Content-Language: am የጎጃሙ ንጉሥ ተክለ ሐይማኖት
header image




የጎጃሙ ንጉሥ ተክለ ሐይማኖት



የጎጃሙ ንጉሥ ተክለ ሐይማኖትን
የሕይዎትና የአርበኝነት ታሪክ ያዳምጡ














1. በአፄ ተክለ ጊዮርጊስ ዘመነ መንግሥት

King Tekle Haymanot of Gojam
የጎጃሙ ንጉሥ ተክለ ሐይማኖት
ንጉሥ ተክለ ሐይማኖት ከንግሥናቸው በፊት አዳል ተሰማ ይባሉ ነበር፡፡
አባታቸው ንጉሥ ተሰማ ጎሹ በኢትዮጵያ አፄዎች ቁጥጥር ሥር የነበሩ የጎጃም ገዥ ነበሩ።
በዚህን ወቅት በጎጃም ያሉት ሌሎች የጎጃም የአገዛዙ ሥርዓት መሳፍንቶች መሪነቱን ለመጨበጥ ፉክክር ጀመሩ፡፡
አዳል ተሰማ፤ አባታቸው ንጉሥ ተሰማ ጎሹ ሲሞቱ ለጠላቶቻቸው በመጋለጣቸው ምክንያት የአባታቸው የደጃዝማች ተሰማ ጎሹ ተቀናቀኝ የሆኑት እና የደጃዝማች ተድላ ጓሉ ልጅ ደጃዝማች ደስታ ተድላ ጎጃምን ለሞቆጣጠር ስለፈለጉ አዳል ተሰማን አሰሯቸው፡፡
አዳል ተሰማም በእስር ቤት እያሉ እድሜያቸው እየጎለመሰ ሲሄድ ከእስር ቤት አምልጠው ጠፉ፡፡
አዳል ተሰማ የራሳቸውን ጦር ካደራጁ በኋላ ጦራቸውን ይዘው በመሄድ ከአጎታቸው ከደጃዝማች ደስታ ተድላ ጋር ጦርነት ገጥመው አሸነፉ፡፡
በኋላም አዳል ተሰማ በወቅቱ ንጉሠ ነገሥት ለነበሩት ለአፄ ተክለ ጊዮረጊስ (ዋግሹም ጎበዜ) ለመገበር ፈቀደኛ በመሆናቸው ተክለ ጊዮረጊስ አዳል ተሰማን የደጃዝማችነት ሹመት ሰጥተው የጎጃም ሹም አደረጓቸው፡፡
ተክለ ጊዮረጊስም አልፈው ተርፈው እህታቸውን ላቀች ገብረ መድኅንን ለደጃዝማች አዳል ተሰማ ዳሩላቸው፡፡
አፄ ተክለ ጊዮርጊስ፤ በዘመኑ ኃያልና ሩህሩህ፣ የተማረኩ ጠላቶቻቸውን የሚምሩ መሓሪ ንጉሥ እንደነበሩ ይነገራል።

2. በንጉሠ ነገሥት ዮሐንስ 4ኛ ዘመነ መንግሥት

The Tekle Haymanot Arch in Debre Markos
የንጉሥ ተክለሐይማኖት ቤተ መንግሥት መግቢያ በር

Photo Link
ሐምሌ 5 ቀን 1863 ዓ.ም. የትግራዩ ደጃዝማች ካሣ ምርጫ (በኋላ አፄ ዮሐንስ 4ኛ)፤ ከንጉሠ ነገሥት ተክለ ጊዮርጊስ ጋር ጦርነት ገጥመው ተክለ ጊዮርጊስን ማሸነፍ ችለዋል፡፡
አፄ ዮሐንስ የኃይል ሚዛናቸውን ለማስጠበቅ ሲሉ፤ አቅም ካላቸው ከሸዋው ምኒልክ ይልቅ ወደ ጎጃሙ ደጃዝማች አዳል ያደሉ ነበር፡፡ ይሁን እንጅ በመጀመሪያወቹ ዓመታት የአፄ ዮሐንስና የአዳል ግንኙነት እምብዛም የሠመረ አልነበረም፡፡
ይልቁንም ደጃዝማች አዳል፤ የንጉሥ ተክለ ጊዮርጊስ ታማኝና በጋብቻ የተሳሰሩ ስለነበሩ ደጃዝማች ካሣ ምርጫ የደጃዝማች አዳልን መሠረት ለማሳጣት ሲሉ፤ ወደ ጎጃም ሄደው ደጃዝማች አዳል ተሰማን ከስልጣን አንስተው በምትካቸው አፄ ቴዎድሮስን ኃይለኛ ተቀናቃኝ ሆኖ ያውካቸው የነበረውን የደጃዝማች አዳል ተሰማ አጎት የተድላ ጓሉን ልጅ ደስታ ተድላን የራስነት ማዕረግ ሰጥተው በጎጃም ላይ ሾሙት፡፡
በዚህም የተነሳ ደጃዝማች አዳል ጎጃምን ጥለው ሄዱ፡፡
ጥር 13 ቀን 1864 ዓ.ም. ደጃዝማች ካሣ ምርጫ “ንጉሠ ነገሥት ዮሐንስ 4ኛ” ተብለው ከነገሱ በኋላ ጎጃምን ለቀው ወጡ ፡፡
አፄ ዮሐንስ ጎጃምን ለቀው እንደሄዱ ደጃዝማች አዳል ወደ ጎጃም ተምልሰው መጥተው ከራስ ደስታ ተድላ ጋር ተዋግተው ራስ ደስታን ከገደሉ በኋላ የጎጃምን ግዛት ጠቅልለው ያዙ፡፡
በ1866 ዓ.ም. ደጃዝማች አዳል ለአፄ ዮሐንስ ለመገበር ፈቃደኛ በመሆናቸው የራስነት ማዕረግ ከተሰጣቸው በኋላ የኢትዮጵያ ዋና ከተማ በመሆን የአፄ ዮሐንስ አራተኛ መቀመጫ በሆነችው በደብረ ታቦር ከተማ አፄ ዮሐንስ ለራስ አዳል ጥር 13 ቀን 1873 ዓ.ም. የንግሥና ሹመት ሰጥተው “ንጉሰ ጎጃም ወከፋ” ተብለው የጎጃምና የከፋ ጠቅላይ ግዛቶችን እንዲያስተዳድሩ ሥልጣን ሲሰጧቸው፤ ልክ እንደአባታቸው እንደ ንጉሥ ተሰማ ጎሹ ሁሉ እሳቸውም ጊዜያቸውን ጠብቀው የጎጃም ንጉሥ ሆኑ።

3. ከንግሥና በኋላ የተከናወኑ ታሪኮች

ንጉሥ ተክለ ሐይማኖት ከፋ ጠቅላይ ግዛትን ለመያዝ ሙከራ ሲያደርጉ እምባቦ ላይ ከሸዋው ንጉሥ ምኒልክ ጋር ግንቦት 30 ቀን 1874 ዓ.ም. ጦርነት ገጥመው በመሸነፋቸው ተማረኩ፡፡
አፄ ዮሐንስም ከሁለቱ ንጉሦች ውጊያ በኋላ ከፋን ንጉሥ ምንይልክ እንዲያስተዳድሩ ከፈቀዱ በኋላ፤ በምትኩ ግን በምኒልክ ይተዳደር የነበረውን የወሎን ጠቅላይ ግዛት ከምኒልክ ነጥቀው ለልጃቸው ለራስ አርያሥላሴ ዮሐንስ እንዲሰጥ አዘዙ፡፡

አፄ ዮሐንስ በጉንደትና በጉራ ከግብፆች ጋር በሚፋለሙበት ወቅት ንጉሥ ተክለ ሐይማኖት በቤገምድርና በሰሜን የተነሳውን የመሀዲስቶች አመፅ ለማክሸፍ ጥር 10 ቀን 1888 ዓ.ም. ከመሀዲስቶች ጋር ጦርነት በገጠሙበት ወቅት ጦራቸው ልክ እንደ አንበሳ ኃያል ክንዱን በወራሪው መሀዲስት ላይ በማሳረፍ ከፍተኛ ተጋድሎ አድርጎ ነበር፡፡ ሆኖም የመሀዲስቶች ጦር ቁጥሩ እጅግ አይሎ ልክ እንደ አንበጣ ፈጣን ወረራ በማካሄዱ የኋላ ኋላ ድሉ የመሀዲስቶች ሆነ፡፡
የመሀዲስት ጦር በጎጃምና በጎንደር በኩል በፈፀመው ወረራ ከፍተኛ ጉዳት ከማድረሱም በላይ ጎንደርን አቃጥለዋል፣ በብዙ ሺህ የሚቆጠሩ ክርስቲያኖች ተጨፍጭፈዋል፣ በመቶዎች የሚቆጠሩ ሴቶችና ሕፃናት ለባርነት ተዳርገተዋል፣ ቀሳውስት ከጣሪያው ላይ ተወርውረው ተገድለዋል፡፡

ይህ ሁሉ ድርጊት ከተፈፀመ በኋላም አፄ ዮሐንስ ንጉሥ ተክለ ሐይማኖት ከንጉሥ ምንይልክ ጋር ግምባር ፈጥረው አብረውብኛል በሚል ሰበብ የንጉሥ ተክለ ሐይማኖትን ጦር ለማጥፋት ጎጃም ድረስ በመዝመት የባላገሩን ቤት በመዝረፍና በማቃጠል በጎጃም ምድር እጅግ ዘግናኝ የሆነ ከፍተኛ እልቂትና ውድመት እንዳደረሱ በታሪክ ተመዝግቧል፡፡

በ1881 ዓ.ም. አፄ ዮሐንስ በጋላባት ጦርነት ላይ ከተሰው በኋላ ንጉሥ ምኒልክ ብዙም ሳይቆዩ እራሳቸውን ንጉሠ ነገሥት ምኒልክ ብለው አወጁ። ንጉሥ ተክለ ሃይማኖትም ለአዲሱ ነጉሠ ነገሥት ታማኝነታቸውን ስለገለፁ፤ ምኒልክም ተክለ ሃይማኖትን የጎጃም ሹም በማድረግ ሰይመዋቸዋል።

በሌላ በኩል፤ የጎጃሙ ንጉሥ ተክለ ሐይማኖት የፈፀሙት ታሪካዊ ተጋድሎ፤ 3 ሺህ ጦር ይዘው በጦር አበጋዝነት (በጦር መሪነት) ወደ ዐድዋ በመዝመት ከዳግማዊ አፄ ምኒልክ ጋር የፋሽስት የኢጣሊያ ጦርን በመግጥም የማይናቅ ተጋድሎ ያደረጉ የጦር አርበኛ ናቸው፡፡

የንጉሥ ተክለ ሐይማኖት የአስተዳደጋቸው ዝርዝር ታሪክ ብዙም ግልጽ ባይሆንም፤ ራስ አዳል ተሰማ ተብለው ከ1861 እስከ 1872 ዓ.ም፤ ከ1873 እስከ 1893 ዓ.ም. ድረስ በድምሩ ለ32 ዓመታት በኢትዮጵያ ግዛት ውስጥ የሰለሞናዊው ሥርዎ መንግሥት አባል በመሆን የጎጃም ንጉሥ ሆነው ገዝተዋል፡፡

ንጉሥ ተክለ ሐይማኖት በአጠቃላይ በኖሩበት የሕይወት ዘመናቸው የተሻለ ነው ብለው ያሰቡትን መልካም ነገር ሁሉ ለሀገራቸው ሲያከናውኑ ኖረው ጥር 3 ቀን 1893 ዓ.ም. በእለተ አርብ ደብረ ወርቅ በተባለው ስፍራ ከዚህ ዓለም በሞት ተለይተዋል፡፡....(የበለጠ ለማንበብ)

ከንጉሥ ተክለ ሃይማኖት ሞት በኋላ፤ አፄ ምኒልክ ጎጃም በአንድ ንጉሥ አስተዳደር ብቻ ሊመራ የማይችል ትልቅና ኃያል አገር እንደሆነ በማሰብ ጎጃምን በሦስት ቦታ ከፍለው ለመቆጣጠር ወሰኑ፡፡

ንጉሥ ተክለ ሐይማኖት ሶስት ወንድና አራት ሴት ልጆች ነበሯቸው፡፡
ወንድ ልጆቻቸውም፤
  1. በዛብህ ተክለ ሐይማኖት
  2. ኃይሉ ተክለ ሐይማኖት እና
  3. በለው ተክለ ሐይማኖት
ይባላሉ፡፡



ምንጭ፤
  1. "አጤ ምኒልክ"  ደራሲ፡- ጳውሎስ ኞኞ የካቲት ወር 1984 ዓ.ም.
  2. "የኢትዮጵያ ታሪክ - ከአፄ ልብነ ድንግል እስከ ዳግማዊ አፄ ቴዎድሮስ"  ደራሲ፡- ተክለ ጻድቅ መኩሪያ 1961 ዓ.ም.
  3. በተጨማሪ ከዊኪፒዲያ የተተረጎመ
  4. የትረካው አጃቢ ሙዚቃ፣ ዋሽንት - በአንሙት ክንዴ   ዩቲውብ