Content-Language: am የወሎው ንጉሥ ሚካኤል
header image



የወሎው ንጉሥ ሚካኤል



የወሎው ንጉሥ ሚካኤልን
የሕይወት ታሪክ ያዳምጡ















1. ትውልድና የአገዛዝ ዘመን


King Mikael of Wollo
የወሎው ንጉሥ ሚካኤል

Photo credit to: allaboutethio.com
ንጉሥ ሚካኤል በ1842 ዓ.ም. አካባቢ የተወለዱ ሲሆን፤ ከመንገሣቸው በፊት ራስ መሀመድ ዓሊ ተብለው ወሎን ይገዙ ነበር፡፡
ከደሴ በስተሰሜን 10 ኪሎ ሜትር ያህል ርቆ ቦርከና ወንዝ አጠገብ በሚገኘው ቦሩ ሜዳ ተብሎ በሚጠራው ሰፊ ረግረጋማ ሜዳ ላይ፤ በግንቦት ወር 1870 ዓ.ም. በንጉሠ ነገሥት አፄ ዮሐንስ 4ኛ አማካኝነት የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ የሲኖዶሱ ሃይማኖታዊ ጉባኤ ተካሂዶ ነበር፡፡
በዚህ ሐይማኖታዊ ጉባዔ ላይ በዋናነት፤ የሸዋው ንጉሥ ምኒልክ፤ የጎጃሙ ራስ አዳል ተሰማ (በኋላ ንጉሥ ተክለ ሐይማኖት)፣ የወሎው ኢማም መሐመድ ዓሊ (በኋላ ንጉሥ ሚካኤል) እና ሌሎችም ተገኝተው ነበር፡፡
በተካሄደውም የሲኖዶሱ ሐይማኖታዊ ጉባኤ ላይ፤ የመንታ ልደት አስተምህሮ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ይፋዊ እምነት ተብሎ እንዲታወቅና ተቀባይነት እንዲያገኝ ሆኖ፤ በተፃራሪው በደብረ ሊባኖስ ገዳም ይሰበክ የነበረው የሶስት ጊዜ ልደት ወይም የጸጋ ትምህርት ደግሞ እንዲወገድና አስተምህሮው እንዳይሰጥ እገዳ ተጥሎበት በነበረበት ወቀት አፄ ዮሐንስ 4ኛ፤ ኢማም መሐመድ አሊንና በወሎ ውስጥ ስልጣን ላይ የነበሩትን ሙስሊሞች ሁሉ በሶስት ወር ጊዜ ውስጥ ክርስትናን እንዲቀበሉ ወይም አቋማቸውን እንዲለውጡ አስገደዷቸው፡፡
የሆነ ሆኖ አንዳንድ የወሎ አመራሮች ወደ ክርስትና ሲቀየሩ እጅግ በጣም ብዙው የወሎ ሙስሊም ህዝብ ግን የክርስትና እምነትን ለመቀበል ፈቃደኛ አልነበረም ፡፡
በዚህ የተነሳ አፄ ዮሐንስ የክርስትና እምነት ለመቀበል ፈቃደኛ ያልነበሩትን በሺዎች የሚቆጠሩ የወሎ ሙስሊሞችን በቦሩ ሜዳ በጅምላ እንዳስጨፈጨፉ ይነገራል፡፡
የንጉሥ ሚካኤል
ባለቤት ሸዋረጋ ምኒልክ
የቀሩትም ክርስትናን ለመቀበል ያልፈለጉት የወሎ ሙስሊሞች፤ ወደ መተማ ፣ ጅማ እና ሐረር ከተማ ለመሸሽ ተገደዋል፡፡
ኢማም መሀመድ ዓሊ፤ የአፄ ዮሐንስን ትእዛዝ በፈቃደኛነት ተቀብለው ክርስትና ሲነሱና መጠሪያቸው ራስ ሚካኤል ሲባል፤ አፄ ዮሐንስ የክርስትና አባታቸው ነበሩ፡፡
ውሎ አድሮም የ42 ዓመቱ ንጉሥ ሚካኤል፤ ከአራት ሚስቶቻቸው መካከል ሦስተኛ ሚስት በማድረግ፤ ከእቴጌ ጣይቱ የማትወለደውንና የዳግማዊ አፄ ምኒልክ 2ኛ ሴት ልጅ የሆነችውን የ25 ዓመቷን ወጣት ሸዋረጋ ምኒልክን አገቡ፡፡
ንጉሥ ሚካኤል እና ሸዋአረጋ ምኒልክ፤ ወይዘሮ ዘነበወርቅ እና ልጅ እያሱን ወልደዋል፡፡

ራስ ሚካኤል፤ ደሴን በመቆርቆርም አዲሲቷ የወሎ ዋና ከተማና የራሳቸው መቀመጫ እንድትሆን አድርገዋል፡፡

2. በአድዋ ዘመቻ ተሳትፎና የአገዛዝ ዘመን

ራስ ሚካኤል በአድዋ ዘመቻ ወቅት በዳግማዊ አፄ ምኒልክ በተመደበላቸው የሶሎዳ ተራራ አውደ ውጊያ ላይ ሆነው ፋሽስት ኢጣሊያን ለመውጋት አሰፈሪ የሆነውን የፈረሰኛ ጦራቸውን እየመሩ ተሠልፈው ተዋግተወል፡፡
King Mikael and His Son Lij Iyasu
ልጅ እያሱ ከአባታቸው ከንጉሥ ሚካኤል ጋር

Photo credit to: allaboutethio.com
በዚህ የዐድዋ ዘመቻ አንድ የኢጣሊያ ብርጌድ የያዘውን ዋና የጦርነት ስፍራ ለቆ ማፈግፈግ ጀመረ፡፡
ወዲያውኑ ያፈገፍግ የነበረው የፋሽስት ብርጌድ ጦር ሳያስበው የራስ ሚካኤል ፈረሰኞች ደርሰው በያዙት ጎራዴ አንገት አንገቱን ሲቀሉት፤ “አጨዱን! አጨዱን!” እያለ በመጮህ ወደ ጠባብ ሸለቆ መገሠገስ ጀመረ፡፡
በዚህ ፋታ በማይሰጠው ውግያ መካከል የብሪጌድ አዛዡ አስከሬን እንኳን በጭራሽ ሊገኝ አልቻለም፡፡

የዳግማዊ ምኒልክን ሞት ተከትሎ በእግራቸው የተተካውና ያልነገሠው ልጅ እያሱ በሰጠው ትዕዛዝ መሠረት፤ ራስ ሚካኤል የወሎና የትግራይ ንጉሥ ሆነው እንዲሾሙ በማድረግ በተዘዋዋሪ ዘውዱን እንዲወርሱ አመቻችቶላቸዋል፡፡
ይሁን እንጅ፤ በልጅ እያሱ አካሄድ ያልተደሰቱት መሳፍንቱ ምክር ቤቱን ሰብስበው፤ የንጉሥ ሚካኤል የሚስታቸው እህት የሆኑት ወይዘሮ ዘውዲቱ ምኒልክ ንግሥተ ነገሥታት ዘውዲቱ ተብለው የአባታቸውን ዙፋን እንዲወርሱና በተጨማሪም ምክር ቤቱ ወጣቱን ራስ ተፈሪ መኮንንን፤ አልጋ ወራሽና የወደፊቱ ንጉሠ ነገሥት ቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ ተብለው እንዲሠየሙ ወሰነ፡፡

3. የሰገሌ ዘመቻ

ልጅ ኢያሱ ከሥልጣናቸው ሲወገዱ፤ ንጉስ ሚካኤል የሰጡት ምላሽ ፈጣን ነበር፡፡
ንጉስ ሚካኤል መስከረም 27 ቀን 1909 ዓ.ም. ሸዋ ላይ ጥቃት ለመሰንዘር እና የልጃቸውን ሥልጣን ለማስመለስ 80 ሺህ የወሎ ጦር ይዘው ሲዘምቱ፤ ልጅ እያሱም በፊናቸው የራሳቸውን ጦር እየመሩ ከወሎ ተነሱ፡፡
ይህ በንግሥት ዘውዲቱ ጦርና በንጉሥ ሚካኤል ጦር መካከል ጥቅምት 7 ቀን የተጀመረው ውጊያ የሰገሌ ጠርነት የሚል መጠሪያ ተሰቶታል፡፡
ስሙንም ያገኘው ጦርነቱ ከተካሄደበት ሥፍራ ሲሆን ሰገሌ ከአዲስ አበባ በስተሰሜን በ 40 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ ይገኛል፡፡
የሰገሌ ጦርነት ከአድዋ ጦርነት ቀጥሎ ትልቁ ጦርነት እንደሆነ ይነገራል፡፡
አለቃ ገብረ እግዚአብሔር ኤልያስ የተባሉት በሥፍራው የነበሩ የአይን እማኝ እንደተናገሩት ከሆነ፤ የሰገሌን ጦርነት ያስጀመሩት ንጉሥ ሚካኤል፤ የእግረኛና የፈረሰኛ ጦራቸውን ውጊያውን እንዲጀምር በጥኋቱ ትእዛዝ ሰጥተው ነበር፡፡
ሆኖም የሸዋ ወታደሮች ጠመንጃዎቻቸውን በማከታተልና እና በገላጣ ሥፍራ እንዲተኩሱ ስልጠና የወሰዱ በመሆናቸው በፍጥነትና በተከታታይ የተኩስ እሩምታ ማርከፍከፍ ሲጀምሩ የንጉሥ ሚካኤል ጦር እንደ ቅጠል መርገፍ ጀመረ፡፡
የወሎ ጦርም ጥይቱን ጨረሰ፡፡
ከዚያም የሸዋው ጦር ተከታታይ ጥቃት በመሰንዘር የወሎን ጦር በማሳደድ በርካታ ምርኮኞችን ለመያዝ ቻለ፡፡

4. ምርኮ፤ እስርና ሕልፈተ ሕይዎት


Negus Mikael Tomb
የንጉሥ ሚካኤል የመቃብር ሥፍራ

Photo Link
የሸዋው ፈረሸኛ ጦር የንጉሥ ሚካኤልን ሠራዊት በየሸለቆው እየተከታተለ ማባረሩን ቀጠለ፡፡
የንጉሥ ሚካኤልም የጦር ካምፕ በሙሉ ተደመሰሰ፡፡
ንጉሥ ሚካኤልም ተማርከው የታዋቂው የጦር አዛዥ የፊታውራሪ ሀብተ ጊዮርጊስ ዲነግዴ እስረኛ ሆኑ፡፡
ልጅ እያሱ፤ የራሳቸውን ጦር ይዘው ውጊያው ሥፍራ ሲደርሱ፤ አባታቸው በጦርነቱ ድል ሆነው አገኟቸው፡፡
በሰገሌው ጦርነት ከሁለቱም ወገን የሙትና ቁስለኛ ቁጥር እጅግ በርካታ ነበር፡፡
ንጉሥ ሚካኤልም ለንግሥት ዘውዲቱ ያቀረቡት ልመና ተቀባይነት እስኪያገኝ ድረስ ጉራጌ አገር ወደሚገኘው ጨቦ ወደተባለው ስፍራ ተሰደው ለሁለት ዓመት ያህል ቆይተዋል፡፡
በመጨረሻም በሆለታ ገነት ለ 6 ወራት ያህል የቁም እስረኛ ሆነው ከቆዩ በኋላ በእስር ቤት ውስጥ እንዳሉ ሕይዎታቸው ሊያልፍ ችሏል፡፡
ንጉሥ ሚካኤል በቆዩባቸው የንግሥና ዘመናት፤ ደሴን ከመቆርቆራቸውም ባሻገር፤ በነበራቸው ጠንካራ የኦርቶዶክስ ተዋህዶ እምነት የተነሳ በርካታ አብያተ ክርስትያናትን አሳንፀዋል፡፡ --> ( የእንግሊዝኛውን ጽሁፍ የበለጠ ለማንበብ )


ምንጭ፤
  1. ከ  allaboutethio የተተረጎመ
  2. ከዊኪፒዲያ የተተረጎመ
  3. የትረካው አጃቢ ሙዚቃ፣ ዋሽንት - በአንሙት ክንዴ   ዩቲውብ