Content-Language: am ደጃዝማች በቀለ ወያ
header image



ደጃዝማች በቀለ ወያ



የደጃዝማች በቀለ ወያን
የአርበኝነት ታሪክ ያዳምጡ
















1. ትውልድና ዕድገት

Dejazmach Bekele Woya
ደጃዝማች በቀለ ወያ

image link
ደጃዝማች በቀለ ወያ ከአባታቸው ከአቶ ወያ አብሴ እና ከእናታቸው ከወይዘሮ ብርቄ ጅሎ ጎዳና ነሐሴ 21 ቀን 1902 ዓ.ም. በደቡብ ሸዋ ሶዶ ውስጥ ልዩ ስሙ ጎጌቲ ሲብስቶ በሚባል መንደር ተወለዱ፡፡
የአማርኛ ትምህርትን እቤታቸው ድረስ አስተማሪ ተቀጥሮላቸው አጠናቀቁ፡፡
በቀለ በአባታቸው የሶዶ ጉራጌ (ክስታኔ) ሲሆኑ በእናታቸው ደግሞ የኦሮሞ ተወላጅ ናቸው፡፡
በቀለ ወያ የደጃዝማች ገብረ ማሪያም ጋሪ የእህት ልጅ ናቸው፡፡
16 ዓመት ሲሞላቸው እናታቸው አጎታቸው ወደሆኑት ወደ ደጃዝማች ገብረ ማሪያም ጋ ወሰዷቸው፡፡
በቀለም እንዳደጉ የአጎታቸው የደጃዝማች ገብረ ማሪያም የእልፍኝ አስከልካይ ሆኑ፡፡
የበቀለ ወያ ጨዋነት፣ ሐቀኝነት፣ ትዕግስት እና ብልህነት ወደ አጎታቸው እንዲቀርቡ አደረጋቸው።
ደጃዝማች ገብረ ማሪያም ጋሪ ከ1923 ዓ.ም. ጀምሮ ለ3 ዓመት የሐረርጌ ጠቅላይ ግዛት ተወካይ ሆነው በቆዩበት ወቅት፤ በቀለ ወያ በ21 ዓመት እድሜያቸው ከአጎታቸው ጋር ሄደው በውትድርና ሲያገለግሉ ቆይተው በኋላም የ “ሻቃ" ማዕረግ ተሰቷቸው ምክትል አስተዳዳሪ ሆነው መሥራት ቀጠሉ፡፡
አጎታቸው ደጃዝማች ገብረ ማሪያም የሚኒስትርነት ማዕረግ ሲሾሙ፤ ሻቃ በቀለ የፀረ ታንክ መሣሪያ ተኳሽነት ሥልጠና ወስደዋል፡፡

2. የአርበኝነት ዘመን ተጋድሎና ጀብዱ

Dejazmach Bekele Woya
ደጃዝማች በቀለ ወያ ከአርበኞቹ ጋር

image credit to: Gordena Ethiopia media
በ1928 ዓ.ም. ፋሽስት ኢጣሊያ በኢትዮጵያ ላይ ወረራ ሲፈጽም፤ ሻቃ በቀለ ከአጎታቸው ከደጃዝማች ገብረ ማሪያም ጋሪ ጋር በመሆን በ26 ዓመት እድሜያቸው ወደ ሰሜን ጦር ግንባር በመዝመት አስደናቂ ወታደራዊ ብቃትን አሳይተዋል፡፡
በደቡብ ጦር ግንባር በሲዳሞ በኩል የገባው የጠላት ጦር ብርቱ ነበርና በቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ ትእዛዝ ገብረ ማሪያም ጋሪ ወደ ደቡብ ጦር ግንባር እንዲዘምቱ ሲታዘዙ፤ ሻቃ በቀለም አብረዋቸው ዘመቱ፡፡
በሲዳሞ በኩል ወደ መሀል አገር የዘመተው የጠላት ጦር የበላይነቱን ይዞ ነበር።
ቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ ትእዛዝ ደጃዝማች ገብረ ማርያም ተመልሰው ወደ ሲዳሞ ግንባር እንዲዘምቱ ታዘዙ።
ደጃዝማች ገብረ ማርያምም ትዕዛዙን ተቀብለው ወደ ደቡብ ጦር ግንባር ሲያቀኑ በቀለ ወያም አብረዋቸው ነበሩ።
በጦር ግንባሩም እንደደረሱ በቀለ ወያ በውጊያው ወታደራዊ ጀብዱ ፈጽመዋል፡፡
የጠላት ታንኮች የወገንን ጦር ሲያጠቁ ሲመለከቱ በጣም ያዝኑ ነበር፡፡
አንድ ቀን አምስት የጠላት ታንኮች በመደዳ ቆመው የወገንን ጦር እያጠቁ ሲመጡ ደጃዝማች ገብረ ማሪያም ተመልክተው፤
“በቀለ ያ ብልሃትህ ለመቸ ሊሆን ነው! አትለውም ወይ! ...ወይኔ!”
እያሉ ሲያዝኑ በቀለ ወያ ዝም ብለው ሲመለከቱ ቆይተው ወደ ታንኮቹ ጠጋ ብለው በደንብ ሲታዩዋቸው በመድፋቸው ተኩሰው የመጀመሪያውን ታንክ መትተው አቃጠሉት፡፡
ቆይተው ሁለተኛውንም ታንክ ደገሙት፡፡
በመጨረሻም በአምስት ደቂቃ ውስጥ አምስቱንም ታንኮች አቃጥለው አነደዷቸው፡፡
ከዚያም በቀለ፤ ደጃዝማች ገብረ ማርያምን፤
“ደጃዝማች! ...ሄደው እሳት ይሙቁ!” እንዳሏቸው ይነገራል፡፡
በ1928 ዓ.ም. በቀለ ወያ የደጃዝማች ገብረ ማርያምን የመድፈኛ ቡድን ፊት ለፊት እየመሩ በበዳና፣ አቄሮና ሶዶ በረሃ ሲጓዝ፤ በደጃዝማች ገብረ ማሪያም ጋሪ ላይ ይተኩስ የነበረውን የጠላት ጦር አውድመውታል፡፡
በዚህም ጦርነት በርካታ በውሃ የሚሰሩ መድፎች፣ 14 ቀላል የአልቢን ጠመንጃወች፣ 30 የጠላት ጦር አዛዦችና በርካታ ወታደሮች ተማርከዋል፡፡
ይህን የጀግንነት ሥራቸውን የተመለከቱት ደጃዝማች ገብረ ማርያም ለበቀለ ወያ የተለየ አድናቆታቸውን ሰጥተዋቸዋል፡፡
ከሰኔ እስከ መስከረም ወር 1928 ዓ.ም. ድረስ ዳባ ሴሬ በተባለው አውደ ውጊያ ላይ ከጠላት ጦር ጋር ከባድ ጦርነት አካሂደዋል፡፡
በዚህ ውጊያ ላይ ደጃዝማች ገብረ ማሪያም ጋሪ ሲቆስሉ ጀግናው በቀለ ወያ ድግሞ 12 የጠላት ታንኮችን ከጥቅም ውጭ በማድረግ አንፀባራቂ ጀብዱ ፈጽሟል፡፡
በተጨማሪም ጀግናው አርበኛ በቀለ ወያ፤ በአለታ ወንዶ፣ በአርበጎና፣ በደላ ቸሬ፣ በሂብኖ፤ በአርሲና በላኪ ደንበል በተካሄዱ ውጊያዎች የፈፀሟቸው ጀብዱዎች በወርቅ ቀለም ተጽፈው እና በታሪክ መዝገብ ተመዝግበው ለትውልድ የሚተላለፉ አኩሪ ገድሎች ናቸው፡፡
ለበቀለ ወያ የሚከተለው ግጥም ተገጥሞላቸዋል፡፡

አላስኬድም አለኝ ጣሊያን በመንገዱ
ያ ሻቃ በቀለ ና ወንዱ ና ወንዱ፤


Dejazmach Gebremariam Gari
ጀግናው አርበኛ ደጃዝማች ገብረማሪያም ጋሪ

image link
ደጃዝማች ገብረ ማሪያም ጋሪ በተከታታይ ውጊያዎች በጀግንነት ሲሳተፉ ቆይተው ጎጌቴ በተባለው ሥፍራ በተካሄደው ከባድ ጦርነት ሲዋጉ ሕይዎታቸው ሊያልፍ ችሏል፡፡
በደጃዝማች ገብረ ማርያም ሞት ምክንያት በቀለ ወያ ጀግና አጋራቸውን በማጣታቸው ከባድ ሀዘን ተሰምቷቸው እንደነበረ ይነገራል፡፡
በቀለ ዋያ ከደጃዝማች ገብረ ማርያም ሞት በኋላ የወንድማቸው ልጅ የሆኑትን ደጃዝማች በዳኔ ጉደታን እና ሌሎችንም አጋሮች ይዘው በትውልድ ሥፍራቸው በሰዶ የርበኝነት ትግላቸውን ቀጠሉ፡፡
በቀለ ወያም አርበኞች ወንድሞቻቸውን እነ በየነ ጉደታን ይዘው የአርበኝነቱን ትግል በሶዶ ውስጥ አምስቱን ዓመት ከአዲስ አበባ 50 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ በመገኘት ከፍተኛ የአርበኝነት ተጋድሎ አድርገዋል፡፡
በተለይ ግንቦት 22 ቀን 1932 ዓ.ም. የፋሽስት ወራሪ ጦር የ24ኛ ብርጌድ አዛዥ እና የክፍለ ሀገሩ አስተዳዳሪ ተብሎ ይጠራ የነበረው ኮሎኔል ካዛባሳ በ18 የወታደር መጫኛ መኪናዎች 22 መኮንኖችንና 60 ወታደሮችን ይዞ ከአዲስ አበባ ጎቴ ወደ ተባለው ስፍራ ለማለፍ በጉዞ ላይ ሳለ፤ ከአዲስ አበባ 60 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ በምትገኘው ሌመን ባኮ ተብላ በምትጠራው ስፍራ እንደደረሱ፤ በአካባቢው የሚገኘው ነዋሪ፤ “ኧረ እነዚህ ሰዎች ማለቃቸው ነውና አኛም በጊዜ እንሽሽ” እየተባባሉ ሲያወሩ ከመካከላቸው አንዱ ወደ ጠላት ወታደሮች ሄዶ አርበኞች በአካባቢው እንዳሉ ሲነግራቸው እነርሱም ራሳቸውን አዘጋጅተው ጉዟአቸውን ቀጠሉ፡፡
አርበኞችም አድፍጠው ምንም ተኩስ ሳያሰሙ መኪኖችን አንድ በአንድ ካሳለፏቸው በኋላ የጠላት መኪኖች ዒላማቸው ውስጥ ሲገቡላቸው፤ በመጀመሪያ ሻቃ በቀለ ወያ ራሳቸው በጥይት ተኩሰው ፊት ለፊት የሚጓዘውን የመኪና ጎማ መተው አሰተነፈሱት፡፡
ሌሎች አርበኞች ደግሞ በተራቸው የሌሎችን መኪኖች ጎማቸውን ተኩሰው አስተነፈሷቸው፡፡
ከዚህ በኋላ የጠላት ወታደሮች መሄጃ አጥተው ሲራወጡ አርበኞቹ እያነጣጠሩ በ 18ቱም መኪኖች ተጭነው የነበሩትን የጠላት መኮንኖችና ወታደሮች በሙሉ አንድ ሰዓት ባልሞላ ጊዜ ውስጥ በጥይት እሩምታ ተኩሰው ገደሏቸው፡፡
በመጨረሻም አርበኞቹ የጠላት ወታደሮችን እሬሣ በሙሉ ለቅመው በራሳቸው ካሚዎን ከጫኗቸው በኋላ ናፍጣ አርከፍክፈው በእሳት ካቃጠሉት በኋላ ሌሉቱን ሙሉ እንደጧፍ ሲነድ እንዳደረ ተዘግቧል፡፡
የበቀለ ወያ ጦር ድል እያስመዘገበ በመቀጠሉ የጠላት ጦር ወደ ሶዶ መጠጋት አልቻለም፡፡
የበቀለ ወያ ጦር በሶዶና በአካባቢው ከጠላት ጋር በሚያካሂዳቸው ውጊያዎች ድል እየቀናው ሲመጣ የአካባቢው ሰዎች ለበቀለ ወያ የነበራቸው ክብር እየጨመረ በመምጣቱ ወደ አርበኞች የሚቀላቀለው ቁጥር እየጨመረ ሄደ፡፡
በኋላም በቀለ ወያ የቅርብ ዘመዳቸው ከሆኑት ከደጃዝማች ገረሱ ዱኪ ጋር ደብዳቤ በመላላክ በጋራ ጠላትን ለመዋጋት ተነጋግረው ትግላቸውን በማቀናጀት የጠላትን ጦር መግቢያና መውጫ አሳጡት፡፡
ደጃዝማች ገረሱ የኢጣሊያ ሰላይ በነበረው ሙሲ ላይ የፈፀሙትን የሞት ቅጣት ተከትሎ በድርጊቱ የተበሳጩት የኢጣሊያ የጦር አዛዦች፤ ከጅማ፣ ከሲዳሞ፣ ከሐረር፣ ከአርሲና ከሸዋ ጦር አሰባስበው እና በጦር አይሮፕላን ጭምር የተደገፈ ውጊያ በመክፈት በደጃዝማች ገረሱና በበቀለ ወያ ሠራዊት ላይ ከባድ ጉዳት አደረሱ፡፡
በዚህም ውጊያ በቀለ ወያ በቀኝ ክንዳቸው ላይ በመቁሰል የለመዱትንና የሚወዱትን የሎንቸር መሣሪያ ለመተኮስ አልቻሉም፡፡ ስለሆነም በደረሰባቸው ከባድ ውጊያ ምክንያት የተበታተነው ጦር እንደገና ተሰባስቦ እስኪደራጅና የቆሰሉትም እስኪያገግሙ ጥቂት ጊዚያት እርፍት አደረጉ፡፡
በ 1932 ዓ.ም. በቀለ ወያ ከራስ አበበ አረጋይ ምክር ለመቀበል ወደ ቡልጋ ተጓዙ፡፡
በቀለ ወያ በድል ከተወጧቸው ከባድ ውጊያዎች ውስጥ አቡ በተባለው ሥፍራ ኮሎኔል ካዛባሳ ከተባለው የጠላት ጦር አዛዥ ጋር በተደረገው ጦርነት 26 የጠላት ጦር መኮንኖች እና 30 ወታደሮች ሲገደሉ፤ የሞቱቱን ወታደሮችን ጭኖ ለመውሰድ የመጡትም 18 የጠላት መኪኖች ሳይቀሩ በእሳት ጋይተዋል፡፡
በቀለ ወያ ከደጃዝማች ገረሱ ጋር በመሆን የሀገራቸው ነፃነት እስኪመለስ ድረስ ያለማቋረጥ የጠላት ጦርን እየደመሰሱና እየማረኩ ታሪክ ሲያስታውሰው የሚኖር ተከታታይነት ያለው ተጋድሎ በማድረግ ትውልዱን የሚያኮራ የጀግንነት ገድል ፈጽመዋል፡፡

3. ከነፃነት በኋላ

ኢትዮጵያ ነፃነቷን ካገኘች በኋላ ደጃዝማች በቀለ ወያ በተለያዩ የአስተደዳደር ሥራዎች ተመድበው አገልግለዋል፡፡
ደጃዝማች በቀለ ወያ የሕክምና ዕርዳታ ለማግኘት ወደ ስዊዘርላንድ ሊጓዙ ሲሉ ባደረባቸው ሕመም ምክንያት ገና በጎልማሳነት እድሜያቸው በተወለዱ በ44 ዓመታቸው በ1946 ዓ.ም. ሕወታቸው ሊያልፍ ችሏል፡፡
ሥርዓተ ቀብራቸውም በመንበረ ፀባፆት ቅድስት ሥላሴ ካቴድራል በክብር ተፈጽሟል፡፡

የደጃዝማች በቀለ ወያ መታሰቢያ

በአዲስ አበባ በልደታ ከፍል ከተማ ወረዳ 9 የሚገኝ አንድ የቅድመ መደበኛ ትምህርት ቤትና እንዲሁም በአብነት አደባባይ ወደ ኮካ ኮላ የሚወስደው 1.2 ኪሎ ሜትር እርዝማኔ ያለው አንድ መንገድ በስማቸው ተሰይሞላቸዋል፡፡


ምንጭ፤
  1. "ቀሪን ገረመው" ደራሲ፤ ቀኝአዝማች ታደሰ ዘወልዴ 2008 ዓ.ም.
  2. …ምስጋና፤ ለገጣሚ፣ ጸሐፊና ጋዜጠኛ ለ ዓለም ኃይሉ ገብረ ክርስቶስ - tuckmagazine.com
  3. …ምስጋና፤ ለወሊሶ ኤኮሎጂ ካምፕ ሳይት:-   Link
  4. የትረካው አጃቢ ሙዚቃ፣ ዋሽንት - በአንሙት ክንዴ   ዩቲውብ