Content-Language: am
ፊታውራሪ አየለ ተሰማ አባጓዴ
ወደ ላይኛው ገጽ ይሂዱ
ቤተ ድረ ገጽ ▼
የታሪክ ማስታዎሻዎች ▼
አፄ ቴዎድሮስ
አፄ ዮሐንስ 4ኛ
ዳግማዊ ምኒልክ
ንግሥት ጣይቱ
ንግሥት ዘዉዲቱ
ልጅ እያሱ
ቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ
ፊታውራሪ አየለ ተሰማ አባጓዴ ▼
አርበኞች ገጽ አንድ
አርበኞች ገጽ ሁለት
ጥያቄና መልስ ▼
ጥያቄና መልስ ገጽ አንድ
ጥያቄና መልስ ገጽ ሁለት
ስለ ድረ ገጽ አዘጋጁ
ፊታውራሪ አየለ ተሰማ አባጓዴ
የፊታውራሪ አየለ ተሰማ አባጓዴን የሕይዎትና የአርበኝነት ዘመን ትረካን ያዳምጡ
Your browser does not support the audio element.
የአርዕስት ማውጫ
1. የወጣትነት ዘመን
2. የጎንደር በጠላት መወረር
3. የበዛሆ ምሽግ
4. በጠላት ላይ ያደረሱት ጥቃት
5. የዳዛ እና የደንቢያ ጀብዱ
6.ተከታታይ የአርበኝነት ተጋድሎ
7. ከነፃነት በኋላ የሕይዎት ዘመን
1. የወጣትነት ዘመን
ፊታውራሪ አየለ ተሰማ
አየለ ተሰማ ከአባታቸው ከአቶ ተሰማ አስረስ እና ከእናታቸው ከወይዘሮ አሰለፈች ወንዴ በ 1879 ዓም. በሰሜን ጎንደር በጭልጋ አውራጃ ውስጥ በተለይም ዳዛ ተብሎ በሚጠራው መንደር ተወለዱ ፡፡ አየለ ሦስት ወንድሞችና አምስት እህቶች ሲኖሩዋቸው እርሳቸው የሁሉም ታናሽ ናቸው፡፡ ከነሱ መካከል በእድሜ ትልቁ ረዳ ይባላሉ፡፡ የአየለ አባት ቀኛዝማች ተሰማ፤ ለልጃቸው ለአየለ ትልቅ ምኞትና ክብር ስለነበራቸውና እኔን የሚተካኝ እርሱ ነው ብለው ይመኙ ስለነበረ ልጃቸውን ቀኛዝማች አየለን “አየለ ክብሬ” በማለት ይጠሯቸው ነበር፡፡ አየለ፤ በልጅነታቸው ከቤተሰቡ አባላት እና ከአከባቢው ጓደኞቻቸው ጋር በመሆን ስለ እርሻና ስለ ከብት እርባታ ዘዴ ተምረዋል፡፡ በተጨማሪም፤ ከወንድሞቻቸው ልጆች አማረ ጣሰው እና አበራ ረዳ ጋር በመሆን በዳዛ አቅራቢያ በሚገኘው በጫቆ ቅዱስ ጊዮርጊስ እና በሚካኤል አብያተ ክርስቲያናት ውስጥ በሃይማኖት መምህሮቻቸው በመሪጌታ እንቁነህ እና በአባ እዝራ የቤተክርስቲያን ትምህርታቸውን ተከታትለዋል ፡፡ አየለ ተሰማ በቤተክርስቲያን ውስጥ በሚማሩበት ጊዜ በድቁናም ያገለግሉ ነበር ፡፡ ከዚህ በተጨማሪ በ12 እና በ18 ዓመት እድሜ መካከል እያሉ፤ እንደ ‹ሲናደር› ፣ ‹ሞስኮቭ› እና ‹ውጅግራ› ያሉ የአባታቸውን ጠበንጃዎች ተሸክመው ከአባታቸው ጋር ይጓዙ ነበር፡፡ በዚህ ጊዜ አየለ ተሰማ የያዟቸውን ጠመንጃዎች አጠቃቀማቸውን በመለማመዱ ጫካ ውስጥ ወፍና የዱር እንስሳትን በማደን የተኩስ ልምምድ ማድረግ ጀመሩ፡፡ አየለ በግብርና ሥራ እምብዛም አልተሳተፉም ፡፡ አየለ እድሜያቸው 18 ዓመት ሲሞላቸው ዳዛ ውስጥ አደባባይ ወንዴ የተባለች ቆንጆ ወጣት ልጅ አግብተው ስህን የተባለች የመጀመሪያ ሴት ልጃቸውን ወለዱ፡፡
2. የጎንደር በጠላት መወረር
ቀኛዝማች አየለ በሽፍትነት ሕይዎት ውስጥ እያሉ፤ የፋሽስት ኢጣሊያ ወራሪ ኃይል ጎንደርን በወረረ በአምስተኛው ቀን መጋቢት 29 ቀን 1928 ዓ.ም. ደግሞ አይከልን ተቆጣጠሩ፡፡ አይከል በጠላት ከመያዟ አስቀድሞ የአይከል ገዥ የነበሩት የጦሩ አዛዡ ፊታውራሪ አለማየሁ ባይተዋ ነበሩ ፡፡ ከፋሽስት ኢጣሊያ ወረራ በኋላም የበጌምድር ገዥው ፋሺስቱ ጀነራል ናዚ ነበር፡፡ ጀነራል ናዚም በበኩሉ ሻለቃ ቲሊንቲን የጭልጋ ገዥ አድሮ ሲሾም፣ ሻለቃ መርሳን ደግሞ የጭልጋ ምክትል ገዥ አድርጎ ሾማቸው፡፡ በአጠቃላይ ጎንደር እና በተለይም የጭልጋ አውራጃ በኢጣልያ እጅ መውደቅን ተከትሎ የፋሽስት ኢጣሊያ ባለሥልጣናት፤ በአካባቢው የሚገኙት የኢጣሊያ ሰላይ የሆኑት ባንዳዎች የሚሰጡትን መረጃ በመጠቀም፤ አርበኞቹ እጃቸውን ከሰጡ እና በሠላማዊ መንገድ ከገቡ የገንዘብ እና ቁሳዊ ሽልማቶችን እንደሚያገኙ በመደለል በአከባቢው የተፈጠረውን ፀረ ፋሽስት ትግል ለማዳከም ጥረት አድርጓል፡፡
3. የእነቀኛዝማች አየለ የበዛሆ ምሽግ
በጥር ወር 1929 ዓ.ም. አካባቢ ፊታውራሪ አየለ እና የአጎታቸው ልጅ አበራ፤ እጃቸውን ለጠላት ላለመስጠት እና ከጠላት ጋር ተባባሪ ሆነው ላለመስራት ቆርጠው ተነሱ ፡፡ አየለ እና አበራ ከተከታይ አርበኞቻው ጋር ጥልቅ ውይይት ካደረጉ በኋላ በአይከል ከሚገኘው የኢጣሊያ ዋና ወታደራዊ ካምፕ ብዙም ሳይርቅ በ10 ኪሎ ሜትር ርቀት በሚገኘው በዛሆ ተብሎ በሚጠራ መንደር አቅራቢያ አንድ ወታደራዊ ስትራቴጂካዊ ስፍራ ላይ የራሳቸውን የመጀመሪያ ምሽግ ሠሩ፡፡ ምሽጋቸውን የሰሩበት ስፍራ የመሬት አቀማመጥ ተራራማ እና ድንጋያማ በመሆኑ ጠላትን ለመከላከል ምቹ ስፍራ ነበር፡፡ በአካባቢው የሚገኙት መላው አርበኞች በፊታውራሪ አየለ እና በአበራ የአመራር ኃላፊነት ስር ሲሆን የአርበኞቹ መሪዎች ፊታውራሪ አየለ እና አበራ ሁለቱም ከታጠቋቸው ሁለት ሽጉጦች ከጥቂት ጥይቶች በስተቀር ሌላ የታጠቁት የጦር መሣሪያ አልነበራቸውም፡፡ ፋሽስት ኢጣሊያ በጫቆ እና ዳዛ የሚገኙ የአርበኞች ቡድን በእነሱ ላይ ጥቃት ለመሰንዘር መዘጋጀቱን ከጥቂት ቀናት በኋላ የኢጣሊያ መኮንኖች ደረሱበት። እንደአጋጣሚ ሆኖ የፊታውራሪ አየለ እና አበራ አርበኞች ጉባጊ ከተባለው ስፍራ ላይ በደፈጣ ውጊያ በጠላት ጦር ላይ ያልተጠበቀ ድል አስመዘገቡ፡፡ በዚህ የደፈጣ ውጊያ ላይ አርበኞቹ 15 ጠመንጃዎችና 5 በቅሎዎችን ማርከዋል። የፊታውራሪ አየለ እና የአበራ የመጀመሪያ ወታደራዊ ድል ዜና ከተሰማ በኋላ ሌሎች የአካባቢው አርበኞች፤ ማለትም እንደነ አቶ መኮንን ዘገየ ፣ አቶ ገላጋይ ቸኮል ፣ አቶ ካሳሁን ተፈራ ፣ አቶ መልካሙ ቸኮል እና አቶ ነጋሽ ጀምበሬ የመሳሰሉት ተቀላቀሏቸው።
4. በጠላት ካምፕ ላይ ያደረሱት ጥቃት
ከበዛሆ ጦርነት በኋላ የፊታውራሪ አየለ እና የአበራ ተዋጊ አርበኞች፤ ጠላትን የሚሰልሉ የውስጥ አርበኞች የሰጧቸውን መረጃዎች በመጠቀም ሌላ ድንገተኛ ጥቃት ለመሰንዘር ከነበሩበት ቦታ ለቀው ወደ መተማ ተንቀሳቀሱ፡፡ እንደ አጋጣሚ ሆኖ የአቶ አየለ ወንድም የሆነው አቶ ታደሰ ተሰማ ጠላትን ከሚሰልሉ የውስጥ አርበኞች መካከል አንዱ ስለነበረ እጅግ ጠቃሚ መረጃዎች ለወንድሙ ያቀብለው ነበር፡፡ በመጨረሻም የፊታውራሪ አየለ እና የአበራ ተዋጊ አርበኞች በምሽት በጠላት ካምፕ ላይ በከፈቱት ውጊያ 3 የኢጣሊያ የጥበቃ ወታደሮችንና በርካታ ቁጥር ያላቸው የኢጣሊያ መኮንኖችን አቁስለዋል፡፡ በዚህ ውጊያ ላይ እንደ አጋጣሚ ሆኖ ፊታውራሪ አየለ ከታች እግራቸው ላይ ቆስለው ወደ መኖሪያ መንደራቸው ወደ ዳዛ በቃሬዛ ተወሰዱ፡፡ ይህ የደረሰው ጉዳት ያበሳጫቸው የኢጣሊያ ወታደሮች በአካባቢው የታወቀውን አቶ ዘውዴ የተባለው ሰው ካሰሩት በኋላ ለፍርድ አቅርበው በሞት እንዲቀጣ ወሰኑበት፡፡ የኢጣሊያ ወታደሮች ጉዳቱን ያደረሱት እንማን እንደሆኑ ካወቁ በኋላ፤ የፊታውራሪ አየለ ወንድም የሆነውን የውስጥ አርበኛ አቶ ታደሰ፤ ወንድማቸውን ፊታውራሪ አየለን በማባበል እጃቸውን እንዲሰጡ እንዲያደርግ ቢያስገድዱትም እርሱ ግን ለመተባበር ፈቃደኛ ባለመሆኑ ታሰረ፡፡ በመጨረሻ የኢጣሊያ መኮንኖች በሌሎች የአከባቢው ባንዳዎች በመጠቀም የፊታውራሪ አየለን አባትና ወንድማቸውን አቶ ረዳን ከአቶ ታደሰ ጋር አይከል በሚገኘው የጣሊያኖች እስር ቤት ካሰሯቸው በኋላ በአካባቢው ተወላጆች ተቃውሞ እንዳይነሳባቸው በማሰብ ጎንደር ወዳአለው ዋናው እስር ቤት አዛወሯቸው፡፡ ከጥቂት ጊዚያት በኋላ ፊታውራሪ አየለ ከጉዳት ካገገሙ በኋላ አገሩን ከየኢጣሊያ ወረራ ነፃ ለማውጣት የአርበኝነት ትግላቸውን ለመቀጠል ወሰኑ፡፡ የፊታውራሪ አየለ ቁርጠኝነት እና የአገር ፍቅር ስሜት በዳዛ የሚገኙትን የአርበኞችን የትግል መንፈስ ያበረታታና ያነቃቃ ነበር።
5. የዳዛ እና የደንቢያ ጀብዱ
ህዳር 30 ቀን 1930 ዓ.ም. ከአይከል የመጡት የኢጣሊያ ወታደሮች በድብቅ ዳዛ የሚገኙትን የቀኛዝማች አየለን አርበኞች አጥቅቶ ለማያዝ መጥተው ነበር። ሆኖም የኢትዮጵያ የውስጥ አርበኞች፤ እነቀኛዝማች አየለ የሚገኙበትን ስፍራ ያመለክታል ብለው የሀሰት የመሬት ካርታ ለጠላት ወታደሮች ስለሰጧቸው እና አርበኞችም ይህን የጠላትን ድብቅ ተንኮል በመረዳት ይህን ድንቅ አጋጣሚ በመጠቀም ቁልፍ የሆነ እስትራተጃዊ ኮረብታ በመቆጣጠርና አመች ቦታዎችን በመያዝ ለውጊያ ተዘጋጁ፡፡ ጠላትም በተሳሳተ ካርታ እየተመራ በአርበኞች ዒላማ ውስጥ ገባ፡፡ አርበኞችም ተኩስ በመክፈት የጠላት ኃይሎችን ደምስሰው 57 የጠላት ጠመንጃዎችንና በርካታ ጥይቶችን ማረኩ፡፡ በድጋሚም ጥር 30 ቀን 1930 ዓ.ም. የቀኛዝማች አየለ አርበኞች ደንቢያ ውስጥ ጨንቀል ተክለሐይማኖት በተባለው የውጊያ ሜዳ ላይ የኢጣሊያንን ጦር በማጥቃት 50 ከብቶችንና 10 ጠመንጃዎችን በመማረክ ጀብዱ ፈጽመዋል። ከላይ የተገለጹት በጠላት ጦር ላይ የተመዘገቡት ተከታታይ ድሎች፤ የቀኛዝማች አየለን የአርበኞች ሞራል ከፍ ያደረጉና የውጊያ መንፈስ ያጠነከሩ በመሆናቸው የተነሳ ወዲያውኑ አይከል ወደሚገኘው የኢጣሊያ ካምፕ በመሄድ በከተማው ዙሪያ የሚገኙትን የኢጣሊያ የጥበቃ ኃይሎችን ተቆጣጠሩ፡፡ ከሱዳን መሃዲስቶች ጋር ሲዋጋ የውትድርና አመራር ልምድ የነበረው የቀኛዝማች አየለ ታላቅ ወንድም ግራዝማች ረዳ፤ የጭልጋ አርበኞች መሪ በመሆንና ሰቀልት፣ መተማና ቋራ አካባቢዎችን በመጨመር የጠላት ኃይልን መታገል ጀመረ፡፡ ቀኛዝማች አየለና አበራም፤ የታላቅ ወንድማቸውን የግራዝማች ረዳ የጦር አመራርን በመቀበል የሌሎች አርበኞች መሪ ሆነው ትግላቸውን ቀጠሉ፡፡ የአገሬው ነዋሪዎችም በወንድማማቾች የሚመራውን የአርበኞችን ገድል ለማወደስ፤
ነጭ አሞራ ዞሮ ይገባል ከዋሻ፣
እንዴት አለህ ዳዛ የጦሩ መነሻ፡፡
የሚል ግጥም ገጥመውላቸዋል፡፡
6. በተከታታይ የተፈፀመ የአርበኝነት ተጋድሎ
የኢጣሊያን ጦር የአርበኞችን ይዞታ ለመደምሰስ በከፍተኛ ትጥቅ ተደራጅቶ ውጊያ ለመግጠም ወደ አርበኞቹ አመራ፡፡ የቀኛዝማች አየለ አጋሮች የሆኑት፤ አማረ ጣሰው፣ ዓለም መኮንን እና ነጋሽ አለሙ የተባሉት አርበኞች ጠላት ወደ እነርሱ ካምፕ እያመራ እንደሆነ መረጃ ስለነበራቸው በዛሆ ላይ በሶስት አቅጣጫ ምሽግ ሰርተው ጠላትን ይጠባበቁ ነበር፡፡ በዚህን ጊዜ እነ ቀኛዝማች አየለ ከአይከል እየሸሹ የሚመለሱትን የጠላት ወታደሮችን በማጥቃት አኩሪ ድል አስመዝግበዋል፡፡ በዛሆ ምሽግ ላይ ሆነው በጠላት ላይ ያደረሱት ጥቃት በአርበኞቹ ላይ ከፍ ያለ የሞራል መነሳሳትና መነቃቃትን ፈጥሯል፡፡ የጭልጋ አርበኞች፤ በጠላት ላይ በተደጋጋሚ ያስመዘገቡት ድልና በተከታታይ ከጠላት ጋር ያካሄዱት የደፈጣና መደበኛ ጦርነት፤ በውጊያ እስትራተጅና ታክቲክ እንዲሁም በአደረጃጀት የነበራቸውን ልምድ እንዲያዳብሩ አግዟቸዋል፡፡ በግንቦት ወር 1930 ዓ.ም. አየለና አበራ ከአርበኞቻቸው ጋር ሆነው ወደ ጎንደር በሚወስደው መንገድ ዋግሚት በሚባለው ወንዝ አጠገብ የውስጥ አርበኞች በማያውቁት እስትራተጃዊ ቦታ ላይ ምሽግ ሰርተው ቦታውን ላይ ጦራቸውን አሰፈሩ፡፡ በዚህን ጊዜ ቁጥራቸው 50 የሚሆኑ የጠላት ወታደሮችን የያዘ ኮንቮይ፤ ሻለቃ መራ በተባለው አዛዣቸው እየተመራ ወደ አይከል በመጓዝ ላይ ነበር፡፡ ይህን የተመለከቱ የቀኛዝማች አየለ አርበኞች በሚጓዘው ኮንቮይ ላይ ተኩስ ከፍተው ብዙ የጠላት ወታደሮችን ሲገሉ፤ ከሞት የተረፉትም ከአዛዣቸው ጋር ወደ ጎንደር ሲሸሹ የነአየለ ወታደሮችም ከጠላት ለመሰወር ቦታውን ለቀው ሄዱ፡፡ እነ ፊታውራሪ አየለ፤ ረዳና አበራ ከጀግኖች አርበኞቻቸው ጋር ሆነው በጎንደር፤ በመተማና በጭልጋ በጠላት ላይ በተከታታይ ያገኙት ድል በሰሜን እና በጎንደር በሰፊው ዝናቸው በመሰማቱ፤ ለሠሩት ጀብድ የአድናቆት ደብዳቤ ከንጉሠ ነገሥቱ
ቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ
ተልኮላቸዋል፡፡ የጠላት ጦር የአርበኞችን ዋና ምሽግ የሆነውንና በሶስት እረድፍ ማለትም፤በሎሚ ዋርካ፣ በመቀነት እና በበዛሆ መሽጎ የሚገኘውን የፊታውራሪ አየለን አርበኞች ለመደምሰስ በሰፊው ተደራጅቶ፣ ተዘጋጅቶና በዘመናዊ መሳሪያ ታጥቆ ከሌሊት እስከ ንጋት በከፈተው ውጊያ ከባድ ጦርነት ተካሄደ፡፡ በዚህም ውጊያ ፊታውራሪ አየለ ሆዳቸው ላይ ተመተው ከባድ ጉዳት ስለደረሰባቸው እና ብዙ ደም ስለፈሰሳቸው በሞት አፋፍ ላይ ደርሰው ነበር፡፡ በዚህን ጊዜ አማረ ጣሰው የተባለው አርበኛ ደርሶ ፊታውራሪ አየለን ከወደቁበት አንስቶ በአቅራቢያው ወደሚገኘው ዋሻ ወስዶ ደበቃቸው፡፡ ከጥቂት ቀናት በኋላ ፊታውራሪ አየለ ከቁስላቸው ስላገገሙ አርበኞቻቸውን እንደገና መምራት ቀጠሉ፡፡ በኋላም የፊታውራሪ አየለ ታላቅ ወንድምና የአርበኞች መሪ ለሆነው ለግራዝማች ረዳ ፤ በንጉሠ ነገሥቱ በተጻፈለት ደብዳቤ መሰረት፤ ግራዝማች ረዳ ከአገሩ አርበኞች ጋር በመሆን የንጉሡን የጦር ኃይል ማለትም፣ ከንጉሡ መልእክተኛ ከደጃዝማች ከበደ ተሰማ እና በጄነራል ስታንፈርድ ከሚመራው ከእንግሊዝ ሠራዊት ጋር በመሆን የጦር መሣሪያዎችን እና ጥይቶችን ለማምጣት ወደ ሱዳን ታዞ ሄደ። ሱዳን ከደረሰ በኋላም፤ ግራዝማች ረዳ ከ
ቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ
ጋር በመገናኘት፤ አንድ ሺህ ብር፣ 300 ያህል ጠመንጃዎች እና 3 ሺህ ጥይቶችን ተቀብለ፡፡ በመጨረሻም ግራዝማች ረዳ ሁለት የእንግሊዝ ወታደራዊ መኮንኖችን፣ ሁለት መድፎችና “ሱሉጉ” ከሚባሉ በርካታ የሱዳን ቅጥረኛ ወታደሮች ጋር በመተማ በኩል ወደ ዳዛ ተመለሰ። ግራዝማች ረዳ ሱዳን ውስጥ በነበረበት ጊዜ ፊታውራሪ አየለ ከደረሰባቸው ጉዳት እምብዛም ባያገግሙም ቅሉ፤ አሁንም በዳዛ ውስጥ የካምፑ ኃላፊ ሆነው ከሌሎች አርበኞች ጋር በጀግንነት በጠላቶቻቸው ላይ ተደጋጋሚ የመልሶ ማጥቃት እርምጃ በመውሰድ በተሳካ ሁኔታ ሲከላከሉ ቆይተዋል። እነ ግራዝማች ረዳ ከሱዳን ከተመለሱ ከ 8 ወራት በኋላ ግንቦት 10 ቀን 1933 ዓ.ም. አርበኞች ተሰባስበው አንጉባ ከተባው ስፍራ አጠገብ የሚገኘውን ‹‹ብሩ ሠፈር›› የተሰኘውን የጠላት ምሽግ ለማጥቃት፤ በፊታውራሪ አየለ፣ በግራዝማች ረዳ፣ በደጃዝማች ከበደ እና በቀኛዝማች ማንአለብህ ባይተዋ መሪነት በአራት እረድፍ ሆነው ወደስፍራው አመሩ፡፡ በሻለቃ ሀንክስ የሚመራው 13ኛው የሱዳን ሻለቃ የእንግሊዝ ጦርም የኢጣሊያ ጦር ወደ መሸገበት ስፍራ በማምራት በሞርታር በመደብደብ ከፊታውራሪ አየለ እና ከግራዝማች ረዳ የአርበኞች ሠራዊት ጋር በመሆን በጠላት ምሽግ ላይ ወረራ ፈጽመው ለአንዴና ለመጨረሻ ጊዜ ምሽጉን ደመሰሱት፡፡ ከዚህ በኋላ በጠላት ቁጥጥር ስር የነበረው ጭልጋ ሙሉ በሙሉ ከጠላት ነፃ መሆን ቻለ፡፡
7. ከነፃነት በኋላ የሕይዎት ዘመን
የፊታውራሪ አየለ ወንድም ግራዝማች ረዳ ንጉሠ ነገሥቱ ዘንድ ቀርበው በታላቁ ቤተ መንግሥት የፊታውራሪነት ማእረግ ተሰቷቸዋል፡፡ ፊታውራሪ አየለ የወረዳ አስተዳዳሪነት ሹመት ቢሰጣቸውም የእርሳቸውን ያህል የአርበኝነት ስራ ላልሰሩት የላቀ ማእረግ ሲሰጣቸው በማየታቸው በተሰጣቸው ሹመት እምብዛም ደስተኛ አልነበሩም፡፡ በኋላም ፊታውራሪ አየለ በተለያየ ጊዜ በተለያዩ ከተማዎች የአስተዳዳሪነት ሹመት ተሰጥቷቸው በርካታ ስራዎችን አከናውነዋል፡፡ በ1966 ዓ.ም. መፈንቅለ መንግሥት ከተካሄደ በኋላ ፊታውራሪ አየለ በተፈጠረው የፖለቲካ ሂደት ውስጥ ለመሳተፍ ፈቀደኛ ስላልነበሩ ቤተሰባቸውን ይዘው ወደ ሱዳን ተሰደዱ፡፡ ከ7 ዓመት የሱዳን ቆይታ በኋላ ፊታውራሪ አየለ ተሰማ በ 1975 ዓ.ም. በጠና ታመው ሱዳን በሚገኘው ጋዳሪፍ ሆስፒታል ውስጥ ሲታከሙ ከቆዩ በኋላ በተወለዱ በ72 ዓመታቸው ከዚህ ዓለም በሞት ተለይተዋል፡፡ አስከሬናቸውም በጊዜዊነት ሱዳን ተዋቫ በሚገኘው የቅዱስ ሚካኤል ቤተ ክርስቲያን ከተቀበረ በኋላ በቤተሰቦቻቸው አማካኝነት አስከሬናቸው እንደገና ተቆፍሮ ወጥቶ ወደ ሀገራቸው ከተመለሰ በኋላ በተወለዱበት ዳዛ በሚገኘው በቅዱስ ጊዮርጊስ ቤተ ክርስቲያን በታላቅ ክብር አርፏል፡፡
ወደ አርበኞች ገጽ 1 ይመለሱ «
ምንጭ፤
ምስጋና የጽሁፍ አስተዋፆ ላደረገው ለ፤ አሹ ዋሴ
ከዊኪፒዲያ የተተረጎመ
wikipedia
የትረካው አጃቢ ሙዚቃ፣ ዋሽንት - በአንሙት ክንዴ
ዩቲውብ