
ፋሽስት ኢጣሊያ ኢትዮጵያን ለመውረር ያዘጋጀው ካርታ
Image Credit to:
nanopdf (re-touched by the webmaster)
ግራዚያኒ ለደቡብ ጦር ግንባር ያሰለፋቸው ቦንብ ጣይ የጦር አውሮፕላኖች ብዛት 100 ይደርሳል፡፡
የግራዚያኒ ጦር በደቡብ ኢትዮጵያ አቅጣጫ ያለውን ሐረርጌን ለመያዝ በማቀድ፤ የኢጣሊያ ቅኝ ግዛት ከሆነችው ከሶማሊያ ከሦስት አቅጣጫ በመነሳት በኢትዮጵያ የኦጋዴን ድንበር በሆኑት ቦታዎች በቆራሄና በዶሎ ላይ ጦርነት ከፍቶ እየተዋጋ ወደፊት በመግፋት ደጋሀቡርን አልፎ ጉዞውን ጀመረ፡፡
ራስ ደስታ ዳምጠው፤ ጥሩ ትጥቅ የነበረውን፣ የሰለጠነ፣ ለአገሩና ለንጉሠ ነገሥቱ ታማኝና ተራማጅ አስተሳሰብ ያለውን ቁጥሩ 40 ሺህ የሚደርስ ጥሩ ተዋጊ ወታደሮቻቸውን እየመሩ ከነገሌ ቦረና በመነሳት፤ በደቡብ ኢትዮጵያ ግንባር የተሰለፈውን በግራዚያኒ በሚመራው የፋሽስት ጦር ላይ ውጊያ ከፍተው የኦጋዴን ድንበር የሀነችውን ዶሎን ከተቆጣጠሩ በኋላ ግራዚያኒን ለመውጋት ወደ ኢጣሊያ ሶማሌላንድ አመሩ፡፡
ራስ ደስታ ዳምጠው፤ ዋና ዋና አሽከሮቻቸው
የደቡብ ኢትዮጵያ ጀግኖች አርበኞች ወደ ጦር ሜዳ ሲጓዙ
Photo Credit to:
newafricanmagazine
የሆኑትን ፊታውራሪ አደመ አንበሶንና ፊታወራሪ ታደመ ዘለቃን እፊት በማስቀደም፤ እርሳቸው የኋላ ደጀን ሆነው፤ ጦራቸው ግን ከፊት እየተዋጋ የኢጣሊያ ግዛት የሆነችው ሶማሊያ ሲደርሱ፤ በኢጣሊያ ሶማሌ ግዛት ውስጥ ታላቅ ሽብርና ፍርሀት ነገሠ፡፡
በዚህ ስጋት የገባው ግራዚያኒ፤ በሶማሌ ያለው መቶ ሺህ ጦር አይበቃኝምና ተጨማሪ ጦር ይላክልኝ እያለ ለአለቆቹ መልዕት ያስተላልፍ ነበር፡፡
ግራዚያኒ ይህም አልበቃው ብሎ፤ ሶማሌዎችን ሰብስቦ ስለኢትዮጵያውያን ጦር ያስነገረው አዋጅ፤
“…ኢትዮጵያውያን ሶማሌን ለመውረር ተሰልፈዋል፡፡
…አኛ ተዋግተን ከተሸነፈን፤ በመርከባችን ተሳፍረን ወደ አገራችን እንመለሳለን፡፡
…እናንተ ግን የምትሄዱበት ስለሌላችሁ፤ ኢትዮጵያውያን፤ የእናንተን ወንዶች እየሰለቡ፤ ሴቶችን ጡታቸውን እየቆረጡ ይበሉታል፡፡ ምግባቸውም የሰው ሥጋ ነው፡፡
…ስለዚህ፤ ነጋዴ ነኝ፤ ገበሬ ነኝ ሳትሉ በአንድነት እንዋጋ፡፡”
የሚል መልዕክት የያዘ ነበር፡፡
በጣሊያኖች አይን እንደ አደገኛ ጠላት የሚታዩት ጀግናው የደቡብ ጦር መሪ ራስ ደስታ ዳምጠው
credit to:
Ethiopicus
በዚህም የግራዚያኒ የውሸት ስብከት የተታለሉ የሶማሌ ሰዎች፤ መሣሪያ እየተቀበሉ በሐይማኖት ከሚመሳሰሏቸው ከሊቢያ ከመጡ የቅኝ ግዛት ወታደሮች ጋር ለውጊያ ተሰለፉ፡፡
ግራዚያኒም ቆራሄ የሚገኘውን የኢትዮጵያን ምሽግ በተከታታይ በአይሮፕላን በሙስታርድ ጋስ ቦንብ የኢትዮጵያን ሠራዊት መጨፍጨፍ ጀመረ፡፡
በመጨረሻም የአዲስ አበባው የየካቲት 12ቱ እልቂት በሚካሄድበት ዕለት፤ በጣሊያኖች አይን እንደ አደገኛ ጠላት የሚታዩት
ራስ ደስታ ዳምጠው፤ ከረዳታቸው ከደጃዝማች ገብረ ማሪያም ጋሪ ጋር በመሆን፤ ከጠላት ጋር ብርቱ ውጊያ ካደረጉ በኋላ፤ ደጃዝማች ገብረ ማሪያም ጋሪ በጦር ሜዳ ሲሞቱ፤
ራስ ደስታ ዳምጠው ቆስለው ከጦር ሜዳ በማፈግፈግ በጉራጌ አካባቢ መስቃ ከተባለው ሥፍራ ተኝተው በስቃይ ላይ እያሉ በጠላት እጅ ከወደቁ በኋላ ሳይውሉ ሳያድሩ በ45 ዓመት እድሜያቸው በጠላት ጥይት ተረሽነው ተገድለዋል፡፡
በዚህ ጊዜ የባሌ አገረ ገዥ የነበሩት ደጃዝማች በየነ መርድ፤ የጦር ወታደሮቻቸውን እንደያዙ፤ ከባሌ ጊኒር ወደ ዋቢ ሸበሌ ይጓዙ ነበር፡፡
አገሩን ከድቶ ወደ ኢጣሊያ ጦር የወገነው ወሎል ጂሌ፤ የራሱንና ብዙ የሶማሌ ወታደሮችን ይዞ በኢጣሊያኖች መሪነት በድምሩ 7 ሺህ ወታደሮችን ይዞ ወደፊት ይጓዝ ነበር፡፡
ራስ ደስታ ዳምጠው በየካቲት ወር 1929 ዓ.ም. እጃቸው በጠላት ሲያዝ
image ink
ከዚህ በኋላ ታህሳስ 17 ቀን 1928 ዓ.ም. የኢትዮጵያ ወታደሮች በጀግንነት እየተዋጉ ሳለ፤ 19 የኢጣሊያ ቦምብ ጣይ አይሮፕላኖች ደርሰው፤ ሰባት ቶን ክብደት ያለው የሙስታርድ ጋስ ቦምብ፤ በደጃዝማች በየነ መርድ የጦር ወታደሮች ላይ አዘነቡት፡፡
ሆኖም የወገን ጦር፤ ዝቅ ብለው በሚበሩት የጠላት አይሮላኖች ላይ በመተኮስ፤ አንድ አይሮፕላን መተው ሲጥሉ፤ ሁሉም የቀሩት አይሮፕላኖች ተመተው ሳይወድቁ ወደ ሰፈራቸው ተመልሰዋል፡፡
በጦርነቱ መሐል፤ የከዳተኛው የወሎል ጂሌ ወታደሮች ውስጥ፤
300 የሶማሌ ወታደሮች እርሱን ከድተው ከኢትዮጵያውያን ወታደሮች ጋር ሲቀላቀሉ፤ በተጨማሪም፤ በነቀኛዝማች ሰለባና በነቀኛዝማች አሰፋ ባሕታ መሪነት ጣሊያንን ከድተው ከወገን ጦር ጋር የተቀላቀሉ የኤርትራ ተወላጆችና ስመ ጥሩ ጀግኖች፤ ከጠላት ጋር ብርቱ ውጊያ ካካሄዱ በኋላ ደጃዝማች በየነ መርድ እና ቀኛዝማች ሰለባ በጦርነቱ ላይ ተገደሉ፡፡
በዚህ ጦርነት ውስጥ፤ ከጠላት ጋር ሆነን አገራችንን አንወጋም ብለው ጠላትን ከድተው ከወገን ጦር ጋር ተደባልቀው የተዋጉና በስም የተገለፁ ኤርትራውያን ቁጥራቸው ቢያንስ 23 ይደርሳል፡፡
ከእነርሱም መካከል፤ የፊታውራሪነት፣ የግራዝማችነት፣ የባላምባራስነት፣ ማዕረግና በተጨማሪም የሚሊተሪ ማዕረግ ያላቸው ከመቶ አለቃ እስከ ሌፍትናንት ኮሎኔል ማዕረግ የደረሱ ይገኙበታል፡፡
በዚህ ጦርነት፤ በመርዛማ የቦምብ ጋዝ የተነሣ፤ ከወገን በኩል እጅግ በርካታ ሰው ከሞተ በኋላ፤ የተረፈው ጦር ወደ ኋላው ሊያፈገፍግ ችሏል፡፡

Image Credit to: nanopdf (re-touched by the webmaster)

Photo Credit to: newafricanmagazine

credit to: Ethiopicus

image ink