Content-Language: am ደጃዝማች ገብረ ማሪያም ጋሪ
header image



ደጃዝማች ገብረ ማሪያም ጋሪ (አባ ንጠቅ)




የደጃዝማች ገብረ ማሪያም ጋሪን (አባ ንጠቅ)
የአርበኝነት ታሪክ ያዳምጡ









1. ትውልድና እድገት


Dejazmach Afework Woldesemayat
ደጃዝማች ገብረ ማሪያም ጋሪ
ገብረ ማሪም በምዕራብ ሸዋ፣ አገምጃ ውስጥ፣ ልዩ ስሙ ሰርቦ ኦዳ ኮሎ በተባለ ስፍራ ውስጥ ከአባታቸው ከአቶ ጋሪ ጎዳና እና ከእናታቸው ከወይዘሮ ሌሎ ጉዴ በ1866 ዓ.ም. 13ኛ ልጅ ሆነው ተወለዱ፡፡
ወላጆቻቸውም የልጃቸውን ስም ገሜሳ ብለው ሰየሙት፡፡ በኦሮምኛ ገሜሳ ማለት መልካም እንደማለት ነው፡፡
ገሜሳም ከተወለደ በኋላ የልጅነት ጊዜውን ያሳለፈው በተወለደበት ሥፍራ ነበር፡፡
ገሜሳ ገና በለጅነት እድሜው አርቆ አስተዋይ እንደነበረ ይነገራል፡፡
ከእለታት አንድ ቀን በፊታውራሪ ዘመንፈስ ቅዱስ የሚመራው የዳግማዊ ምኒልክ ጦር ገሜሳ ያለበት ስፍራ ድረስ መጣ፡፡
ፊታውራሪ ዘመንፈስ ቅዱስም ወጣቱን ገሜሳን ማርከው ወደ አዲስ አበባ በማምጣትና ከዚያም ወደ መሐል ሸዋ ቡልጋ አውራጃ ወደሚገኘው ወደ ኢቲሳ ተክለ ሐይማኖት ገዳም እንዲወሰድ አደረጉ፡፡
በዚያን ወቅት ኢቲሳ ተክለ ሐይማኖት ገዳም በርካታ ወጣቶች ለወደፊት በኃላፊነት ቦታ የሚታጩበትና በታማኝነት አገራቸውን እንዲያገለግሉ የሚቀረጹበት ቦታ ሆኖ ከማገልገሉም ባሻገር፤ በቤተ ክህነት የተዋህዶን ሐይማኖት እየተማሩና በተጨማሪም የቤተ መንግሥትም ሥርዓት እንዲማሩ የሚደረግበት ስፍራ ነበር፡፡
ገሜሳ በኢቲሳ ተክለ ሐይማኖት ገዳም ትምህርቱን እየተማረ ሳለ በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ሐይማኖት መሠረት በክርስትና ስሙ በገብረ ማሪያም መጠራት ጀመረ፡፡
ገብረ ማሪያም ትምህርቱን በሚከታተልበት ወቅት ስለቤተሰቡ ሁኔታ ምንም መረጃ አልነበረውም፡፡
ቤተሰቦቹም ልጃቸው ገሜሳ በሕይወት የለም ብለው እርማቸውን አውጥተው ነበር፡፡
የረጅም ጊዜ ሥልጠናውን ሲከታተል ቆይቶ የሚካኤል እለት የጎፈር ሚካኤል ንግሥ ሲነግሥ በተወለደበት ሥፍራ በእለቱ ብቅ አለ፡፡
ቤተሰቦቹም የልጃቸውን መምጣት ተመልክተው አንድ ሰንጋ በሬ አርደው በደስታ ተቀበሉት፡፡
ገብረ ማሪያም ከዘመዶቹ ጋር ጥቂት ቀናት ካሳለፈ በኋላ ወደ ፊታውራሪ ዘመንፈስ ቅዱስ ዘንድ ተመልሶ የጀመረውን ትምህርት አጠናቀቀ፡፡
የገብረ ማሪያም እናት ግን የአገምጃ ተወላጅ ወደሆኑትና ገብረ ማሪያም በልጅነት ወደሚያውቃቸው ወደ በጅሮንድ ባልቻ ሳፎ ዘንድ ወስደው እዚያው እንዲያገለግል አደረጉት፡፡
በጅሮንድ ባልቻ ሳፎ በጊዜው የቤተ መንግሥቱ በጅሮንድ (የግምጃ ቤት ሹም) ነበሩ፡፡
በጅሮንድ ባልቻም፤ ገብረ ማሪያምን ታማኝ ወታደር ብቻ ሳይሆን ብቁ አስተዳዳሪም እንዲሆን አደረጉት፡፡
በፈረስ ጉግስ ጨዋታ ዝነኛ የነበረው ገብረ ማሪያም ጋሪ፤ አባ ንጠቅ የተባለውን የፈረስ ሰም ያገኘው በዚያን ጊዜ ነበር፡፡

2. በዐድዋ ዘመቻ ስለመካፈል


በ1888 ዓ.ም. ገና የ22 ዓመት ወጣት የነበረው ገብረ ማሪያም ጋሪ ከበጅሮንድ ባልቻ ሳፎ ሠራዊት ጋር ወደ ዐድዋ ዘመተ፡፡
የካቲት 23 ቀን 1888 ዓ.ም. እሁድ ጧት ጎህ ሲቀድ የበጅሮንድ ባልቻ ጦር ከፋሽስት ኢጣሊያ ጦር ጋር ውጊያ ሲጀምር ገብረ ማሪያም ጋሪም አብሮ ተሰለፈ፡፡
በዚህም ውጊያ መሐል በጅሮንድ ባልቻ እና አንደኛው ወንድማቸው ሲቆስሉ አንደኛው ግን ሕይዎቱ አልፏል፡፡
ወጣቱ አርበኛ ገብረ ማሪያም ጋሪ ግን ከጦርነቱ ተርፎ የአድዋው ድል ተቋዳሽ በመሆን ከድል አድራጊው ከዳግማዊ ምኒልክ ሠራዊት ጋር በድል ተመልሷል፡፡
ይህም የዐድዋ ጦርነት ተጋድሎ ገብረ ማሪያም ጋሪን የፊታውራሪነት ማዕረግ ሊያሰጠው ችሏል፡፡

3. ከዐድዋ ዘመቻ መልስ


ከዐድዋ ድል በኋላ ደጃዝማች ባልቻ ሳፎ የሲዳሞ ገዥ ሆነው ሲሾሙ ፊታውራሪ ገብረ ማሪያምም አብረው ከሄዱ በኋላ የባልቻ ሳፎ ልዩ ረዳት በመሆናቸው የአውራጃ ገዥነት ሹመት አግኝተው ሲያገለግሉ ቆዩ፡፡
ዳግማዊ ምኒልክ ሕመም እየፀና ከሄደ በኋላ ልጅ እያሱ ሥልጣኑን ሲረከቡ የአድዋ ዘመቻ ባለድል የነበሩትን ደጃዝማች ባልቻ ሳፎንና አብረዋቸው የነበሩትን ፊታውራሪ ገብረ ማሪያም ጋሪን ከሲዳሞ አስነስተው ከመንግሥታዊ ሥራ ውጭ አደረጓቸው፡፡
ከዚያ በኋላ ፊታውራሪ ገብረ ማሪያም ጋሪም ወደ ትውልድ አገራቸው ወደ አገምጃ በመመለስ ለ 25 ዓመታት ከተለዩዋቸው ቤተሰቦቻቸው ጋር በመቀላቀል እርስታቸው ላይ በግብርና ሥራ ከመስራታቸውም በላይ ለአካባቢያቸው የልማትና የአስተዳደር በርካታ ሥራዎችን አበርክተዋል፡፡
ልጅ እያሱ ከሥልጣናቸው መነሳታቸውን ተከትሎ በወሎው ንጉሥ ሚካኤልና በመንግሥት ጦር መካከል በተደረገው ጦርነት ፊታውራሪ ገብረ ማሪያም ከመንግሥት ወገን ሆነው ተዋግተዋል፡፡
ንግሥተ ነገሥታት ዘውዲቱና በ አልጋ ወራሽ ልዑል ራስ ተፈሪ መኮንን (በኋላ ንጉሠ ነገሥት ቀዳማዊ ኃይለሥላሴ) መካከል ተከስቶ የነበረው የሥልጣን ትንቅንቅ የዳግማዊ አፄ ምኒልክና የንግሥቲቱ ደጋፊ የነበሩትን ደጃዝማች ባልቻን አላስደሰተም ነበር፡፡
ልዑል አልጋ ወራሽ ተፈሪ መኮንንም የደጃዝማች ባልቻን መኳንንቶችና ባለሟሎችን እያስከዱ ወደእርሳቸው ማምጣት ጀመሩ፡፡
ደጃዝማች ባልቻን በጣም የጎዳቸው ግን የቅርብ አጋራቸው የሆኑት ፊታውራሪ ገብረ ማሪያም እርሳቸውን ከድተው ወደ ራስ ተፈሪ መሄዳቸው እንደነበር ይነገራል፡፡
ከዚህ በኋላ ፊታውራሪ ገብረ ማሪያም ወደ ቤተ መንግሥት ከመጡ በኋላ የልዑል አልጋ ወራሽ ተፈሪ መኮንን አገልጋይ በመሆን አጋፈሪ ሆነው ተመደቡ፡፡ የአጋፋሪነት ማዕረግ በአሁኑ አጠራር የፕሮቶኮል ሹም እንደማለት ነው፡፡
የልጅ እያሱ ከሥልጣን መውረድ ያላስደሰታቸው የወሎው ንጉሥ ሚካኤል በንግሥተ ነገሥታት ዘውዲቱ መንግሥት ላይ ጦርነት ሲያውጁ፤ ፊታውራሪ ገብረ ማሪያም ጋሪ ከመንግሥት ጦር ጋር ተቀላቅለው ተዋግተው ቆስለዋል፡፡

4. በሐረርጌ ጠቅላይ ግዛት የፈፀሟቸው ተግባራት


ንግሥተ ነገሥታት ዘውዲቱ ምኒልክ መጋቢት 24 ቀን 1922 ዓ.ም. ከዚህ ዓለም በሞት ከተለዩ በኋላ ግንቦት 20 ቀን 1922 ዓ.ም. ፊታውራሪ ገብረ ማሪያም ጋሪ የደጃዝማችነት ማዕረግ ተሰቷቸው የሐረርጌ ጠቅላይ ግዛት እንደራሴ ሆነው ተሸሙ፡፡
ደጃዝማች ገብረ ማሪያም ጋሪ የሐረርጌ ጠቅላይ ግዛት እንደራሴ በነበሩበት ጊዜ የኢጣሊያ መንግሥት በ1900 ዓ.ም. ከኢትዮጵያ መንግሥት ጋር የነበረውን ውል በማፍረስ በሶማሊያ የኢጣሊያ ግዛት ውስጥ የነበሩትን ወታደሮቹን በማንቀሳቀስ ወደ ኦጋዴን በማስገባት ግዛቱን ለማስፋፋት ይጥር ነበር፡፡
ይህን ሁኔታ የተረዱት ደጃዝማች ገብረ ማሪያም ጋሪ በሐምሌ ወር 1923 ዓ.ም. በጅጅጋ ከሚገኘው ጠቅላይ የጦር ሠፈራቸው 3,000 ወታደሮቻቸውን ይዘው በአካባቢው ሠርጎ ገብቶ የነበረውን የኢጣሊያ ኃይል በውጊያ እየተፋለሙ ካፀዱ በኋላ ከአካባቢው ሹማምንቶችና ነዋሪዎች ጋር ሠላማዊ ውይይት በማካሄድ ሥፍራው የኢትዮጵያ ግዛት መሆኑን አረጋግጠው ተመልሰዋል፡፡
ከዚህም በኋላ በኦጋዴን በሚገኘው ሰፊ መሬት 12 ከተሞችን በማቋቋም አስተዳዳሪዎችን እና ፀጥታውን የሚያስከብሩ ወታደሮችን ከመደቡ በኋላ ከተሞችን እርስ በርስ የሚያገናኙ መንገዶችን አሠርተዋል፡፡
ሆኖም የደጃዝማች ገብረ ማሪያም ጋሪን መልካም ተግባር ያልወደዱላቸው አንዳንድ መኳንንቶች በምቀኝነት ተነሳስተው ያልተገባ ክስ ለንጉሠ ነገሥቱ በማቅረብ ከቦታቸው እንዲነሱ ጎትጉተው ከሐረርጌ ሹመታቸው እንዲነሱ አስደርገዋል፡፡
ንጉሰ ነገሥቱ ቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ ወደ ሐረርጌ በመጓዝ በደጃዝማች ገብረ ማሪያም ጋሪ ምትክ ልጃቸውን ልዐል መኮንንን መስፍነ ሐረር አድረገው በሾሙበት ወቅት፤ የአገር ሽማግሌዎች፣ ባላባቶች፣ መኳንንቶችና ብዙ ሕዝብ በተሰበሰበበት ደጃዝማች ገብረ ማሪያም ጋሪ የፈፀሙትን ከፍተኛ ተግባር አስመልክተው ሲናገሩ፤
“አሁን በአደባባይ ጠርተን የምናናግርህ ሙያህን ለሕዝብ ለመግለጽ ነው፡፡ እኛ አገልግሎትህን ከጥንት ጀምሮ እናውቀዋል፡፡ (አገልግሎትህን) ሁሉ ስላልተረዳው እናዝናለን፡፡ ገና ስራ ስንጀምር አብረህ ሳትለይ፤ የማለዳውን ቁር እና የቀትሩን ፀሐይ ሳታዳምጥና ሳትበገር ዘብ ሆነህ ከዚህ ደርሰናል፡፡ በሐረር ጠቅላይ ግዛት ወሰኖች ብዙ ችግር እንደገጠመን ተገልጿል፡፡ አንዳንድ ቅን ሀሳብህን ያልትረዱልህ ሰዎች ባይመስላቸውም ስላላወቁልህ እናዝናለን፡፡ ከፊታቸው ስናመሰግንህ ለውለታህ የሚበዛበት አይደለም፡፡”
ካሉ በኋላ የኢትየጵያን የወርቅ የክብር ኮከብ ኮርዶን ኒሻን በአንገታቸው ላይ አጥልቀውላቸዋል፡፡
ከዚህ በኋላ ደጃዝማች ገብረ ማሪያም ጋሪ የሐረርጌ ጠቅላይ ግዛት እንደራሴነትን ለልዑል መኮንን አስረከቡ፡፡ እርሳቸውም የአገር ግዛት ምኒስትርነት ሹመት ከተሰጣቸው በኋላ በርካታ ሥራዎችን መሥራታቸው ይነገራል፡፡

5. የደጃዝማች ገብረ ማሪያም ጋሪ የአርበኝነት ተግባር


መስከረም 25 ቀን 1928 ዓ.ም. የኢጣሊያ ፋሽስት ወራሪ ኃይል ዳግም በሰሜን ኢትዮጵያ በሦስት አቅጣጫ ማለትም፤ በዐድዋ፣ በአዲግራትና በእንጢጮ ወረራ ሲፈጽም፤ በደቡብ ኢትዮጵያ አቅጣጫም እንዲሁ በዶሎ እና በምሥራቅ ኢትዮጵያ በኦጋዴን በኩል በታንክ፣ በመድፍና በአየር ወረራ ፈፀመ፡፡
በዚህን ወቅት ደጃዝማች ገብረ ማሪያም ጋሪ በ62 ዓመት የአዛውንት እድሜያቸው በሰሜን በኩል በቆቦ አቅጣጫ ከተሰለፈው የኢትዮጵያ ጦር ጋር በመሆን በተደረገው ጦርነት የጠላትን የተዘጋ መተላለፊያ አስከፍተዋል፡፡
ከዚያ በኋላም ደጃዝማች ገብረ ማሪያም ጋሪ በንጉሠ ነገሥቱ ትእዛዝ፤ ወንድሞቻቸውን፣ መኳንንቶቻቸውንና ወታደሮቻቸውን ይዘው ወደ ደቡብ ግንባር ወደ ሲዳሞ በመጓዝ የራስ ደስታ ዳምጠው ጦር ረዳት በመሆን የአርበኝነት ተጋድሏቸውን ቀጠሉ፡፡
ግንቦት 10 ቀን 1928 ዓ.ም ድኑን በተባለው ስፍራ ላይ ደጃዝማች ገብረ ማሪያም ጋሪ፤ በታላቅ ወንድማቸው በቀኛዝማች ኡርጋ ጋሪ፣ በሻቃ በቀለ ወያ እና በፊታውራሪ ተሰማ አብዲ በመታገዝ በሁለት አቅጣጫ በጠላት ጦር ላይ ጥቃት በመክፈት ከፍተኛ ድል ተቀዳጅተዋል፡፡
ሻቃ በቀለ ወያ የደጃዝማች ገብረ ማርያምን የመድፈኛ ቡድን ፊት ለፊት እየመራ በበዳና፣ አቄሮና ሶዶ በረሃ ሲጓዝ፤ በደጃዝማች ገብረ ማርያም ላይ ይተኩስ የነበረውን የጠላት ጦር አውድመውታል፡፡
በዚህም ጦርነት በርካታ በውሃ የሚሰሩ መድፎችና 14 ቀላል የአልቢን መሣሪያዎችን ሲማርኩ፣ 30 የጠላት ጦር አዛዦችና በርካታ ወታደሮችንም ጭምር ማርከዋል፡፡
ጀግናው አርበኛ ደጃዝማች በቀለ ወያ
ይህን የጀግንነት ሥራቸውን የተመለከቱት ደጃዝማች ገብረ ማርያም ለበቀለ ወያ የተለየ አድናቆታቸውን ሰጥተዋቸዋል፡፡
ከሰኔ እስከ መስከረም ወር 1928 ዓ.ም. ድረስ ዳባ ሴሬ በተባለው አውደ ውጊያ ላይ ከጠላት ጦር ጋር ከባድ ጦርነት አካሂደዋል፡፡
በዚህ ውጊያ ላይ ደጃዝማች ገብረ ማርያም ጋሪ ሲቆስሉ ጀግናው በቀለ ወያ ድግሞ 12 የጠላት ታንኮችን ከጥቅም ውጭ በማድረግ ታላቅ የጀግንነት ትግባራትን ፈጽመዋል፡፡
ደጃዝማች ገብረ ማርያም ጋሪ በተከታታይ ውጊያዎች በአኩሪ ጀግንነት ከጠላት ጦር ጋር በመፋለም ላይ እያሉ ጎጌቴ በተባለው ሥፍራ በተካሄደው ከባድ ጦርነት ላይ የካቲት 13 ቀን 1929 ዓ.ም. በተወለዱ በ63 ዓመታቸው ሕይዎታቸው ሊያልፍ ችሏል፡፡
በደጃዝማች ገብረ ማርያም ሞት ምክንያት ሻቃ በቀለ ወያ ጀግና አጋራቸውን በማጣታቸው ከባድ ሀዘን ተሰምቷቸው እንደነበረ ይነገራል፡፡

በደጃዝማች ገብረ ማሪም ጋሪ ስም የተሰየመው የሊሴ ገብረ ማሪያም ትምሕርት ቤት የተቋቋመው በቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ ዘመነ መንግሥት በ1940 ዓ.ም. ነበር፡፡
የሊሴ ገብረ ማሪያም ትምሕርት ቤት
የፈረንሣይንና የኢትዮጵያን ወዳጅነት ለማጠናከር በ1939 ዓ.ም. ማሕበር ሲቋቋም፤ ትምህርት ቤቱም ሊሴ ገብረ ማሪያም ተብሎ ተሰየመ፡፡
ደጃዝማች ገብረ ማሪም ለሀገራቸው ነፃነት ሲሉ ያደረጉትን ታላቅ የአርበኝነት ተጋድሎ ለማስታዎስ ሲሉ ንጉሠ ነገሥቱ ቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ የፈረንሳይ ትምሕርት ቤቱ በስማቸው እንዲጠራ አድርገዋል፡፡
ትምህርት ቤቱ እንደተከፈተም በመጀመሪያ ይማሩበት የነበሩት የአርበኞችና የስደተኞች ቤተሰቦች ልጆች ነበሩ፡፡
የአቢሲንያ ባንክም የአንዱ የባንክ ቅርንጫፍ በስማቸው እንዲሰየም አድርጓል፡፡


ምንጭ፤
  1. ምስጋና፤ ለሸገር ትዝታ ዘአራዳ - ተራኪ፤ ተፈሪ ዓለሙ  
     --› ዩቲውብ ሊንክ ክፍል 1
     --› ዩቲውብ ሊንክ ክፍል 2
  2. የትረካው አጃቢ ሙዚቃ፣ ዋሽንት - በአንሙት ክንዴ   ዩቲውብ