ደጃዝማች ነሲቡ ዘአማኑኤል
የደጃዝማች ነሲቡ ዘአማኑኤል የአርበኝነትና የሕይዎት ዘመን ትረካ
ነሲቡ ዘአማኑኤል አዲስ አበባ በሚገኘው በዳግማዊ ምኒልክ ትምህርት ቤት ከወንድማቸው ወሰኔ ጋር የተማሩ ሲሆን በዚያም የምዕራቡን ዓለም ትምህርት ቀስመዋል፡፡
እንደ ፐሮፌሰር ባህሩ ዘውዴ አባባል፤ ነሲቡ ዛማኑኤል፤ ከወንድማቸው ከወሰኔ ጋር በ20ኛው ክፍለ ዘመን ከነበረው የመጀመሪያው ትውልድ ውስጥ አንፀባራቂ ከሆኑት ምሁራን መካከል ይቆጠራሉ በማለት ገልፀዋቸዋል፡፡
በ1885 ዓ.ም. የተወለዱት ደጃዝማች ነሲቡ ዛማኑኤል የአዲስ አበባ ከንቲባ በመሆን አገልግለዋል፡፡
ነሲቡ የለውጥ አራማጅ ከንቲባ ስለነበሩ፤ ካደረጓቸው ማሻሻያዎችም መካከል፤
- የከተማ መሬት ምዝገባ እና ምደባ፣
- የትራፊክ ፖሊስ ማቋቋም፣
- የጽዳት ጠባቂዎችን መመደብ፣
- በበዓላት ወቅት ጥይት የመተኮስ ባህልን መከልከል ፣
- ሌባን ለማውጣጣት ጥቅም ላይ ይውል የነበረውን የሊባ ሻይ ጥንታዊ ሥርዓትን መከልከል፣
- በየመንገዱ የሞቱ እንስሳትን ማሶገድ፣ መቅበር፣
- በዋና መንገዶች ዳር ለሚገነቡ ሰዎች ግንባታው የከተማዋን ውበት ይጨምራል ተብሎ ስለሚታመን ለግንባታው ብድር መስጠት፣
- የአዲስ አበባን ዘመናዊ የውኃ አቅርቦት ሥርዓት ለማዘመን የተሞከሩ የማስተዋወቅ ምርምሮች፤
የሚሉት ይገኙበታል፡፡
ነሲቡ ዛማኑኤል፤ በዘመናዊ መንገድ ያደራጁት የማዘጋጃ ቤት ፖሊሶች አዛዥ በነበሩበት ወቅት፤
በ1928 ዓ.ም በልዑል ራስ ተፈሪ መኮንን በኋላ (ቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ) እና በደጃዝማች ባልቻ ሳፎ መካከል በነበረው የስልጣን ሽኩቻ፤
ራስ ተፈሪን በመደገፍ ከፍተኛ ሚና ተጫውተዋል።
በ1928 ዓ.ም. ነሲቡ ዛማኑኤል የጦር ሚኒስቴር ዳይሬክተር ሆነው በቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ ተሹመዋል።
ነሲቡ ዛማኑኤል፤ በሚስዮን ትምህርት ቤት ስለተማሩ፣ ጣሊያንኛ እና ፈረንሳይኛ ቋንቋ ስለሚናገሩ እና የአውሮፓ ዘመናዊ ልብሶችን እና ዩኒፎርሞችን በመልበሳቸው ምክንያት በብዙ መሳፍንቶች ዘንድ ኢትዮጵያዊ እንዳልሆኑ ይቆጠሩ ነበር።
በ1923 ዓ.ም. ልዑል ራስ ተፈሪ መኮንን ንጉሠ ነገሥት ከሆኑ በኋላ ነሲቡ ዛማኑኤል የደጃዝማችነት ማዕረግ ተሰቷቸው የጉራጌ ጠቅላይ ግዛትን እና የሶዶ ጠቅላይ ግዛትን እንዲያስተዳድሩ ሹመት ተሰጣቸው።
በኋላም በ1924 ዓ.ም. የባሌ ጠቅላይ ግዛት አስተዳዳሪ ሆነው ተሸሙ፡፡
2. በፋሽስት ኢጣሊያ ወረራ ወቅት በደቡብ ጦር ግንባር የነበራቸው ተሳትፎ
በደቡብ ግንባር የነበረው የኢትዮጵያ ጦር የሚመራው በሲዳሞው ገዥ በራስ ደስታ ዳምጠው ሲሆን፣ በደቡብ ምሥራቅ ግንባር የነበረውን የኢትዮጵያ ጦር ደግሞ የሐረር ገዥ በሆኑት በደጃዝማች ነሲቡ ዛማኑኤል ነበር፡፡
ከሰሜኑ ጦር ግንባር ጋር ሲነፃፀር የደቡብ ጦር ግንባር በመሣሪያ አቅርቦትም ሆነ በአመራሩ የውጊያ ስሜት የተሻለ ነበር ማለት ይቻላል፡፡
ደጃዝማች ነሲቡ በሁለተኛው የፋሽስት ወረራ ወቅት “በደቡብ ጦር ግንባር” ተዋግተዋል። በተለይ ግራዝማች አፈወርቅ ወልደሰማያት ከሞቱ በኋላ በዚህ ግንባር የኢትዮጵያ ጦር ዋና አዛዥ ሆነው የደቡብን ጦር በአዛዥነት መርተዋል፡፡
ደጃዝማች ነሲቡ፤ በተለይ በኦጋዴን ጦርነት ወቅት ከኢጣሊያው ጄኔራል ሮዶልፎ ግራዚያኒ ጦር ጋር ሲዋጉ የነበረውን የኢትዮጵያ ሠራዊት መርተዋል።
በዚህ ከግራዚያኒ ጋር በተደረገው ጦርነት የፋሽስት ጦር በኢትዮጵያ ሠራዊት ላይ የሙስታርድ ጋስ ቦምብ በሚያዘንብበት ወቅት ነሲቡ፤
“...የመንግስታቱ ድርጅት የሆነው ሊግ ኦፍ ኔሽንስ አሁን እያወራ በአለበት ሰዓት እኛ እየታገልንና እየሞትን ነው።
እኛ ቤታችንንና መሬታችንን በመጠበቃችን ምክንያት በመበሳጨቱ፤ በጦርነት የሚታወቁትን በጣም መጥፎ የሆኑ ሁሉንም አይነት መሣሪያዎችንና ዘዴዎችን የሚጠቀም ወራሪ አጋጥሞናል።
ምናለበት ወንዶች ከሆኑ እንደሰው ቢዋጉ!
በቅሎቻችን፣ በጎቻችንና ከብቶቻችን በየሜዳው እየሞቱ ነው።
መሬቶቻችን ሳየቀሩ በጋዝ ቦምብ እየተቃጠሉ ነው፡፡”
በማለት ሐዘናቸውን በምሬት ተናግረዋል፡፡
3. የደጃዝማች ነሲቡ በጄኔቭ ቆይታ
ደጃዝማች ነሲቡ፤ በግንቦት ወር 1928 ዓ.ም. ንጉሠ ነገሥቱ እና ንጉሣውያን ቤተሰቦች ወደ እንግሊዝ አገር በስደት ሲሄዱ አብረው ሄደዋል።
ደጃዝማች ነሲቡ፤ ንጉሠ ነገሥቱ ለዓለም መንግሥታት ማህበር (ሊግ ኦፍ ኔሽንስ) አቤቱታ ለማቅረብ ወደ ጄኔቭ ሲሄዱ፤ ወደ ጄኔቭ ለተጓዘው የልዑካኑ ቡድን መሪ በመሆን ለአጭር ጊዜ አገልግለዋል፡፡
ደጃዝማች ነሲቡ፤ ለሊግ ኦፍ ኔሽንስ ጉባዔ ዋና ፀሐፊ የሚቀርበውንም ሁለት የውሳኔ ሃሳቦችን አርቅቀው አቅርበዋል፡፡
4. የደጃዝማች ነሲቡ ሕልፈተ ሕይዎት
ራስ ነሲቡ፤ ጥቂት ጊዚያትን እንደቆዩ ባደረባቸው ሕመም ምክንያት ንጉሣዊያን ቤተሰቡን ለመለየት ተገደዱ፡፡
በኋላም በጦርነቱ ወቅት በደረሰባቸው የሙስታርድ ጋስ ቦምብ ሳቢያ ህመማቸው ስለጠናባቸው ጥቅምት 6 ቀን 1929 ዓ.ም. ስዊስዘርላንድ በምትገኘው በዳቮስ ከተማ በተወለዱ በ43 ዓመት የጎልማሣነት እድሜያቸው ከዚህ ዓለም በሞት ተለይተዋል፡፡
ደጃዝማች ነሲቡ፤ ባለቤታቸው ወይዘሮ ውሂብ ፓሻ ካጠገባቸው አልተለዩዋቸውም ነበር፡፡
ደጃዝማች ነሲቡና ባለቤታቸው ወይዘሮ ውሂብ፤ ወይዘሮ ማርታ ነሲቡ የተባሉ አንድ ሴት ልጅ አፍርተዋል፡፡
ልጃቸው ወይዘሮ ማርታ ነሲቡ የተዋጣላቸው ድንቅ ኢትዮጵያዊ አርቲስትና ፀሐፊ እንደነበሩ ተዘግቧል። ደማቅ ሥዕሎቻቸውም ዘመናዊውን ከባህላዊው ያጣመሩ መሆናቸው ይነገራል፡፡
ምንጭ፤
- "የታሪክ ማስታወሻ" ደራሲ፡- ደጃዝማች ከበደ ተሰማ 1962 ዓ.ም.
- "የኢትዮጵያ ታሪክ - ከአፄ ቴዎድሮስ እስከ ቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ" ደራሲ፡- ተክለ ጻድቅ መኩሪያ 1961 ዓ.ም.
- "የኢትዮጵያ ታሪክ ከ 1847 እሰከ 1983" ደራሲ፡- ፕሮፌሰር ባሕሩ ዘውዴ
- ከዊኪፒዲያ የተተረጎመ
- የትረካው አጃቢ ሙዚቃ፣ ዋሽንት - በአንሙት ክንዴ ዩቲውብ