶ የማይታሰብ ነው ብሏል፡፡
የንጉሠ ነገሥቱም አቋም ይህንኑ የመሠለ ስለሆነ ሀሳቡን ከመቀበል በስተቀር ምርጫ የለንም፡፡
ሲል አስታወቀ፡፡
ካኒንጋሃምም ሌላ ታሪክ መፍጠር ስላልፈለገ በጉዞው ፕሮግራም መሠረት፤ ንጉሠ ነገሥቱ ሚያዝያ 27 ቀን 1933 ዓ.ም. ከቀኑ 6 ሰዓት ላይ እጅግ በደመቀ ሁኔታ ታጅበው ከታላቁ ቤተ መንግሥት ደረሱ፡፡