አባኮስትር በጦር ሜዳ ተጋድሎ የማይበገር፣ በእምነቱም የማይደራደር መሆኑን የኢጣሊያ ባለሥልጣኖች ስላመኑበት፤ በማግባባት ዘዴ ለማጥመድ ኢጣሊያዊው የጎጃም ገዥ ደብዳቤ ጽፎ ላከለት፡፡
የተላከውም ደብዳቤ ሲነበብ፤
“ደብረ ማርቆስ ድረስ መጥተህ እጅህን ብትሰጥ የኢጣሊያ መንግሥት መሐሪ ስለሆነ ምሕረት ያደርግልሃል፡፡
ልጅህንም ለቀን አንተንም የጎጃም እንደራሴ ስለምናደርግህ ለኢጣሊያ መንግሥት ታማኝ ሆነህ ግባ፡፡”
የሚል ነበር፡፡
አባኮስትርም ለተጻፈለት ደብዳቤ፤
“ጎጃምን ያህል አገር እንደራሴነት ካገኘሁ፣ ልጄም ከተለቀቀች ሌላ ምን እፈልጋለሁ፡፡
ለኢጣሊያ መንግሥት ታማኝ ናቸው የሚላቸውን መልእክተኞች ይላክልኝና እመጣለሁ፡፡”
የሚል መልስ ላከ፡፡
የኢጣሊያ ባለሥልጣናትም በአባኮስትር ደብዳቤ ተደስተው ታማኝ የሚሏቸውን መልክተኞች ላኩ፡፡ መልክተኞችም አባኮስትር ዘንድ ደረሱ፡፡
ወደ አባኮስትር የተላኩት መልዕክተኞች፤ ቀኛዝማች እጅጉ ለማ፣ ቀኛዝማች አደራና ሌላ ሦስተኛ ሰውም ነበር፡፡
አባኮስትር ወደ መልክተኞች እያፈጠጠ፤
“በሉ የምትሉትን ልስማ፡፡ ምን ዝም አሰኛችሁ? አንተ ሶስተኛው ሰው ደግሞ ማን እሚሉህ ነህ?”
በማለት በንዴት ስሜት እየተንጎራደደ ጠየቃቸው፡፡
ቀኛዝማች አደራም ሶስተኛው ሰው አስተርጓሚ መሆኑን አስረዳ፡፡
አባ ኮስትርም ድጋሚ በሚያሰፈራ አስተያየት ወደመልክተኞች እያፈጠጠ፤
“ዛሬ ደግሞ ምን ይፈልጋሉ ጌቶቻችሁ?
የኢጣሊያ ታማኞች እጄን ለማያዝ ቸኩላችኋል እሳ?”
ኧረ ለመሆኑ ምን መስየ ታየሁት? እጄን ይዞ ለመሾም ነው እንዲህ የቸኮለው?
በማለት ተናገረ፡፡
መልክተኞችም፤
ከናንተ ጋር ይምጣ ተብለን ታዘን ነው እንጅ እኛ ጦር አስከትለን አልመጣንም ብለው መለሱ፡፡
አባ ኮስትርም፤
“እነ አጅሬ ታማኝ መሆናችሁን መች አጣሁት?
እነዚህ ሰዎች እንወደዳለን በማለት በወገናቸው ላይ እየፈረዱ ብዙ ጀግኖች ወንድሞቻችንን አስለቅሰዋል፡፡ ጎበዝ፤ እናንተም ታውቃላችሁ ፍረዱ!”
በማለት ዙሪያውን የተቀመጡትን አርበኞች ጠየቃቸው፡፡
አርበኞችም፤ “በቤልጅግ ጠመንጃ ግንባራቸውን ፈልጦ እንጨት ላይ መስቀል ነው” በሚለው ፍርድ ተስማምተው ለኢጣሊያ ታማኝ በነበሩት በሁለቱ ዳኞች ላይ ወዲያውኑ የሞት ቅጣቱ ተፈጸመባቸው፡፡
አባኮስትር በጣሊያኖች ስለተማረከችው ልጁ ሲናገር፤
“ልጄ እናቷ በጦር ሜዳ ስትሞትባት ያለኋት እኔ መሆኔ እርግጥ ነው፡፡
ቢሆንም ቅሉ አካሌ የሆነችው ልጄም ሆነች ነባቢት ነፍሴ ከኢትዮጵያ ነፃነት እንደማይበልጡብኝ አምናለሁ፡፡
ስለዚህ ራሴን የኢጣሊያ መሣሪያ በማድረግ ልጄን ከምርኮኛነት አላወጣትም፡፡”
በማለት ቁርጥ ያለ አቋሙን ተናገረ፡፡
ከዚህ በኋላ አባኮስትር በላይ የደብረ ማርቆስ ገዥ ለሆነው ለኢጣሊያ አዛዥ በጻፈው ደብዳቤ ላይ፤
“የላክልኝን እንግዶች በሚገባ አስተናግጃቸዋለሁ፡፡
ወሬውን እንዲነግርህ የላካችሁትን አስተርጓሚ መልሼ ልኬዋለሁ፡፡
ጎጃም የእኔ አገር ሲሆን፤ አንተ ደግሞ ከሮማ መጥተህ የጎጃምን እንደራሴነት እሰጥሀለሁ ማለትህ ያሳዝናል፡፡
ልጄንም፣ እኔንም የፈጠረን እግዚአብሔር ነው፡፡
ልጄን እንደፈለክ አድርጋት እንጅ እኔ ለኢጣሊያ መንግሥት ታማኝ ሆኘ አልገዛም፡፡”
የሚል መልስ ላከላቸው፡፡
በ10 ዓመት ዕድሜዋ በጠላት ተማርካ የነበረቸው የበላይ ዘለቀ ሴት ልጅ ወይዘሮ ሻሸወርቅ በላይ በመካከለኛ የዕድሜ ዘመኗ የተነሳችው ፎቶ
ፎቶው ተወስዶ የተስተካከለው ከ፤
borkena.com
የአባኮስትር ልጅ ሻሸወርቅ በላይ የተወለደችው በ1920 ዓ.ም. አካባቢ ሲሆን ስትማረክ ገና የ10 ዓመት ልጅ ነበረች፡፡
ጣሊያኖች አባ ኮስትርን አባብሎ ወደ እነርሱ ለማስገባት ያሰቡት ሁሉ ሳይሳካ ቀረ፡፡
የአባኮስተር ሠራዊት የኢጣሊያንን ጦር ገጥሞ በጠላት ላይ ከፍተኛ ጉዳትና ውርደት በማድረሳቸው በተገኘው ድል አርበኞች ከፍተኛ ደስታ ተሰምቷቸዋል፡፡
በዚህም ጦርነት፤ የኢጣሊያ ጦር አዛዥ አንድ ኮሎኔል ጨምሮ 28 የኢጣሊያ ወታደሮች፣ አንድ ሺህ ያህል የባንዳ ወታደሮች፣ ሲሞቱ፤ በከብት የሚጫን አንድ የውሃ መትረየስ፣ 9 የራዲዮ መገናኛ፤ 9 ባዙቃና በርካታ ጠመንጃዎችና ጥይቶች ተማርከዋል፡፡
ጠላት በዚህ በደረሰበት ከፍተኛ ሽንፈት ምክንያት ሽብር ላይ በመሆኑ፤ አራቱ ያባ ኮስትር ታማኝ አሽከሮች ከሻሸወርቅ ሞግዚት ጋር በአንድነት ሆነው ልጅቷን ከኢጣሊያ የጦር ካምፕ ለማሶጣት አቀዱ፡፡ እቅዳቸውንም በድብቅ ሄደው ለአባኮስትር በማማከር በነሐሴ ወር 1932 ዓ.ም. በግምት ከምሽቱ 3 ሰዓት ነጎድጓዳማ ካፊያ በነበረበት ጥቅጥቅ ባለ ጨለማ ውስጥ ልጅቷን ይዘው ከጠላት ካምፕ አውጥተው ወደ ሸበል በረንታን በረሃ ይዘዋት ሄዱ፡፡ በመጨረሻም ያባ ኮስትር ታማኝ አሽከሮች፤ እነአባኮስትር የሠፈሩበት የጦር ካምፕ ሲደርሱ፤ አባኮስትር እና አርበኞቹ በተሰበሰቡበት በትልቅ አዳራሽ ውስጥ ሰፊ ድግስ ተደግሶ፣ እየተበላና እየተጠጣ፣ ፉከራው እና ቀረርቶው ደምቆ ነበር፡፡
አባኮስትርም ልጁ የሻሽወርቅ በላይ ከጠላት እጅ ወጥታ በደህና መድረሷና ከእርሱ ጋር በመገናኘቷ ከፍተኛ እፎይታና ደስታ ተሰምቶታል፡፡
አባኮስትር ለሚያቅራራው ሰው የሚከተለውን የሽለላ ግጥም ነገረው፡፡
- አህያ ነው ጣሊያን ክብሩን የማይጠብቅ፣
- ከሰው ሀገር መጥቶ እማይጠነቀቅ፡፡
- እማይሆንለትን ከጀግና አገር ገብቶ፣
- ከእኛ እጅ ጣለው ኃጢያቱ በርክቶ፡፡
- ለገንዘብ የሚሞት የቅጥር ወታደር፣
- ራሱን ያፈቅራል አይሆንም ለሀገር፡፡
- አይሆንም ለሀገር አይሆንም ለዘመድ፣
- ለገንዘብ የሚሞት ይቅር አይወለድ፡፡
የአባኮስትር አርበኞችም ስለአባኮስትር ሲናገሩ፤
“ከግል ክብርና ዝና ይልቅ ለሀገርና ለሕዝብ ደህንነት የሚጥር ወጣት የጦር መሪ በማግኘታችን ዕድለኞች ነን፡፡
ንቁነቱ፣ ደፋርነቱ፣ ለጭፍራው አሳቢነቱ፣ ሐይማኖተኛነቱ፣ ለሕዝብ ተቆርቋሪነቱ እና ለሀገር ነፃነት ታጋይነቱ፤ አባኮስትር በላይን የልጅ አዋቂ አድርጎታል፡፡”
በማለት መሪያቸውን አሞግሰውታል፡፡
ፎቶው ተወስዶ የተስተካከለው ከ፤ borkena.com