የውጭ ኃይሎች ኢትዮጵያን በቅኝ ግዛት ለመያዝ የነበራቸው ፍላጎትና ሙከራ የተጀመረው አፄ ቴወድሮስ ወደ ስልጣን ከመምጣታቸው ከ1845 ዓ.ም. ቀደም ብሎ ነበር፡፡ በዚያን ጊዜ፤ ቱርኮችና ግብጾች ኢትዮጵያን በቅኝ ግዛት ለማያዝ በያሉበት የሚራወጡበት ወቅት ነበር፡፡
አለፎ ተርፎም በባህርም ሆነ በምድር የኢትዮጵያን ወሰን እያለፉ አገር መያዝ ጀምረው ነበር፡፡
ለምሳሌ ቱርኮች ለኛ ይገባናል እያሉ የኢትዮጵያን የባህር ጠረፍ ይዘዋል፡፡ ግብፆችም በሰሜን ምዕራብ ያለውን የኢትዮጵያ ግዛት ለእኛ ይገባናል እያሉ አደጋ በመጣልና በመያዝ ላይ ነበሩ፡፡
ግብፆች የያዙትን ወሰን እያሰፉ ይዘርፋሉ፣ ቤት ያቃጥላሉ፣ ሴትና ወንዱን እየማረኩ ባሪያ ያደርጋሉ፣ በቁርአን ትምህርት ያላመነውንም በሰይፍ ይቀጣሉ፡፡
ፈረንሳዮችም ከኢትዮጵያ ጠላቶች ጎን ተሰልፈው የመሣሪያ ዕርዳታ እያደረጉ ወረራውን ይደግፉ ነበር፡፡ ፈረንሳዮች ይህን የሚያደርጉበት ምክንያት የኢትዮጵያ መንግሥት ሲዳከም በአዲስ ኃይል ዘምተው ኢትዮጵያን በቅኝ ግዛት ለማያዝ ዕቅድ ስለነበራቸው ነበር፡፡
አፄ ቴወድሮስ ከመንገሣቸው አስቀድሞ የነበራቸው ግዛት መላ ኢትዮጵያን አያጠቃልልም ነበርና በዚያን ወቅት የሮም ካቶሊክ ወደ ኢትዮጵያ የላኳቸው ያዕቆብ (ጃኮቢስ) የሚባሉ ሚሲዮናዊ በሀገር ጉዳይ ጣልቃ እየገቡ ያልሆነ ስብከትና ስለላ እያካሄዱ ሲያስቸግሯቸው ደጃዝማች ካሣ አባረሯቸው፡፡ የሮም ካቶሊኩ አባ ያዕቆብም ከተባረሩ በኋላ ወደ ትግራይ ሄደው ከትግራዩ ገዥ ከደጃዝማች ውቤ ጋር ተቀመጡ፡፡
ደጃዝማች ካሣ፤ ደጃዝማች ውቤን በጦርነት ድል አድርገው ከነገሡ በኋላ አባ ያዕቆብ ከአገር ጥለው በመውጣት በቫቲካን ላሉት የካቶሊክ ሊቀ ጳጳስ መባረራቸውን አቤቱታ አቀረቡ፡፡
የካቶሊክ ሊቀ ጳጳሱም ”እንዴት አንድ ዜጋ ያለምክንያት ይባረራል“ በማለት ለኢጣሊያ መንግስት አቤቱታ ሲያቀርቡ የኢጣሊያ መንግስትም በኢትዮጵያ ጉዳይ ያገባኛል ለሚለው ለፈረንሳይ መንግሥት የተፈጠረውን ጉዳይ አስረዱ፡፡ የፈረንሳይ መንግሥትም ወደ ኢትዮጵያ እግሩን ለማስገባት ምኞት ስለነበረው የቴዎድሮስን መንግሥት በይፋ መቃወሙን ገለፀ፡፡
አባ ያዕቆብም አፄ ቴዎድሮስን ለመጣል፣ እነከሌን እንርዳ እያሉ የኢትዮጵያ መኳንንቶችን ስም እየጠሩ ከፈረንሳይ መንግሥት ጋር መጻጻፍ ጀመሩ፡፡
ይህን በመሳሰሉ በንጉሠ ነገሥቱና በሀገር ላይ በሚፈጸሙ ደባወችና በሌሎች ምክንያቶች ጭምር አፄ ቴዎድሮስ የውጭ አገር ሰዎችን እየጠሉ መጡ፡፡ የሚሲዮናውያንንም ስብከት ከለከሉ፡፡
በኢትዮጵያ ውስጥ ሚሲዮናውያን ስለሚያደርጉት ስብከት አፄ ቴወድሮስ፤
“...በሚገባ አውቃለሁ፡፡ የአውሮጳ መንግሥታት አንድ አገር መያዝ ሲፈልጉ፤ መጀመሪያ ሚሲዮናውያንን ይልካሉ፡፡ ቀጥለውም ሚሲዮናውያኑን የሚያጠናክር ቆንሲል ብለው ይሾማሉ፡፡ ከዚያም በኋላ ቆንሲሉን የሚጠብቅ ወታደሮችን ይልካሉ፡፡ እኔ እንደ ሂንዱስታን ራጃ ቂል ሆኜ እንደዚያ እንዲደረግ የምፈቅድ ሰው አይደለሁም፡፡”
በማለት በአውሮፓውያኑ ሸር የነቁባቸውም መሆኑን ገልፀዋል፡፡
በእርግጥም አፄ ቴወድሮስ ስለ ሚሲዮናውያኑ ተግባር የተናገሩት ትክክል ነበር፡፡ አብዛኛዎቹ ሚሲዮናውያን አገር ውስጥ የሚገቡት ለትክክለኛው የወንጌል ስብከት ሳይሆን፤ የተደበቀው ተግባራቸው ግን፤ የኢትዮጵያን ሁኔታ በማጥናት፣ የመንግስቱን ድክመትና ጥንካሬ ለመሰለል ነበር፡፡
እንግሊዞችም ቢሆኑ ወደ ኢትዮጵያ እግራቸውን ለማስገባት አስበው መጠቀሚያ ያደረጓቸው ወደ ኢትዮጵያ የላኳቸውን የፕሮቴስታንት ሚሲዮናውያንን ነበር፡፡
የእንግሊዝ መንግስት፤
“አፄ ቴወድሮስ በእንግሊዝ መንግስት ሀሳብና ፍላጎት መሰረት በፈቃደኛነት እንዲሰሩ ለማድረግና፤ ፈቃደኛ ሆነው ተባብረው ባይሰሩ ግን፣ ግብፅ አገር የሚገኘው የእንግሊዘ ገዥ ያለውን ኃይል ተጠቅሞ ስነሥረዓት እንዲያስተምራቸውና ሥልጣኔ እንዲያሳያቸው እንዲደረግ… ይህም አዲስ የተቋቋመው የአፄ ቴወድሮስ 'ህፃን' መንግሥት ስለሆነ ማንኛውንም ኃይል መቋቋም ስለማይችል በግብፆች ጦር እንዲመታ...”
በማለት ትእዛዝ አስተላልፎ ነበር፡፡
አፄ ቴወድሮስ በውጭ ኃይሎች ተደጋጋሚ ማስፈራሪያ ቢቀርብላቸውም እርሳቸው አውሮፓውያኑን የሚፈሉጓቸው ሀገራቸውን ለማልማት ብቻ እንጅ፤ ማንም ተነስቶ በበላይነትም ሆነ በስብከት ትዕዛዝ ሊሰጣቸው እንደማይችል በተደጋጋሚ አስታውቀዋል፡፡
አፄ ቴወድሮስ ከአውሮፓ ስለሚላኩ ሰዎች፤
”...ስትመጡ አፍቅሬ፣ በአክብሮት እቀበላችኋለሁ፡፡ አኖራችኋለሁም፡፡ ይህንንም የማደርገው የአውሮፓ ሰዎች ሁሉ፤ ’እነደምወደው እነደ ዮሀንስ ቤል እየመሰላችሁኝ ነው፡፡’ እናንተ ግን ውሸታሞች፣ ቀጣፊዎች ናችሁ፡፡ መልካም ሳደርግላችሁ እናንተ ግን በመጥፎ መለሳችሁልኝ፡፡ እኔን የሚያጥላላ ነገር ትናገራላችሁ፣ ትጽፋላችሁም፡፡ በዓለም ላይ መጥፎ ስም አሰጣችሁኝ፡፡ ...ወደ አገራችሁ በምታስተላልፉት ነገር ሁሉ እኔን የሚያጥላላ ነገር ትናገራላችሁ፡፡”
በማለት ተናግረዋቸዋል፡፡
አፄ ቴወድሮስ፤ በዘመነ መሳፍንት ተወልደውና ነግሠው ዘመነ መሳፍንት የመጨረሻ ፍጻሜውን እንዲያገኝ ያደረጉ ደፋርና ጀግና ንጉሠ ነገሥት ነበሩ፡፡
አፄ ቴወድሮስ ግዛቶቻቸውን ሁሉ አንድ አድርገው ማእከላዊ መንግሥት ለመመስረት ብዙ ደክመዋል፡፡
ካውሮፓውያኑም ጋር አገራቸው የቴክኒክና የጥበብ ትብብር እንዲደረግላቸው በተደጋጋሚ ሳይሰለቹ ግንኙነት በመፍጥር ተለማምጠዋል፡፡
ሀገራቸው ኢትዮጵያ በሥልጣኔ እንድትበለጽግላቸው በተቻላቸው ሁሉ ጥረት አድረገዋል፡፡
ያ ሁሉ ጥረትና ልፋት ግን የእራሳቸውና የራሳቸው ብቻ ሆኖ ቀረ፡፡ በቅን ልቦና ህልማቸውንና ሀሳባቸውን የሚጋራቸው ሰው በማጣታቸውና ከውጭም ሆነ ከውስጥ ተቀናቃኞቻቸው ስለተነሱባቸው ብቻቸውን ቀሩ፡፡
በውጭ ግንኙነቱም በኩል ቢሆን የአውሮፓውያኑን የፖለቲካ ሴራና ሸፍጥ ሳይረዱ ቅን ልቦና ብቻ ይዘው መቅረባቸው እምብዛም አላስኬዳቸውም፡፡
በተለይ በሀገር ውስጥ ለዘመናት ተተብትቦ የቆየው የዘመነ መሳፍንት አስተሳሰብና ባሕል አላራምድ ብሎ ጎትቶ ስለያዛቸው ያለጊዜአቸው ቀድመው የተፈጠሩ የኢትዮጵያ መሪ ነበሩ ለማለት ይቻላል፡፡
አፄ ቴወድሮስ በአንድ ስኬት ብቻ የሚረኩ ንጉሥ አልነበሩም፡፡ ሌላ ውጤት ለማየት ትጋት ይጨምራሉ፡፡
ንጉሡ አዲስ ነገር ለመፍጠር ያላቸው እልህ፣ ቁጭት፣ ቁጣ፤ ትጋት፣ ቁርጠኝነት፣ የጋለ ስሜት፣ ተሳትፎና ክትትል፣ የአመራር ብቃት፣ ለሳይንስና ቴክኖሎጅ ያላቸው መነሣሣት ሁሉ በአጠቃላይ ተደምሮ ኢትዮጵያ የላቀ ደረጃ ላይ እንድትደርስ የነበራቸውን ታላቅ ምኞት፣ ተስፋና ራዕይ የሜያሳይ ነበር፡፡
በታሪክ የትምህርት ዘርፍ አንቱ ከተባሉ ምሁራን አንዱ የሆኑትና የዘር ሐረጋቸው ከትግራይ የሚመዘዘው ፕሮፌሰር ገብሩ ታረቀ፤ በአንድ ወቅት በተዋቂዋ የ ebs ቴሌቪዥን ጋዜጠኛ ህሊና አዘዘ፣
”ከኢትዮጵያ መሪዎች ማንን ያደንቃሉ?“ ተብሎ ቀርቦላቸው ለነበረው ጥያቄ፤
“ የቀደሙትን መሪዎች አልፌ፣ ከአፄ ቴዎድሮስ እሰከ ጠቅላይ ሚኒስትር መለስ ባነፃፅር፤ ቴዎድሮስን የሚያህል የለም፡፡”
በማለት መልሰዋል፡፡
አንቱ ከተባሉ እውቅ የኢትዮጵያ የታሪክ ምሁራን መካከል ፕሮፌሰር ባሕሩ ዘውዴም ስለ አፄ ቴዎድሮስ፤
"...ከዘመናቸው የቀደሙ ታላቅ”
በማለት ገልፀዋቸዋል፡፡
የኢትዮጵያ ዕውቁ የታሪክ ተመራማሪ ምሁር ፕሮፌሰር ሪቻርድ ፓንክረስት በበኩላቸው አፄ ቴዎድሮስን፤
"ምንም ይሁን ምን ቴዎድሮስ ልዩና ዕፁብ ድንቅ፣ በኢትዮጵያ የረጅም ታሪክ ግዙፍ!”
በማለት ገልፀዋቸዋል፡፡
ለአፄ ቴወድሮስ መንግስት መዳከም ከሚጠቀሱት አበይት ምክንያቶች ውስጥ፤
- በደቡብ ኢትዮጵያ የተከሰተው ግጭትና በሰሜን በኩል የኦሮሞ ሚሊሺያዎች የተቀሰቀሰው አመፅ፤
- በትግራይ የተቀሰቀሰው አመፅና፤
- በቀይ ባህር አቅራቢያ በኦቶማን ቱርክ እና በግብፅ ወታደሮች ይፈፀም የነበረው የማያቋርጥ ወረራ
ተጠቃሽ ናቸው፡፡
አፄ ቴወድሮስ ሙሉ በሙሉ በሚባል መልኩ አጋር በማጣታቸው ንዴትና ብስጭታቸው እየተባባሰ ሄደ፡፡
ኢትዮጵያን አንድ ለማድረግ ታጥቆ የተነሳና ትልቅ ዓላማ የነበረው ጀግና መሪ ከጥቂት ባለሟሎቻቸው ጋር ብቻ በመሆን ሰፊ የነበረው የመንቀሳቀሻ ግዛቶቻቸው እየጠበቡ ሄደው በደብረ ታቦርና በመቅደላ አካባቢ ብቻ ተወስነው ቀሩ፡፡ አልፎ ተርፎም ንጉሡ መቅደላ ላይ ለመመሸግ ተገደዱ፡፡
60 ሺህ ይገመት የነበረው ሠራዊታቸው እየመነመነ ሄዶ ወደ 10 ሺህ አሽቆለቆለ፡፡
በመጨረሻም እንግሊዞች የታሰሩባቸውን እስረኞች ለማስፈታትና አፄ ቴወድሮስን ማርኮ እጃቸውን ለመያዝ በጀነራል ናፒየር የጦር መሪነት 32 ሺህ የሚደርሱ ዘመናዊ መሣሪያ የታጠቁና በወታደራዊ ሙያ ብቁ የሆኑ ወታደሮች በመላክ የጦርነት አዋጅ አወጁባቸው፡፡
የተላከው የእንግሊዝ ተዋጊ ጦር ያለምንም ተቀናቃኝ የኢትዮጵያን ድንበር አቋርጦ ወደ መሀል ሀገር እንዲገሰግስ የአፄ ቴወድሮስ ባላንጣ (ተቀናቃኝ) መሳፍንቶች ከእንግሊዝ ጦር መሪዎች ጋር በመመሳጠር የተቻላቸውን ሁሉ አድርገዋል፡፡
አፄ ቴወድሮስም 65 የሚደርሱ የእንግሊዝ እስረኞችን ፈተው ከለቀቁ በኋላ 5 ሺህ ያህል ተዋጊ ሠራዊታቸውን አሰልፈው ሚያዝያ 2 ቀን 1860 ዓ.ም. ከቀኑ ለ 11 ሰዓት ሩብ ጉዳይ ሲሆን በእንግሊዞች ላይ ተኩስ እንዲከፈት ትእዛዝ ሰጡ፡፡
የተሰራውን መድፍ እኒዲተኮስ ቢያዙም ተኳሽ ኢትዮጵያውያን አንድ የመድፍ ጥይት ብቻ ማጉረስ ሲገባቸው ሁለት ጥቶች በአንዴ በማጉረሳቸው መድፎ ተሰንጥቆ ከአገልግሎት ውጭ ሆነ፡፡ በዚህም ድርጊት አፄ ቴዎድሮስ በጣም ተበሳጩ፡፡
የአፄ ቴወድሮስ ሠራዊት የሚዋጋው በጦርና በጎራዴ በመሆኑ የእንግሊዞችን ጦር መመከት ስለተሳነው ሠራዊታቸው እየተመናመነ ሄዶ ንጉሡ ከጥቂት የጦር አለቆቻቸው ጋር ብቻ ቀሩ፡፡
የእንግሊዝ ጦርም የመቅደላን ተራራ በመድፍ ሳያቋርጥ መደብደቡን ቀጠለ፡፡
አፄ ቴዎድሮስ ከጀነራል ናፒየር ጋር እርቅ ለማድረግ አስበው ለላኩት የእርቅ ደብዳቤ የተሰጣቸው መልስ፤ የያዟቸውን እስረኞች ለቀው እርሳቸውም እጃቸውን ካልሰጡ እርቅ እንደሌለ ከደጃዝማች አለሜ አንደበት ከሰሙ በኋላ መልእክተኛውን አሰናብተው ወደ ፈጣሪያቸው ፀልየው ሲጨርሱ፤
“ኃይለኞችን እንደ ህፃን በክንዱ ይዞ የኖረ እንደ እኔ ያለ ወታደር፤ ዛሬ በሰው ክንድ መያዝን ሊታገስ አይችልም፡፡”
በማለት ተናገሩ፡፡
ንግግራቸውንም እንደጨረሱ ሽጉጣቸውን አውጥተው ሊጠጡ ሲሉ ወዲያውኑ ባጠገባቸው የነበሩት ወዳጆቻቸው
ሽጉጣቸውን ቀምተው አስጣሏቸው፡፡
በዚህ ሰዓት አጠገባቸው የነበረው ጋሻ ጃግሬአቸው፣
“እጃችንን እንስጥ” አላቸው፡፡ እርሳቸውም፣
የለም በሰዎች እጅ ከመውደቅ በእግዚአብሔር እጅ መውደቅ ይሻላል፡፡
ብለው መለሱለት፡፡ ወዲያውኑ ታማኝ ወዳጆቻቸው በጥይት እየተመቱ መውደቅ ጀመሩ፡፡ ከእርሳቸው አጠገብ የነበሩት ሦስት ታማኞቻቸው ብቻ ቀሩ፡፡
ንጉሡም ወዲያውኑ አጠገባቸው የነበሩትን እነዲሸሹ ካዘዙ በኋላ ወልደ ጋብር ወደተባለው ታማኛቸው ዞር ብለው፤
አለቀ፡፡ በእነርሱ እጅ ከምወድቅ እራሴን እገላለሁ፡፡
ካሉት በኋላ፣
ሽጉጣቸውን ከአፎቱ መዘው አፋቸው ውስጥ ከተው ሲተኮሱ ወደቁ፡፡ የተኮሱት ጥይትም በላንቃቸው አልፋ በማጅራታቸው በኩል ወጣች፡፡
በአቅራቢያው የነበሩ የተኩስ ድምፅ የሰሙ ሁለት የአይርሽ ወታደሮች ደርሰው ሲመለከቱ ያ ቆፍጣና ንጉሠ ነገሥት ቴዎድሮስ በጀርባቸው ተንጋለው አገኟቸው፡፡ ወታደሮቹም የጀግናው የአፄ ቴዎድሮስን ሽጉጥና የጣታቸውን ቀለበት ሰርቀው ወሰዱ፡፡
አፄ ቴወድሮስ በነገሡ በ 13ኛው ዘመነ መንግሥታቸው፤ ሚያዝያ 2 ቀን 1860 ዓ. ም. ከእንግሊዞች ጋር የጀመሩት ጦርነት፤ ሚያዝያ 6 ቀን 1860 ዓ. ም. ተጠናቆ በዚሁ ዕለት ከቀኑ 10 ሰዓት ከ 10 ደቂቃ ሲሆን፤ እጄን ለጠላት አሳልፌ አልሰጥም በማለት በራሳቸው ሽጉጥ ራሳቸው ላይ ተኩሰው በወሰዱት እርምጃ በ 50 ዓመት እድሜያቸው የሕይወታቸው ፍጻሜ ሆነ፡፡
ቆራጡና ጀግና ዳግማዊ አፄ ቴዎድሮስም፤ የራሳቸውንና የአገራቸውን የኢትዮጵያን ክብር ለባእዳን አሳልፈው ላለመስጥት ሲሉ ራሳቸውን መስዋዕት አደረጉ፡፡
የአፄ ቴወድሮስ የቀብር ሥነ ሥርዓትም በአቅራቢያው በሚገኘው የማሪያም ቤተ ክርስቲያን ተፈፀመ፡፡
አፄ ቴዎድሮስ ሲሞቱ ዳግማዊ ምኒልክ የተናገሩትን 'ማሳያ' የተባለው ፀሀፊ፤
“...ዳግማዊ ምኒልክ አፄ ቴዎድሮስን የወዷቸው ስለነበር የአፄ ቴዎድሮስን ሞት በሰሙ ጊዜ በጣም አዘኑ፡፡
...ቴዎድሮስ ዳግማዊ አባቴ ስለሆኑ አዝኛለሁና እዘኑልኝ ብለው አዋጅ አስነገሩ፡፡
…አስተማሪዬን አጣሁ፡፡
...ቴዎድሮስ እኔን በመልካም አስተዳደግ አሳድገውኛል፡፡
ይሄ ልቤን ነክቶታል፡፡”
በማለት ግልጾታል፡፡
- ገደልን እንዳይሉ ሞተው አገኟቸው፣
- ማረክን እንዳይሉ ሰው የለ በጃቸው፣
- ምን አሉ እንግሊዞች ሲገቡ አገራቸው፤