Content-Language: am ግርማዊ ቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ ገጽ አራት
header image


(ድረ ገጽ 4)

ግርማዊ ቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ




ፋሽስት ኢጣሊያ ኢትዮጵያን በጦር ኃይል አምበርክኮ ለመግዛት እንደማያዛልቀው በማመኑ የተለያዩ ከፋፋይ ተግባራትን ተጠቅሟል፡፡
የኢትዮጵያን ሕዝብ በዘር፣ በሐይማኖትና በቋንቋ ከፋፍሎ እርስ በርስ እያዋጋ ለመግዛት በርካታ ድርጊቶችን ፈጽሟል፡፡
የፋሽስት ኢጣሊያ ወረራ ዋና ዓላማ፣ የኢትዮጵያን ሕዝብ እርስ በርሱ አፋጅቶ በመጨረስ የራሱን ሕዝቦች ኢትዮጵያ ለማስገባት እቅድ ነበረው፡፡
በዚህም ምክንያት ዕቅዱን ለማሳካት ሲል፤ ክርስቲያኑን በሙስሊሙ ላይ፣ አማራውን በኦሮሞው ላይ፣ አዳሉን በሶማሌው ላይ፣ የተማረውን ባልተማረው ላይ ከማስነሳቱም በላይ፤ የኦሮሞን ወታደር ወደ አማራው አገር፣ የአማራውን ወታደር ወደ ኦሮሞው አገር፣ የኤርትራውን ወታደር ወደ ሸዋ በመላክ እርስ በርሱ እያጣላና እያዋጋ ኖሯል፡፡
ሌላው ቀርቶ፤ በቤተ ክርስቲያን አጠገብ መስጊድ፤ በጳጳሱ መኖሪያ አጠገብ የሙስሊም ቃዲ እያስቀመጠ እርስ በርስ እያቃቃረ ለማጣላት ያልፈነቀለው ድንጋይ የለም፡፡

ጣሊያኖች ሕዝቡ እርስ በርሱ መጣለት አለመቻሉን ሲመለከቱ ሌላ የማባቢያ መንገድ ቀየሱ፡፡
በአትዮጵያ መንግሥት በክብር ይሰጡ የነበሩትን፤ የራስነት፣ የደጃዝማችነትና የፊታውራሪነት የማዕረግ ስሞች ለማይገባው ሰው ሁሉ መስጠት ጀመሩ፡፡
ጥቁር ሰው ለመቅረብ ይጠየፉ የነበሩት ጣሊያኖች፤ መኖሪያ ቤታቸው ድረስ እየጠሩ አብረው እየበሉና እየጠጡ በደስታውም በሐዘኑም ተካፋይ መሆን ጀመሩ፡፡
ፊት ለፊት የሚዋጓቸውን አርበኞችን፤ አንዳንዶቹን በዘመዶቻቸው በኩል በማባበል እያቀረቡ ልብስ እያለበሱ፤ መትረየስና ሽጉጥ እያስታጠቁ፤ የሚንሸራሸሩበት የግል አውቶሞቢል እየሰጡ የአርበኛውን ልብ ለማሸፈት ሞከሩ፡፡
የተወሰኑ መኳንንቶችን፣ ካህናቱን፣ ወጣቱንና ወይዛዝርቶችንም ሳይቀር እየመረጡ ሮም ድረስ በክብር እየወሰዱ ከተማቸውን በማሳየት፤ ያላቸውንም ኃያልነት እያስረዱና ከሙሶሎኒም ጋር በማገናኘት ልባቸውን በማሸነፍ፤ እንዲሁም በማይጨው ጦርነትና ግራዚያኒን ለመግደል ተወስዶ በነበረው እርምጃ የተፈጠረውን የጠላትነት ቁስልና ቂም በመሻር ያለምንም ተቃውሞ በሰላም እንዲገዙላቸው የሚቻላቸውን የስነልቦና ዘዴ ተጠቅመዋል፡፡
ይህን ሁሉ የማባበል ዘዴ ሊጠቀሙ የፈለጉበት ምክንያትም፤ በየቦታው የተበተነው አርበኛውና በውጭም ያለው ስደተኛ እውነት መስሎት ተመልሶ ሲገባላቸው፤ የተለመደውን የጭካኔ ተግባር በመፈፀም ድብቅ ዓላማቸውን እውን ለማድረግ እንጅ የኢትዮጵያውያን ደህንነትና ክብር አሳስቧቸው አልነበረም፡፡
ይህም የፋሽስት ስውር ወጥመድ በኢትዮጵያውያን አርበኞችና በሕዝቡም ዘንድ የተደበቀ ጉዳይ አልነበረም፡፡
ፋሽስት ኢጣሊያ የአርበኞችን ስነ ልቦና ለመስለብ ይጠቀምባቸው የነበሩት የማታለል ዘዴዎች ሁሉ፤ በኋላ ላይ ለኢጣሊያ ተገዥ የነበሩትና ለእነርሱ ይሠሩ የነበሩት መኳንንቶችና ወጣቶች ወደ ልቦናቸው መመለስ ሲጀምሩ በእርግጥ ለአገር መሥራት በስተመጨረሻ ምን ያህል እንደሚያስከበር እየተገነዘቡ ሲሄዱ አገር ወዳድ አርበኞችም ልባቸውና ሞራላቸው እየበረታ መጣ፡፡
ለጥቅም ከተሸነፉት ከጥቂት ባንዳዎች በስተቀር፤ አብዛኛው የኢትዮጵያ ሕዝብ ግን በተቃራኒው በአንድነት በመቆም የፋሽስት ኢጣሊያ ሴራን ለማክሸፍ፤ በዘር፤ በሐይማኖትና በቋንቋ ሳይከፋፈል፤ አገሩን ከጠላት ነፃ ለማውጣት፤ በከተማም፣ በገጠርም፣ ከትልልቅና ከትንንሽ አውራጃዎች ሳይቀር በሚኖርበት አካባቢ፤ ገበሬውም፣ ነጋዴውም፣ የአስተዳደር ሠራተኛውም፣ ወታደሩም፣ የቤተ ክህነት ሰዎችም፤ ወንድ ሴት ሳይል ሁሉም አለቃና ጭፍራ እየመረጠና እየተደራጀ በዱርና በጫካው ሁሉ ተደብቆ ጠላትን በአርበኝነት መውጫ መግቢያ እያሳጣ ይዋጋ ነበር፡፡

Gojam Patriots wounded and killed in during fighting




የውስጥ አርበኞች የተለያዩ መረጃ የመሰብሰብ ዘዴዎች ይጠቀሙ ነበር፡፡
ወደ ጠላት ጦር ተጠግተው በማድፈጥ የጠላትን ጦር እንቅስቀሴ የሚሰልሉ ቃፊሮች ነበሯቸው፡፡
የውስጥ አርበኞች፤ ከጠላት ጋር አብረው እየዋሉና እያደሩ፤ የጠላትን ጦር ጥንካሬና ድክመት፤ እንዲሁም የታቀዱ ዘመቻወችንም ሆነ ወታደራዊ እንቅስቃሴዎችን በተመለከተ እየሰለሉ ለኢትዮጵያ አርበኞች በቅድሚያ እንዲደርሳቸው ያደርጉ ነበር፡፡
አልፎ ተርፎም ጠላት በሚጠቀምበት አስተዳደር ውስጥ የተሰጣቸውን ኃላፊነት በመጠቀም ለአርበኞች የውሸት የይለፍ መታወቂያ ወረቀት በማውጣት አርበኞች የሚፈልጉትን መረጃ እንዲያገኙ ረድተዋል፡፡
መጠጊያ ላጡና ጠላት ለሚያሳድዳቸው አርበኞችም መሸሸጊና መደበቂያ ያዘጋጁላቸው ነበር፡፡

የውስጥ አርበኞች የሚሰማሩት መረጃ በማቀበል ሥራ ላይ ብቻ አልነበረም፡፡
ማንነታቸውንም በመደበቅ የጠላትን ተቋማት በማፍረስ የሽብር ተግባር ላይ ጭምር ይሠማሩ ነበር፡፡
ለእነደዚህ አይነቱ ተግባር፤ በተለይ ሴቶች ሰለማይጠረጠሩ ከወንዶች ይልቅ የላቀ ሥራ ይሠሩ ነበር፡፡
በዚህ ረገድ ከፍተኛ ዝና ያተረፈችውና የጠላት ጦር እንዲደመሰስ ሁኔታዎችን በማመቻቸት የጀግንነት ተግባር የፈፀመችው የሴት የውስጥ አርበኛዋን ወይዘሮ ሸዋረገድ ገድሌን መጥቀስ ይቻላል፡፡
የመከላከያ ሚኒስቴር ባዘጋጀው ይፋዊ ሰነድ መሠረት ጥር 17 ቀን 1937 ዓ.ም. ከቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ እጅ የሜዳሊያ ሽልማት ያገኙትን 277 የሴት አርበኞችን ዝርዝር አካቶ አውጥቷል፡፡
ሽልማቱን ያገኙት ብቻ ወሳኝ ሚና ተጫውተዋል ማለት አይደለም።
ስፍር ቁጥር የሌላቸው ሴቶች ለሀገራቸው ነፃነት ሲሉ በውጊያ መስመር በመሰለፍና በውስጥ አርበኝነት ጭምር በርካታ የአርበኝነት ተጋድሎ አድርገዋል።
ሴቶች ለነፃነት ትግሉ ያበረከቱት አስተዋፅኦ ከፍተኛ እንደሆነ የጽሑፍም ሆነ የቃል ምንጮች ይስማማሉ፡፡
በተለይ በፋሽስት ወረራ ወቅት በዋነኝነት በከተማና በገጠር የውስጥ አርበኝነት ሥራ ላይ በመሰማራት ለአርበኞች ያደረጉት አስተዋፅዖ በምንም መልኩ ከተዋጊ ወታደሮች ያነሰ አልነበረም፡፡
በድብቅ የሚካሄደው የአርበኝነት ሥራው የሚሠራው በተደራጀው “የውስጥ አርበኞች ማዕከላዊ ኮሚቴ” አማካኝነት ነበር።
በተለይም የውስጥ አርበኞች ሴቶች አባላት ለተዋጊ አርበኞች፤ ምግብ፣ ልብስ፣ ባሕላዊ መድኃኒቶች፣ ጥይቶችና የእጅ ቦንቦችን ሳይቀር ከማቅረብ አኳያ ሰፊ አገልግሎት የሰጡ ሲሆን ከሁሉም በላይ የስለላ መረጃ በማቀበል ረገድ ሰፊ ሚና ተጫውተዋል፡፡
ሌላው ቀርቶ ሴቶቹ ከኢጣሊያ ወታደሮች እና ከከፍተኛ የኢጣሊያ መኮንኖች ሳየቀር በሴትነታቸው አባብለውና ወዳጅ መስለው የጦር መሣሪያወችን በመስረቅ እና የጦር መሣረያዎችና ጥይቶች ማከማቻ ቦታወችን እየሰለሉ ያሉበትን ቦታ በመጠቆም አርበኞች በደፈጣ ውጊያ ወረው መሣሪያወቹን እንዲወስዱ ከፍተኛ እገዛ አድረገዋል፡፡
መሳሪያዎችን ለአርበኞቻቸው የሚያስተላልፉበት መንገድም እጅግ የሚደንቅ ነበር፡፡
የጠላት የፍተሻ ኬላዎችን ለማለፍ ሲፈልጉ ይጠቀሙባቸው የነበሩት ዘዴዎች ለምሳሌ፤
መሣሪያዎችን በአልጋ ላይ አስቀምጠውና ልብስ አልብሰው በወንዶችና በሴቶች ለቅሶ ታጅበው የሞተ ሰው ለቀብር የሚወስዱ በማስመሰል፣
ከወንዝ ውሀ ለመቅዳት የሚሄዱ መስለው ጥይቶችን በእንስራቸው ከተው በመወሰድ እና እንዲሁም
በከብቶች እበት ውስጥ ጠፍጥፈው በማድረቅና የደረቀ የማገዶ ኩበት የተሸከሙ በማስመሰል፣
ድንቅ ትግባራትን ፈጽመዋል፡፡
በዱር በገደሉ የመሸጉት የኢትዮጵያ አርበኞች፤ ከኢትዮጵያ የውስጥ አርበኞች ጋር በመቀናጀት፣ ርሃብና እርዛት ሳይበግራቸው፣ በየበረሀው እና በየሸለቆው ተንከራተው ለአምስት ተከታታይ ዓመታት በቁርጠኝነት ለኢትዮጵያ አርነት ከወራሪው ፋሽስት ኢጣሊያ ጋር ያደረጉት ትንቅንቅ፣ ተጋድሎና የከፈሉት መስዋዕትነት ሲታይ፤ በዘመናዊ የኢትዮጵያ ታሪክ ውስጥ፤ ለመጭው ትውልድ ሁሉ ታላቅ አርዓያ የሚሆን እጅግ አኩሪ ገድል ሆኖ ሲዘከር የሚኖር ታላቅ ተግባር ሆኖ አልፏል፡፡


mussolini-and-Hitler
ሙሶሎኒ እና ሂትለር

Photo credit to: theweek
የኢጣሊያ መንግሥት ወደ ሁለተኛው የዓለም ጦርነት መግባቱ ለኢትዮጵያ መንግሥት የነፃነት በር ከፈተ፡፡
በሰኔ ወር 1932 ዓ.ም. ሙሶሎኒ የሂትለር አጋር በመሆን ወደ ሁለተኛው የዓለም ጦርነት ሰተት ብሎ በመግባቱ ከፍተኛ ስህተት ፈፀመ፡፡
በዚህም ምክንያት የሂትለር ተቀናቃኝ የሆኑትን የእንግሊዝንና የፈረንሳይን አጋርነት አጣ፡፡
በተለይም እንግሊዞች፤ ሙሶሎኒ የሂትለር አጋር በመሆኑ፤ በምሥራቅ አፍሪካ የቅኝ ግዛቶቻቸው ላይ ያንዣበበ አደጋ መሆኑን ተረዱ፡፡
የኢጣሊያ ጽኑ ወዳጅ የነበረችው እንግሊዝም አፍታም ሳትቆይ ወዲያውኑ በኢጣሊያ ላይ ወደ ቀንደኛ ጠላትነት ተለወጠች፡፡
ከዚህ በኋላ ችላ ተብሎ የነበረው የኢትዮጵያ ጉዳይ እንደገና ተቀስቀሶ ለንደን ላይ በኢትዮጵያ ንጉሠ ነገሥትና በእንግሊዝ መንግሥት መካከል የጋራ የጦር ህብረት እንዲኖራቸው ተስማሙ፡፡
Haile Selassie with Daniel Arthur Sandford and Colonel Wingate
ንጉሠ ነገሥቱ ማክሰኞ
ሚያዝያ 7 ቀን ጐጃም
ከገቡ በኋላ 1933 ዓ.ም.
በግራ፤ከጀነራል ስታንፈርድ
በቀኝ፤ ከኮሎኔል ዊንጌት ጋር
ስለጦር ዕቅድ ሲወያዩ
እንግሊዞችም፤ በኢጣሊያ ላይ ኢትዮጵያውያንን ሊያስተባብሩላቸው የሚችሉት፤ የኢትዮጵያው ንጉሠ ነገሥት ግርማዊ ቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ መሆናቸውን ስላመኑ ከእንግሊዝ የጦር መሪዎችና ወታደሮች ጋር ሆነው ከስደት ወደ አገራቸው እንዲመለሱ አመቻቹላቸው፡፡
በዚህም መሠረት የእንግሊዝ መንግሥት የግርማዊ ቀዳማዊ አፄ ኃይለ ሥላሴን ንጉሠ ነገሥትነት ተቀብሎ፤ ንጉሠ ነገሥቱን ወደ ቀድሞ ዙፋናቸው ለመመለስ ፈቃደኛ በመሆኑ፤ ንጉሠ ነገሥቱ፤ በሐምሌ ወር 1932 ዓ.ም. ከሌፍትናንት ጀነራል ዊሊያም ፕላት ጋር ተገናኝተው የፋሽስት ጦርን ከኢትዮጵያ ለማሶጣት የሚቻልበትን መንገድ ለመወያየት ወደ ሱዳን አመሩ፡፡
በዚህም መሠረት ንጉሠ ነገሥቱ በ1933 ዓ.ም. በጥቅምት ወር መጨራሻ ላይ፤
  1. የእንግሊዝ ጠቅላይ ሚኒስትር ዊኒስተን ቸርችል አማካሪ የሆነው የደቡብ አፍሪካው ጀነራል ሰመት፣
  2. የሕንድ ተጠሪና ገቨርነር ጀነራል የሆነው አርኪባልድ ዋቬል፣
  3. ሌፍትናንት ጀነራል ዊሊያም ፐላት እና
  4. ሌፍትናንት ጀነራል አለን ካኒንግሃም
በተገኙበት ስብሰባ አካሂደው ወደ ኢትዮጵያ ስለሚደረገው ዘመቻ ተወያዩ፡፡
ሌፍትናንት ጀነራል ዊሊያም ፕላት ሱዳን ውስጥ የነበረውን “የኢጣሊያ ምስራቅ አፍሪቃ” የተሰኘውን የፋሽስት ኢጣሊያ ጦር ለመውጋት የተደራጀው የዘመቻ ክንፍ አዛዥ ነበር፡፡
ጀነራል ፕላትና ኮሎኔል ስታንፈርድም፤ ግዳጅ 101 (mission 101) የተሰኘውን ቀዳሚ ጦር በመላክ ባህር ዳር፣ ዳንግላና ደብረ ማርቆስ ተከማችቶ የነበረውን የፋሽስት ጦር በጎጃም ካሉት አርበኞች ጋር በመቀናጀት ወግቶ በማሶጣት፤ ንጉሠ ነገሥቱ በጥቅምት ወር 1933 ዓ.ም. አዲስ አበባ እንዲገቡ ዕቅድ አወጡ፡፡
Patriots Attacking the Enemy Fort at Derba Marcos
የጎጃም አርበኞች ደብረ
ማርቆስ የመሸገውን የፋሽስት
ጦር ለማስለቀቅ ሲዋጉ

Photo link
ንጉሠ ነገሥቱ የእንግሊዝ ጦርን ይዘው ወደ አገር ቤት ሊመለሱ መሆኑ ሲሰማ፤ በኢጣሊያ መንግሥት ላይ ከፍተኛ ድንጋጤን ፈጠረ፡፡
እንግሊዞች ኢትዮጵያ በሚገኘው የኢጣሊያ ጦር ላይ ጦርነት የከፈቱት ከሱዳንና ከኬንያ ግዛት በኩል ነበር፡፡
በሜጀር ጀነራል ዊሊያም ፕላት የሚመራው ጦር በኤርትራ የሚገኘውን የኢጣሊያን ጦር እንዲያጠቃ ተደረገ፡፡
በኮሎኔል ስታንፈርድ እና በሻለቃ ዊንጌት የሚመራው የጌዲዎን ጦር የተሰኘው ደግሞ፤ ከሱዳን ተነስቶ 600 ኪሎ ሜትር በመጓዝ ንጉሠ ነገሥቱን አጅቦ ጎጃም መግባት ቻለ፡፡
በኢትዮጵያ ደቡብ አቅጣጫ ደግሞ በሌፍትናንት ጀነራል ሰር አለን ካኒንግሃም የሚመራው የእንግሊዝና የሶማሊያ ቅኝ ግዛት ጦር፤ ከእንግሊዝ ቅኝ ግዛት ከሆነችው ሶማሊያ ተነስቶ ወደ ኢጣሊያ ሶማሌላንድና ወደ ሐረር ጉዞ ጀመረ፡፡
በዚህ የጦርነት የውጊያ አቅጣጫ፤ በተለይ ከረንን ለመያዝ እንገሊዞች ብዙ መስዋዕትነትን ከፍለዋል፡፡
ሆኖም የአምስት አመቱ ያልተቋረጠ የአርበኞች ትግል ያመነመነው የጠላት ጦር ሳይወድ በግድ የሽንፈት ጽዋ ለመቅመስ ተገደደ፡፡

ንጉሠ ነገሥቱም ከ 4 ዓመት ከ 8 ወር የስደት ቆይታ በኋላ በጥር 1932 ዓ.ም. ከለንደን ተነስተው በሰኔ ወር ማለቂያ ላይ ከተከታዮቻቸው ጋር ሆነው ሱዳን ዋና ከተማ ካርቱም ገቡ፡፡
ንጉሠ ነገሥቱ ካርቱም ከገቡ በኋላ ባደረጉት ንግግር፤
"...ኢጣሊያ ከጀርመን ጋር ተባብራ፤ በታላቋ ብሪታንያና በፈረንሳይ መንግሥታት ላይ ጦርነት ስለከፈተች፤ እነርሱም እርዳታቸውን ስለሰጡን የተመኘነውን አግኝተን ደርሰንላችኋል፡፡
ከእንግዲህ ወዲያ የእንግሊዝና የፈረንሳይ የጦር አይሮፕላኖች በኢጣሊያ ግዛትና በኢትዮጵያ ሰማይ ላይ ያንዣብባሉ፡፡
ስለዚህ የኢትዮጵያ አርበኞች ሰይፋችሁን ወደ ሰገባው ሳትከቱ፤ ፊታችሁን ከጠላት ላይ ሳትመልሱ፤ ሠንደቅ ዓላማችሁን ሳታጥፉ፤ ለባዕድ አንገዛም ብላችሁ ለአምስት ዓመታት በዱር በገደሉ ስትጋደሉ ቆያታችሁ፤ ይኸው አሁን የተጋድሏችሁና የመስዋዕትነታችሁን ፍሬ ለማየት በቅታችኋል፡፡”
የሚል መልዕክት በሬድዮ ለኢትዮጵያ አርበኞች አስተላለፉ፡፡

ንጉሠ ነገሥቱም ከካርቱም ተነስተው ጥር 10 ቀን 1933 ዓ.ም. ጌድዮን ከተሰኘው በሻለቃ ዊንጌት ከሚመራው ከእንግሊዝ ጦርና ከእንግሊዝ ቅኝ ግዛት አገሮች ከተውጣጣው ከአፍሪካ ልዩ ኃይል (African special force) ጋር በመሆን በሱዳንና በጐጃም ድንበር በምትገኘው ኦሜድላ ተብላ በምትጠራው ስፍራ ከደረሱ በኋላ የይሁዳ አንበሳ ያለበትን የኢትዮጵያ ሠንደቅ ዓላማ ሰቀሉ፡፡
Ethiopian patriates holding machine guns captured from the enemy
የኢትዮጵያ አርበኞች ከፋሽስት
ወታደሮች የማረኩትን ዘመናዊ
መሣሪያ በመያዝ የንጉሠ ነገሥቱን
አዲስ አበባ መግባት ሲጠባበቁ

Photo link
ወደ ደብረማርቆስ የሚሄዱበት ቀን እስኪወሰን ድረስ ኦሜድላ ጥቂት ቀናት ከቆዩ በኋላ የጦር ሠራዊታቸውን ይዘው በእንግሊዝ ታንኮች እየተረዱ ጠላትን በውጊያ እያባረሩ፤ መጋቢት 28 ቀን 1933 ዓ.ም. እሁድ ከሰዓት በኋላ በዘጠኝ ሰዓት ደብረማርቆስ ቤተ መንግሥት ገብተው የኢትዮጵያን ሠንደቅ ዓላማ ሰቀሉ፡፡
ከዚያ በኋላ በየአገሩ ለተሠማሩ አርበኞች የኢትዮጵያ ነፃነት መረጋገጡን በማስመልከት የደስታ መግለጫ ላኩ፡፡
በጀነራል ካኒንግሃም መሪነት ከደቡብ አቅጣጫ በሲዳሞ በኩል የመጣውም የታላቋ ብሪታኒያ ጦርና የኢትዮጵያ አርበኞች ጦር በጋራ ጠላትን በማጥቃት ድል አድርገው መጋቢት 28 ቀን 1933 ዓ.ም. አዲስ አበባ ሲገቡ የአዲስ አበባ ከተማ ከጠላት እጅ ነፃ መውጣቷን አረጋገጠች፡፡
ንጉሠ ነገሥቱ ከደብረ ማርቆስ ተነስተው በ 3ኛው ቀን ፍቼ ከተማ ገቡ፡፡
ንጉሠ ነገሥቱ ሚያዝያ 22 ቀን 1933 ዓ.ም. ፍቼ ሲገቡ፤ ራስ አበበ አረጋይ ፍቼ ድረስ በመሄድ በሰልፍ ተቀበሏቸው፡፡
በመጨረሻም ንጉሠ ነገሥቱ፤ ፍቼ ከተማ 2 ቀን ከቆዩ በኋላ፤ መኳንንቱን፣ የእንግሊዝ ጦር አዛዦችንና ወታደሮችን አስከትለው ሰኞ ጧት ሚያዝያ 27 ቀን 1933 ዓ.ም. ንጉሠ ነገሥቱ እንጦጦ ማርያም ቤተ ክርስቲያን በር ላይ ሲደርሱ ስመ ጥሩው ጀግና ክቡር ራስ አበበ አረጋይ ቁጥሩ 10 ሺህ የሚደርስ አርበኞቻቸውን አሰልፈው እጅግ የደመቀና የጋለ አቀባበል አድርገውላቸዋል፡፡
Emperor Haile Selassie entering his palace
ንጉሠ ነገሥቱ ከስደት
ከተመለሱ በኋላ አዲስ
አበባ እንደገቡ ወደ ታላቁ
ቤተ መንግሥት ሲያመሩ
ንጉሠ ነገሥቱም ከእንጦጦ ማርያም ተነስተው በግልጽ አውቶሞቢል ላይ ሆነው በነጭ ፈረስ ላይ በተቀመጠው በእንግሊዛዊው ኮሎኔል ዊንጌት፤ በጌድዮን ጦር እና በአርበኞች ታጅበው ወደ አዲስ አበባ ጉዞ ለመቀጠል ተዘጋጁ፡፡
በዚህን ጊዜ በእንግሊዛዊው ጀነራል ካኒንገሃም አማካይነት በሞተር ብስክሌቶችና በቀላል ታንኮች ላይ በመሆንና፤ በተጨማሪም ከደቡብ አፍሪካ የመጡ ወታደሮችና የፖሊስ ሠራዊት ፈረሰኞች ወደ እንጦጦ ተልከው ንጉሠ ነገሥቱን እንዲያጅቡ ከተደረገ በኋላ ንጉሠ ነገሥቱ በደማቅ ንጉሣዊ ክብር ታጅበው ወደ አዲስ አበባ ጉዞኣቸውን ቀጠሉ፡፡
ካኒንግሃምም የክብር ዘብ አሰልፎ የደስታ መግለጫ መድፍ እያስተኮሰ ደስ በሚያሰኝ ሥነሥርዓት ተቀበላቸው፡፡
Haile Selassie hoisting Ethiopian Flag
ንጉሠ ነገሥቱ ሚያዝያ 23 ቀን
1933 ዓ.ም. አዲስ አበባ ከገቡ በኋላ
በታላቁ ቤተ መንግሥት የኢትዮጵያን
ሠንደቅ ዓላማ ሲሰቅሉ
አዲስ አበባ ሲገቡ፤ የአዲስ አበባ ሕዝብ ከያለበት ነቅሎ ወጥቶ በታላቅ ስሜት ውስጥ ሆኖ ከእንጦጦ ጀምሮ እስከ ታላቁ ቤተ መንግሥት ድረስ ግራና ቀኝ ተሰልፎ የደስታ እንባ እየተራጨ፤ ወንዱ በሆታ፣ ሴቱ በልልታ፣ መኳንንቱ በጭብጨባና እጅ በመንሳት ወደር የሌለው ደስታውን ገልጾላቸዋል፡፡
ንጉሠ ነገሥቱም በሕዝባዊ ሠልፉ መሐል ተጉዘው ታላቁ ቤተ መንግሥት ከደረሱ በኋላ ከመኪናቸው ወርደው በቤተ መንግሥቱ ባልኮኒ ላይ ወጥተው ለሕዝቡ በታዩ ጊዜ በአደባባዩ ላይ የተሰበሰበው ሕዝብ፤ ከፍ ያለ የወዳጅነት አቀባበል አድርጐላቸዋል፡፡

Ethiopian patriates holding machine guns captured from the enemy
በንጉሠ ነገሥት ቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ ጥቅምት 13 ቀን
1937 ዓ.ም. ተመርቆ በአራት ኪሎ አደባባይ
የቆመው የሚያዝያ 27 የድል ሐውልት

Photo Credit to: addisababa.travel
ንጉሠ ነገሥቱ አዲስ አበባ ታጅበው ከገቡ በኋላ በታላቁ የዳግማዊ ምኒልክ ቤተ መንግሥት ተገኝተው የኢትዮጵያን ሠንደቅ ዓላማ በክብር በመስቀል አውለብልበዋል፡፡
የአናት ሀገራቸውን ነፃነት ለማስከበር ሲሉ ከፋሽስት ኢጣሊያ ወራሪ ጦር ጋር ተዋድቀውና መስዋዕት ሆነው ድልን ላጎናጸፉን ለውድ የኢትዮጵያ አርበኞች መታሰቢያ ይሆን ዘንድ ንጉሠ ነገሥቱ ቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ የአርበኞች የድል ቀን መታሰቢያ የሆነውንና “ሚያዝያ 27" በመባል የተሰየመውን የድል ሐውልት በማሠራት ጥቅምት 13 ቀን 1937 ዓ.ም. በኦፊሴላዊ ስነ ሥርዓት መርቀውታል፡፡


Emperor Haile Selassie in 1942
ግርማዊ ቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ
በ 1934 ዓ.ም.

Photo link
እንግሊዞች፤ ከራሳቸው ዓለም አቀፋዊ እስትራተጅክ ጠቀሜታ በመነሳት የተጫወቱት ግንባር ቀደም ሚና ኢትዮጵያ ነጻነቷን ከተቀዳጀች በኋላ በኢትዮጵያ ውስጥ የበላይነት እንዲቀዳጁ አድርጓቸዋል፡፡
ከ1928ቱ የኢጣሊያ ወረራ በፊት፤ በእንግሊዝ፣ በኢጣሊያና በፈረንሳይ መካከል ኢትዮጵያን ለመቆጣጠር የነበረው የሦስቱ አገሮች ፉክክር በእንግሊዝ ብቸኛ የበላይ ተቆጣጣሪነት ተተካ፡፡
ይህም የእንግሊዞች የበላይ ተቆጣጣሪነት ህጋዊ መሠረት ያገኘው፤ ኢትዮጵያ ከእንግሊዝ ጋር በ1934 እና በ1937 ዓ.ም. በተፈራረመችው ሁለት ሰምምነቶች አማካይነት ነው፡፡
ምንም እንኳን በመጀመሪያው የ1934ቱ ስምምነት መሠረት እንግሊዞች ለይስሙላ የኢትዮጵያን ነፃ ሕልውና ቢያውቁም፤ እያንዳንዱ የስምምነቱ አንቀጽ የኢትዮጵያን ጥገኝነትና የእንግሊዝን የበላይነት የሚያረጋግጥ ነበር፡፡
ለእንግሊዞች ህጋዊ መብት ከሰጣቸው የስምምነቱ አንቀጾችና ከስምምነቱ ውጭ ይፈጽሟቸው ከነበሩት ተግባራት መካከል ብንጠቅስ፤
  1. በኢትዮጵያ የተመደበው የእንግሊዝ አምባሳደር፤ ከሌሎች አምባሳደሮች ሁሉ የተለየ ስፍራ መሰጠቱ፣
  2. በኢትዮጵያ የሚገኙት የእንግሊዝ ዜጎች ሁሉ በኢትዮጵያ ማዕከላዊ አስተዳደር ውስጥ በአማካሪነትም ሆነ በዳኝነት ቁልፍ ቦታዎችን እንዲቆጣጠሩ መደረጉ፣
  3. የአገሪቱ የፖሊስ ሠራዊት ሙሉ በሙሉ በእንግሊዝ ቁጥጥር ሥር እንዲውል መደረጉ፣
  4. የኢትዮጵያ መንግሥት ለሥራው የሚያስፈልጉትን የሌላ አገር ዜጎችን ለመቅጠር የሚችለው የእንግሊዝን ፈቃድ ካገኘ ብቻ እንዲሆን መወሰኑ፣
  5. የኢጣሊያ የጦር ምርኮኞችንና ሲቪል የኢጣሊያ ሠራተኞችን በተመለከተ የመጨረሻውን ውሳኔ የመስጠቱን ሥልጣን እንግሊዞች ብቻ መውሰዳቸው፣
  6. የኢትዮጵያ ንጉሠ ነገሥት መንግሥት አይነተኛ ሥልጣን የሆነውን፤ ጦርነትን በአገሩ ላይ ማወጅ የሚችለው፤ በምሥራቅ አፍሪካ የእንግሊዝ የጦር ኃይል አዛዥ ከፈቀደ ብቻ መሆኑ፣
  7. የእንግሊዝ የጦር መኮንን አስፈላጊ ሆኖ ሲያገኘው ያስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ማወጅ እንዲችል የኢትዮጵያ ንጉሠ ነገሥት የመፍቀድ ግዴታ እንዲኖርበት መደረጉ፣
  8. ከኢትዮጵያ መንግሥት እውቅናና ፈቃድ ውጭ የእንግሊዝ ጦር፤ ንብረት መውርስና ሌላም ተመሳሳይ ከባድ እርምጃዎችን መውሰዱ፣
  9. በኢትዮጵያ የሚገኘው የእንግሊዞች ጦር፤ እንግዳ በሆነ አጠራር፤ “የኢትዮጵያ ሠራዊት” በመባል ከመጠራቱም ሌላ ለኢትዮጵያ ሉአላዊነትም ሆነ ነፃነት ጭራሽ ከበሬታ ያልነበረው መሆኑ፣
  10. ለሁለቱ አገሮች ደህንነት ያስፈልጋል በሚል ሰበብ እንግሊዞች አስፈላጊ ሁኔታዎችን በማመቻቸት በኢትዮጵያ ውስጥ የገንዘብ ፖሊሲን በሚመለከቱ ጉዳዮች ላይ ከፍተኛ ቁጥጥር ማድረግ መጀመራቸው፣
  11. በተለይ እንግሊዞች የፖለቲካ ኦፊሰር እያሉ በየአስተዳደሩ የመደቧቸው የራሳቸው ሰዎች በኢትዮጵያ መንግሥት አስተዳደር ጣልቃ እየገቡ፤ የውሸት ፕሮፓጋንዳና የቴሌግራም መልዕክት እያቀነባበሩ በማታለልና በማስፈራራት ራሳቸው ባዘጋጁት እስር ቤት ሳይቀር ማሰር መጀመራቸው፣
  12. በኢትዮጵያ ንጉሠ ነገሥት መንግሥት የተመደቡትን የአስተዳደር ሰዎች ወደ ጎን በመተው ጣሊያን ሾሟቸው የነበሩትን ሹማምንቶች በመስበክ የራሳቸው ፍላጎት ማስፈጸሚያ በማድረግ በግልጽ ችግር መፍጠራቸው፣
  13. የኢትዮጵያ መንግሥት አስተዳደር ሥርዓትና ፀጥታ እንዳይከበር ለማድረግ በማቀድ፤ በተለይ የወደቀውን ሁሉ በመለቃቀምና የአገሩ ተወላጅ ከጠላት የሚረከበውን ጠመንጃና ጥይት ሁሉ በግድ እየነጠቁ ባሕር ውስጥ መጨመራቸው፣
  14. በተለይ ገንዘብና ንብረትን በተመለከተ በቀጥታ መጋዘን እየሰበሩ እየገቡ በመውሰድ ለራሳቸው መጠቀሚያ ለማድረግ ተደጋጋሚ ሙከራዎችን ማድረጋቸው፣
የሚሉት ይገኙበታል፡፡

በሌላም በኩል ጣሊያኖች ኢትዮጵያ ውስጥ በቆዩባቸው ጊዚያት የሠሯቸውንና ያከማቹትን ንብረቶች አብዛኛውን ማለት ይቻላል፤ ለኢትዮጵያ ምንም ንብረት ሳያስቀሩ በማንአለብኝነት እንግሊዞች ዘርፈው ወስደውታል፡፡
ፎክስ በተሰኘው የኤርትራ ድረ ገጽ ላይ እንደተጠቀሰው ከሆነ፤
  1. አራት ሚሊዮን የእንግሊዝ ፓውንድ የሚያወጡ የሕክምና መገልገያ መሣሪያዎችና የተለያዩ መድሐኒቶች፣
  2. ለሆስፒታል የሚጠቅሙ የኦክሲጅን ማምረቻ ፋብሪካወች፣
  3. የምሕንድስና መሣሪያዎች፣
  4. የጋራጅ መሣሪያዎች፣
  5. የሕትመት መሣሪያዎች፣
  6. የጭነት መኪናዎች፣
እና ሌሎችም ንብረቶች እንዳሉ በሙሉ የእንግሊዝ ቅኝ ግዛት ወደሆኑት፤ ወደ ኤርትራ፣ ሕንድ፣ ኬንያ፣ ዩጋንዳና ሊቢያ ድረስ ተጓጉዘዋል፡፡ -->(የበለጠ ለማንበብ)
እንግሊዞች ስምምነቱ የሰጣቸውን ሕጋዊ ሥልጣን ተገን በማድረግ በኢትዮጵያ ያሉት የእንግሊዝ ባለሥልጣኖችና የጦር መኮንኖች ከመጠን ያለፈ የትምክህተኝነት ስሜት ያሳዩ ነበር፡፡
ይህ ሁሉ የእንግሊዞች አካሄድ ለኢትዮጵያ ንጉሠ ነገሥት አስተዳደር ምቹ ሁኔታን ባለመፍጠሩ ምክንያት ንጉሠ ነገሥቱን ማስቀየሙ አልቀረም፡፡
British troops enter Addis Ababa
የእንግሊዝ ወታደሮች ተሰልፈው
አዲስ አበባ ሲገቡ

Photo link
እንግሊዞች ንጉሠ ነገሥቱን ወደ ዙፋናቸው ለመመለስ ያደረጉት እርዳታ እንደ ትልቅ ውለታ ቢቆጠርም ቅሉ፤ አሰተዳደራቸው በእንግሊዞች ጣልቃ ገብነት ሲሰናከል ዝም ብሎ ለማየት ፈቃደኛ አልነበሩም፡፡
የእንግሊዞችን አጋርነት እንጅ አለቅነታቻውን አልፈለጉም፡፡
በኋላም በ1937 ዓ.ም. በሁለቱ መንግሥታት መካከል የተደረገው ሁለተኛው ስምምነት፤ የኢትዮጵያን ሉአላዊ መብቶች እንደገና ለማስመለስ ችሏል፡፡
የእንግሊዝ ኤምባሲ በሌሎች አቻዎቹ ላይ የነበረው የበላይነትም ቀረ፡፡
የኢትዮጵያ መንግሥትም ማናቸውንም የውጭ ዜጎች በአማካሪነት ለመቅጠር ያለው ነፃነት ተረጋገጠ፡፡
በተጨማሪም እንግሊዞች የጅቡቲ አዲስ አበባን የባቡር መሥመር ለኢትዮጵያ ለመመለስ መስማማታቸው፤ ለኢትዮጵያ በኢኮኖሚም ሆነ በወታደራዊ መስክ ከፍተኛ ጠቀሜታ ነበረው፡፡
ምንም እንኳን የ1937ቱ ስምምነት ለኢትዮጵያ ከበፊቱ የተሻለ ነፃነት የሰጠ ቢመስልም፤ በተለይ ኢትዮጵያ በነበራት የግዛት ጥያቄ ላይ ያለገደብ ሥልጣን የነበራቸውና ፈላጭ ቆራጮች እንግሊዞች ነበሩ፡፡

እንግሊዞች ወደ ኢትዮጵያ ከገቡ በኋላ ድብቅ ፖለቲካዊ ዕቅዳቸው ምን ነበር?

እንግሊዞች በአካባቢው በነበራቸው ወታደራዊ የበላይነት ተጠቅመው ኤርትራንና ኦጋዴንን በቁጥጥራቸው ስር አድረገው ስለነበረ፤ ሁለቱንም ግዛቶች ከኢትዮጵያ ገንጥሎ ለመውሰድ ዕቅድ ነበራቸው፡፡
ኦጋዴንን በተመለከተ የእንግሊዞች ዕቅድ፤ ከእንግሊዝና ከኢጣሊያ ሶማሌ ላንድ ጋር በመደባለቅ “ታላቂቷ ሶማሊያ” የሚል ስያሜ ከተሰጠው በኃላ በእንግሊዞች የሚተዳደር ግዛት ለመመስረት ነበር፡፡
ሶማሊያ ከቅኝ ግዛት ነፃ ከወጣች በኋላም፤ የሶማሊያ መንግሥት ለረጅም ጊዜ በኦጋዴን ላይ ያነሳ የነበረው የይገባኛል ጥያቄ፤ ከላይ የተገለፀውን የእንግሊዞችን እቅድ መነሻ በማድረግ የተጠነሰሰ የግዛት ማስፋፋት ሕልም ነበር፡፡

ሌላው የእንግሊዞች ዕቅድ ድግሞ፤ ኤርትራን ለሁለት ለመክፈል ነበር፡፡ ይኸውም፤
- አንደኛው ዕቅዳቸው፤ የኤርትራ ቆላማው ክፍል፤ በጂኦግራፊ፣ በዘርና በሐይማኖት ከሚቀራረበውና ጎረቤት ከሆነው ከሱዳን ጋር ለማዋሀድ ሲሆን፣

- ሁለተኛው ዕቅዳቸው፤ ትግራይን ከኢትዮጵያ ገንጥሎ ከኤርትራ ደጋማው ክፍል ጋር በማዋሀድ አንድ ራሱን የቻለ ነፃ ሀገር ሆኖ እንዲመሰረት ለማድረግ ያለመ ነበር፡፡
ይህን የእንግሊዞችን አፍራሽ ዕቅድ ስንመለከት፤ ኤርትራን የራሷ ግዛት ለማድረግ የምትጥረው ኢትዮጵያ፤ ይባስ ብሎ ትግራይንም ልታጣ የምትችልበት ሁኔታ ተፈጥሮ ነበር፡፡
አብዛኛው የእንግሊዞች ዕቅድ፤ ኢጣሊያ በአምስት ዓመቱ የኢትዮጵያ ቆይታቸው ደንግገውት የነበረውን አስተዳደራዊ ክልል አጽድቆ የማስቀጠል ፍላጎትን ያዘለ ነበር፡፡





ኢትዮጵያ ከኢጣሊያ አገዛዝ ነፃ ከወጣች ጊዜ ጀምሮ በኦጋዴንና በኤርትራ ያላትን የይገባኛል ጥያቄ ከማንሳት የተቆጠበችበት ጊዜ የለም፡፡
የኦጋዴን ግዛት እስከ 1928 ዓ.ም. ድረስ ዓለማቀፋዊ እውቅናን ያገኘ የኢትዮጵያ አካል እንደነበረ ይታወቃል፡፡
እንግሊዞች ይህን እያወቁ፤ የኦጋዴንን ግዛት ከቀረው የኢትዮጵያ ግዛት ነጥለው በራሳቸው ቁጥጥር ስር ማድረጋቸው ሕጋዊ ያልሆነ እርምጃ ነበር፡፡
Fasist Italians gives training to Eritrean children
የፋሽስት ኢጣሊያ መኮንኖች ለኤርትራ
ተወላጅ ሕፃናት ሥልጠና ሲሰጡ
Photo link
ምንም እንኳን ኤርትራ ከ 1882 ዓ.ም. ጀምሮ የኢጣሊያ ቅኝ ግዛት ሆና ብትቆይም፤ ከቀረው የኢትዮጵያ አካል ጋር በታሪክ የተሳሰረች ከመሆኗም በላይ፤ በአንድ በኩል የጠላትን ዳግመኛ ወረራ ለመከላከልና በተጨማሪም ነፃ የሆነ የባሕር ወደብ ለማግኘት ስትል፤ ኢትዮጵያ፤ ኤርትራን ታስፈልገኛለች በማለት ያለማቋረጥ ጠንካራ ጥያቄ ማቅረቧን ቀጠለች፡፡
እንደሚታወቀው ኤርትራ፤ ከ1882 ዓ.ም. በፊት 'መረብ ምላሽ' በሚል መጠሪያ የምትታወቅ የኢትዮጵያ አካል ነበረች፡፡
ፋሽስት ኢጣሊያ በኢትዮጵያ ላይ የመጀመሪያውን የአድዋን ጦርነት በ1888 ዓ.ም. ሲያውጅ፤ ሁለተኛውን የፋሽስት ወረራ ደግሞ በ1928 ዓ.ም. የፈፀመው፤ የኤርትራን ግዛት እንደ መግቢያ በር ተጠቅሞ ነበር፡፡
ኢትዮጵያ ለኤርትራ ጥያቄ ትክክለኛውን መልስ እስክታገኝ ድረስ ጥረቷን ቀጥላ፤ አሥር ዓመታት ያህል ከተጓተተ በኋላ መልስ ሊያገኝ ችሏል፡፡
የኦጋዴንም ጥያቄ በኢትዮጵያና በእንግሊዝ መካከል በተደረገው ድርድር መልስ አግኝቷል፡፡
በመጨረሻም የኢትዮጵያ መንግሥት ብዙ ጥረት ካደረገ በኋላ በ1947 ዓ.ም. እንግሊዝ ከኦጋዴን ምድር ለመጨረሻ ጊዜ ለቃ ወጣች፡፡
የኤርትራ ግዛት ወደ ኢትዮጵያ እነዲመለስ የቀረበውን ጥያቄ በተመለከተ፤ የተለያዩ ወገኖች የተለያዩ የመፍትሔ ሀሳቦች ማቅረብ ጀመሩ፡፡

የቀረቡት የመፍትሔ ሀሳቦች ሲጠቃለሉም፤ በነፃነት ወይም በአንድነት ዙሪያ ያጠነጠኑ ነበሩ፡፡
በወቅቱ በኤርትራ ውስጥ ከተቋቋሙት የፖለቲካ ቡድኖች መካከል፤ በኤርትራ ሕዝብ ዘንድ ሰፊ መሠረትና ተቀባይነት የነበረው፤ ከኢትዮጵያ ጋር ለመዋሀድ የሚታገለው ቡድን ነበር፡፡
ነፃነትን ያቀነቅኑ የነበሩት የተለያዩ የፖለቲካ ቡድኖች ደግሞ ያስተሳሰራቸው የነበረው ብቸኛው መንስኤ፤ አነድነትን በመቃወም ላይ ብቻ የተመሰረተ ነበር፡፡

የተወሰኑት የነፃነት አቀንቃኝ ቡድኖቹ ይንቀሳቀሱ የነበሩት በቆላማው የኤርትራ ክፍል ሲሆን መጠሪያቸውም 'የሙስሊም ሊግ' ወይም በአረብኛው አጠራር፤ 'ራቢጣ አልኢስላሚያ' ይባል ነበር፡፡

ሌሎቹ የነፃነት አቀንቃኝ ቡድኖች ደግሞ፤ በእንግሊዞች እቅድ መሠረት ኤርትራን ከትግራይ ጋር አጣምሮ ነፃ የሆነ አገር ለመመስረት የሚታገሉትና በደጋማው የኤርትራ ክፍል የሚንቀሳቀሱት፤ የኢጣሊያ ተጽእኖ እንዲቀጥል የሚሹት የኢጣሊያውያን ነዋሪዎችን፣ ክልሶችንና የቀድሞ የኢጣሊያ ወታደሮችን ያቀፈና የ 'ሊበራል ፕሮግረሲቭ ፓርቲ' ተብሎ የሚጠረው ቡድን ነበር፡፡

ለአንድነትና ለነፃነት በሚታገሉት ቡድኖች ውስጥ፤ ክርስቲያኖችና ሙስሊሞች ቢኖሩም ቅሉ፤ በአንድነት ቡድኑ ውስጥ ግን በቁጥር ክርስቲያኖች ይበዙ ነበር፡፡
ሁለቱም የነፃነትና የአንድነት ቡድኖች የውጭ ደጋፊ ኃይሎች ነበሯቸው፡፡

የአንድነት ቡድኖች የኢትዮጵያን መንግሥት ድጋፍ ሲያገኙ፤ የነፃነት ቡድኑ ማለትም፤ የሊበራል ፕሮግረሲቭ ፓርቲው ደግሞ ከሞላ ጎደል በእንግሊዞች የተፈጠረ ቡድን ነበር፡፡
ቀደም ሲል እንደተገለጸው፤ እንግሊዞች ኤርትራን ለመከፋፈል በነበራቸው እቅድ፤ ቆላማውን የኤርትራ ክፍል ቆርሶ እራሷ ወደምታስተዳድረው ሱዳን መቀላቀልና ትግርኛ ተናጋሪውን የኤርትራ ደጋማውን ክፍል ደግሞ ከመረብ ወንዝ ማዶ ከሚገኙ የትግራይ ወገኖች ጋር አዋህዶ ነፃ የሆነ ሀገረ መንግሥት ለማቋቋም የታለመ ነበር፡፡
ይህንን የእንግሊዞች ዕቅድ ለማስፈጸም ነበር የ "ሊበራል ፕሮግረሲቭ ፓርቲ" የተሰኘው ቡድን ከአንድነት ቡድኑ ጋር በተፃራሪ ቆሞ ይታገል የነበረው፡፡
ኢጣሊያም በበኩላ፤ ኤርትራን ቢያንስ በእጅ አዙር ለመቆጣጠር በማሰብ ይመስላል፤ ለኤርትራ ነፃነት ታጋዮች ሁሉ ያልተቆጠበ ድጋፍ ታደርግ ነበር፡፡

የኢድሪስ አዋቴ ነፃ አውጭ ወታደሮች

Photo link
የኤርትራ ጉዳይ፤ ለአራቱ ኃያላን መነግሥታት ማለትም፤ ለአሜሪካ፣ ለእንግሊዝ፣ ለፈረንሣይና ለሶቪየት ህብረት ውይይት ቀርቦ አንድም ስምምነት ሳያገኝ ስለቀረ፤ በመጨረሻ ለተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ተላለፈ፡፡
የተባበሩት መንግሥታት ድርጅትም፤ በርማ (በአሁኑ አጠራር ማይናማር)፣ ጓቲማላ፣ ፓኪስታን፣ ደቡብ አፍሪካና ኖርዌይ የሚገኙበት ኮሚሽን በማቋቋም ጉዳዩ እንዲታይ ወሰነ፡፡
ከተቋቋሙት የኮሚሽኑ አባላት መካከል፤ ከኖርዌይ በስተቀር የቀሩት አገሮች በሙሉ፤ ኢትዮጵያ በኤርትራ ላይ አለኝ የምትለውን የይገባኛል ጥያቄ የሚቃዎሙ ነበሩ፡፡
ሆኖም የኮሚሽኑ አባላት ወደ ኤርትራ ሄደው ሲጎበኙ፤ በሕዝቡ ዘንድ ያጋጠማቸው ጠንካራ የአንድነት ስሜትን በመመልከት፤ በርማና ደቡብ አፍሪካ የነበራቸውን አቋም ለመለወጥ ተገደዋል፡፡
የኢጣሊያ ደጋፊ የሆነችው የላቲን አሜሪካዋ ጓቲማላና ራሷን የኤርትራ ሙስሊሞች ጠበቃ አድርጋ የቀረበችው ፓኪስታን በአንድነት ሆነው፤ ኤርትራ ነፃ አገር እንድትሆን ድጋፍ ሲሰጡ፤ ደቡብ አፍሪካና በርማ ደግሞ፤ ኤርትራ ከኢትዮጵያ ጋር በፌዴሬሽን እንድትተዳደር መረጡ፡፡
ኖርዌይ ደግሞ ብቻዋን ሆና ኤርትራ ከኢትዮጵያ ጋር ትዋሃድ የሚለውን አቋም ያዘች፡፡
Idris Awate statue
አሥመራ የሚገኘው የኤርትራ
ነፃ አውጭ ግንባር መሪ
የነበረው የኢድሪስ አዋቴ ሐውልት

Photo link
በመጨረሻም የተባበሩት መንግስታት ጠቅላላ ጉባኤ በቁጥር 390 ባስተላለፈው ውሳኔ መሠረት ህዳር 23 ቀን 1943 ዓ.ም. ኤርትራ ከኢትዮጵያ ጋር በፌዴሬሽን ትተዳደር የሚለው ሀሳብ ተቀባይነት አገኘ፡፡
ከዚህ በኋላ ነው እንግዲህ የአንድነትና የነፃነት ኃይሎች የፌዴሬሽኑን ሃሳብ ለማፍረስ ሥራየ ብለው በየፊናቸው መንቀሳቀሱን የተያያዙት፡፡
ኤርትራን ከኢትዮጵያ ጋር ለማዋሀድ የሚያስችለው የፌደሬሽን ቀመር፤ በተለይ ለነፃነት በሚታገሉት ቡድኖች በኩል ተቀባይነት በማጣቱ፤ የኤርትራ ፓርላማ፤ የፌደራል አስተርዳደር ስምምነቱን በማፍረስ ኤርትራ ከኢትዮጵያ ጋር ሙሉ በሙሉ እንድትቀላቀል ህዳር 5 ቀን 1955 ዓ.ም. በመወሰን ራሱን በራሱ አከሰመ፡፡

ከዚህ በኋላ ኢትዮጵያ ከኤርትራ ጋር ሙሉ በሙሉ እንድትቀላቀል የተላለፈው ውሳኔ ያልጣማቸው ኤርትራውያን፤ ኤርትራን በትጥቅ ትግል ሙሉ በሙሉ ከኢትዮጵያ ነፃ ማውጣት አለብን ብለው በኢድሪስ አዋቴ መሪነት የነፃ አውጭ ግንባር በአቋቋሙ ከጥቂት ዓመታት በኋላ እንደገና ለኤርትራ ነፃነት ቆሜያለሁ የሚሉ ማለትም ሻዕቢያና ጀብሀ የሚባሉ ሁለት ተፃፃሪ ድርጅቶች ተፈጠሩ፡፡
እነዚህ ሁለት ተፃፃሪ ኃይሎች በርእዮት ዓለም ከመታገል ይልቅ በሥልጣን ሽሚያ ምክንያት፤ ከ 1964 ዓ.ም. እስከ 1966 ዓ.ም. ድረስ ባለው ጊዜ ውስጥ ደም ያፋሰሰ የእርስ በርስ ጦርነት አካሂደዋል፡፡


ምንጭ፤
  1. "የኢትዮጵያ ታሪክ - ከአፄ ልብነ ድንግል እስከ አፄ ቴዎድሮስ"  ደራሲ፡- ተክለ ጻድቅ መኩሪያ 1961 ዓ.ም.
  2. "የኢትዮጵያ ታሪክ ከ 1847 እሰከ 1983"  ደራሲ፡- ፕሮፌሰር ባሕሩ ዘውዴ
  3. "የታሪክ ማስታወሻ"  ደራሲ፡- ደጃዝማች ከበደ ተሰማ 1962 ዓ.ም.
  4. "ሕይወቴና የኢትዮጵያ እርምጃ - ፩ኛ መጽሐፍ"  ደራሲ፡- ቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ ንጉሠ ነገሥት 1928 ዓ.ም.