Content-Language: am ራስ አሉላ እንግዳ (አሉላ አባነጋ)
header image




ራስ አሉላ እንግዳ (አሉላ አባነጋ)




የጀግናው ጦር መሪ የራስ አሉላ እንግዳን (አሉላ አባነጋ)
የአርበኝነትና የሕይወት ታሪክ ያዳምጡ















1. ትውልድ፣ ዕድገትና የትዳር ዘመን

ራስ አሉላ እንግዳ በ1879 ዓ.ም.
አሉላ የተወለዱት በተንቤን አውራጃ መናዊ በተባለች መንደር ከገበሬ አባታቸው ከእንግዳ እቁቤ በ1831 እና 1833 ዓ.ም. መካከል እንደሆነ ይገመታል፡፡
ምንም እነኳን አሉላ የዘር ሐረጋቸው ከመሳፍንት ቤተሰብ ባይሆንም በመጀመሪያ አሉላ በዘር ሀረጋቸው የእንደርታ ገዥ እና የመሬት ባላባት ከነበሩት ከእውቁ ራስ አርአያ ድምፁ ጋር በመቀራረብ ወዳጅነት መሰረቱ፡፡
ከጊዜ በኋላም አሉላ እድሜያቸው 20 ዓመት ሲሞላቸው ወደ ደጃዝማች ካሣ ምርጫ (በኋላ አፄ ዮሐንስ) በመጠጋታቸው እና የእርሳቸውን ይሁንታ በማግኘታቸው በመጀመሪያ የቤተ መንግሥታቸው የእልፍኝ አስከልካይ (በአሁኑ አጠራር የፕሮቶኮል ሹም) ሆነው ተሾሙ፡፡
ይበልጡኑ ደግሞ አባታቸው በአፄ ቴዎድሮስ በመገደላቸው ሳቢያ በበቀል ተነሳስተው ለሦስት ዓመት ብቻ የነገሡት የላስታው ዋግ ሹም ጎበዜ፣ በኋላም ንጉሥ ተክለ ጊዮርጊስ ጋር አፄ ዮሐንስ ባደረጉት ጦርነት፤ አፄ ዮሐንስ በጦርነቱ ድል ሲያደርጉ አሉላ የተክለ ጊዮርጊስን እጅ ይዘው ለአፄ ዮሐንስ በማስረከባቸው በንጉሡ ዘንድ ይበልጥ ተወዳጅ እንዳደረጋቸው ይተረካል፡፡
አሉላ 30 ዓመት ሲሞላቸው በባላባታዊ የአስተዳደር ሥርዓት ውስጥ ከፍተኛ ስፍራ በማግኘት ጠንካራ የአመራር ችሎታ እንዳላቸው እያስመሰከሩ ቀጠሉ፡፡
አሉላ የ30 ዓመት እድሜ ላይ እያሉ ወይዘሮ ብትወጣን አግብተው ሦስት ልጆችን አፍርተው ተለያይተዋል፡፡
ሁለተኛ ሚስታቸው የራስ አርአያ ድምፁ ልጅ የሆኑትን ወይዘሮ አምለሱን ቢያገቡም ብዙ ሳይቆዩ ሚስታቸው በሞት ተለይተዋል፡፡

2. የኩፊት ጦርነት

Ras Mulugeta Yigezu
አሥመራ የነበረው የያኔው
የራስ አሉላ መኖሪያ ቤት
በማህዲስት የሱዳን ጦር እና በኢትዮጵያ ሠራዊት መካከል የመጀመሪያው ውጊያ የተደረገው መስከረም 23 ቀን 1875 ዓ.ም. በአሥመራና በከሰላ አጋማሽ ላይ በሚገኘው ኩፊት ከተባለው ስፍራ ላይ ነበር፡፡ ማህዲስቶች አብዛኛውን በኤርትራ የሚገኙትን ጎሳዎች ለማሳመን ጥረት አድርገው ነበር፡፡
ሁለቱም ኃይሎች በጊዜው በጦር ሜዳ ጥሩ ስምና ዝና በነበራቸው ጀነራሎች የሚመሩ ነበሩ፡፡
የማህዲስቶቹ ጦር በዑስማን ዱግ የሚመራ ሲሆን የኢትዮጵያው ጦር ደግሞ በአሉላ አባነጋ የሚመራ ነበር፡፡
ውጊያው ከተጀመረ በኋላ ማህዲስቶች በውጊያው ብልጫ ስለነበራቸው በኢትዮጵያ ጦር ላይ ጉዳት ከማድረሳቸውም በላይ አሉላም በውጊያው ላይ ቆስለው ነበር፡፡
በኋላም የኢትዮጵያ ጦር በውጊያው በርትቶ ስለተዋጋ ድሉ የኢትዮጵያውያን ሆነ፡፡
በዚህ ውጊያ 3 ሺህ የማህዲስት ወታደሮች ሲሞቱ በኢትዮጵያ ጦር በኩል፤ የአሉላ ዋና የጦር አዝማች የነበሩት ብላታ ገብሩ እና አሳላፊ ሐጎስን ጨምሮ የማህዲስቶችን ግማሽ ያህሉ ሞተዋል፡፡
ማህዲስቶች በዚህ ብቻ ሳያባቁ በደቡብ ምእራብ ወለጋ፣ በአሶሳ ቤኒሻንጉል እና በኮሞሻ፤ ቀደም ሲል ግብፆች ይዘውት የነበረውን እነርሱን ተክተው በአካባባው ለመስፋፋት ራሳቸውን ካጠናከሩ በኋላ አልፈው ተርፈው ወደ ኦሮሞ ምድር ዘልቀው ይዞታቸውን ለማስፋፋት ቢሞክሩም የአካባቢው ነዋሪ በሠላም አልተቀበላቸውም፡፡
ይህን የማህዲስቶችን ወደ ምእራብ ኢትዮጵያ ሠርጎ መግባትን የተመለከቱት ዳግማዊ አፄ ምኒልክ፤ ዋና የጦር መሪያቸውን ራስ ጎበና ዳጨን ወደ ቦታው ዘምተው ማህዲስቶችን እንዲመክቱ በሰጡት ትእዛዝ መሠረት ጥቅምት 5 ቀን 1881 ዓ.ም. ራስ ጎበና ከማህዲስቶች ጋር ተዋግተው መልሰዋቸዋል፡፡

3. የሂዌት ሰምምነት

የሄዊት ስምምነት ወይም የአድዋ ስምምነት ተብሎ የሚጠራው ግንቦት 27 ቀን 1876 ዓ.ም በብሪታንያ፣ በግብፅ እና በኢትዮጵያ መካከል በአድዋ የተፈረመ ስምምነት ነው።
ይህ ሰምምነት የብሪታንያው ተወካይ በሆነው በአድሚራል ዊሊያም ሂዌት ስም ተሰይሟል፡፡
ስምምነቱ በግብፅና በኢትዮጵያ መካከል ለረጅም ጊዜ ሲንከባለል የቆየውን ግጭት እንዲያበቃ ቢያግዝም በተዘዋዋሪ ግን በኢትዮጵያ እና በኢጣሊያ መካከል አዲስ ግጭት አስነስቷል።
ስምምነቱ 7 አንቀጾች ነበሩት፡፡
የስምምነቱ ውል በሰሜን ኢትዮጵያ በሚገኘው በኤርትራ ምድር በአሥመራ ከተማ የተካሄደ ሲሆን፤ በግብፅ በኩል፤ በማሰን ቤይ፤ በብሪታንያ በኩል፤ በአድሚራል ዊሊያም ሂዌት፤ በኢትዮጵያ በኩል የኤርትራ ተጠሪ ሆነው በአደራደሩት በራስ አሉላ አማካኝነት ተካሂዷል፡፡
በስምምነቱ የመጀመሪያ አንቀፅ፤ ኢትዮጵያ በምፅዋ ወደብ በኩል የጦር መሳሪያን ጨምሮ ሁሉንም እቃዎች በነፃ ለማጓጓዝ እንደምትችል ይደነግጋል።
በዚህም በመጀመሪያው የውል አንቀፅ መሠረት የኢትዮጵያን መብት እንድታስከብር ብሪታንያ ኃላፊነቱን ወስዳለች፡፡
በሁለተኛው የስምምነቱ አንቀፅ፤ ከ1860 ዓ.ም ጀምሮ በግብፅ ተይዞ የነበረውን በከረን አካባቢ የሚገኘውን ቦጎስን ወደ ኢትዮጵያ እንድትመለስ ይደነግጋል።
በሶስተኛው የስምምነቱ አንቀፅ፤ የግብፅ ወታደሮችን ከከሰላ ለማስወጣት በሚወሰደው እርምጃ ኢትዮጵያ እርዳታ እንድታደርግ ይደነግጋል።
በአራተኛው የስምምነቱ አንቀፅ፤ ከግብፅ ለኢትዮጵያ ተሹመው የሚላኩትን ጳጳስ የይለፍ ፈቃድ ግብፅ እንድትፈቅድ ይደነግጋል፡፡
በአምስተኛው የስምምነቱ አንቀፅ፤ ግብፅና ኢትየጵያ ወንጀለኞችን አሳልፈው እንዲሰጡ ይደነግጋል፡፡
የመጨረሻው የስምምነቱ አንቀፅ ስድስተኛው አንቀፅ ሲሆን፤ ይህም በስምምነቱ አንቀጾች ላይ ግብፅ እና ኢትዮጵያ ሳይግባቡ ቢቀሩ ብሪታንያ ሁለቱንም አገሮች እንደምትሸመግል ይደነግጋል፡፡
ስምምነቱ ከተጠናቀቀ በኋላ ተዋዋዮቹ ወደ አድዋ በማምራት ስምምነቱ ለንጉሠ ነገሠቱ አፄ ዮሐንስ ቀረበ፡፡
የሚገርመው ነገር፤ ኢትዮጵያ የባሕር በር እንዲኖራት አፄ ዮሐንስ ያቀረቡትን ጥያቄ ወደ ጎን በመተው እንደገና ሌላ የመጨረሻ ያሉትን ስምምነት ሲፈጽሙ፤ የግብፅን እና የእንግሊዝን መብት ይበልጥ የሚያረጋግጥ እና ድል የሚያቀዳጅ ሆኖ፤ ነገር ግን የኢትዮጵያን የባሕር በር ጥያቄ የዘነጋ ሰምምነት ሆኖ ተጠናቀቀ፡፡

4. የሂዌት ስምምነት መፍረስ

የሂዌት ስስምምነት ከፀደቀ በኋላ ብዙም ሳይቆይ በግብፅ ተይዞ የነበረው የምፅዋ ወደብ በእንግሊዝ ይሁንታ ጣሊያኖች እንዲይዙት ተደረገ፡፡
ግብፆች በኢትዮጵያ ከተሸነፉ በኋላም ራስ አሉላ አልተዘናጉም፡፡
ከሁሉም በላይ ይህ ጊዜ የአውሮፓ ኢምፔሪያሊዝም መላውን አፍሪካ በቅኝ ግዛት ለመቀራመት ያሰፈሰፈበት ወቅት ነበር፡፡
ጣሊያኖችም የሂዌት ስምምነትን በመጣስ በቀይ ባሕር ዳርቻ እና በአካባባዊ በሚገኙት በምፅዋና በሰዓጢ አካባቢ መስፈር ጀመሩ፡፡
የራስ አሉላ ቀዳሚ እና ዋና አጀንዳ የኢትዮጵያን የግዛት አንድነት በማስከበር ዋስትና ማግኘት ነበር፡፡
አሉላ በሂዌት ስሰምምነት ከብሪታንያ ጋር የተዋዋሉበት ዋናው ዓላማ ደርቡሾችን (ግብፅን) ለመቆጣጠር በማሰብ ሲሆን፤ በአንፃሩ ግን የጣሊያኖች በሰሜን ኢትዮጵያ በቀይ ባሕር አካባቢ መስፈር ምክንያቱ የእንግሊዞች ይሁንታ እንዳለበት ጠርጥረዋል፡፡
እንግሊዞች፤ በአፍሪካ ቀንድ ውስጥ የሚያካሂዱት ፖለቲካ በዋናነት ሁለት መልክ (double standard) ያለው እንደሆነ አሉላ ምንም ጥርጣሬ አልገባቸውም፡፡
ሃጌ ኤልሪች፣ የተባለው እስራኤላዊ የታሪክ ምሁር፤ “ኢትዮጵያ እና የገጣማት የነፃነት ፈተና” በሚል ርዕስ በጻፈው መጽሐፉ ራስ አሉላ የተናገሩትን ሲጠቅስ፤
“…እንግሊዞች የሂዌት ስምምነትን አፍርሰው አገሬን ጣሊያኖች እንዲወስዱት ሲፈቅዱ ምን ለማድረግ ፈልገው ነው?
…በቦጎስ (ከረን) የሰፈረውን የግብፆች ጦር አልተውኩላቸውም ነበርን?
…ምንም ቢዘገይም በከሰላ አልተዋጋሁላቸውም ነበርን?
…የሚቻለኝን ሁሉ አላደረኩላቸውም ነበርን?
…እናንተ እንግሊዞች፤ የፈለጋችሁትን ካደረግልንላቸሁ በኋላ እኛን ተዋችሁን፡፡”
በማለት ገልጾታል፡፡
አሉላ ከኩፊት ጦርነት በኋላ ከቁስላቸው እምብዛም ሳያገግሙ ወደ አሥመራ መመለስ ግድ ሆነባቸው፡፡

5. የዶጋሊ ጦርነት ዋዜማ

ከከሰላ ውጊያ በኋላ አሉላ ፈጥነው 5 ሺህ ተዋጊ ሠራዊታቸውን ወደ አሥመራ በማንቀሳቀስ ጊንዳና ሰዓጢ በተባሉት ስፍራዎች አሰፈሩ፡፡
አሉላ ከጣሊያኖች ጋር ውጊያ ከመጀመራቸው አስቀድሞ፤ ከአይለት አውራጃ አስተዳዳሪ ከሆኑት ከሻለቃ አርዓያ እና ከጊንዳ አስተዳዳሪ ከሆኑት ከባላምባራስ ተሰማ ባገኙት መረጃ መሠረት ጣሊያኖች ይዞታቸውን ወደ ምጽዋ በማስፋፋት ላይ መሆናቸውን ለአፄ ዮሐንስ ሪፖረት አድርገውላቸዋል፡፡
ይህን የጣሊያኖችን ወደ ቀይ ባሕር መስፋፋት፤ አሉላ ዝም ብለው አልተመለከቱም፡፡
ይልቁንም የሂዌት ስምምነት ላይ እንግሊዝን ወክሎ የተስማማው የአድሚራል ዊሊያም ሂዌት ረዳት ለሆነው ለሀሪሰን እስሚዝ፤ እንግሊዞች የሂዌትን ስምምነት እንዳፈረሱና ቃላቸውን እንዳላከበሩ፣ ይልቁንም ከቱርክ በስተቀር ሁሉም የአውሮፓ አገራት ጣሊያኖች ወደ ምፅዋ መስፋፋታቸውን ሁሉም እንደደገፉት እና እርሱም ውሸታም መሆኑን ነግረውታል፡፡
አሉላ፤ ወደ ጎጃም ተሻግረን ለአባይ ድልድይ በመስራት የጎጃሙንንጉሥ ተክለ ሐይማኖትን እናግዛለን በማለት እራሳቸውን መሀንዲሶች ነን በማለት ለስለላ ለመጓዝ አቅደው የነበሩትን የጣሊያን ሰላዮችን ይዘው አስረዋቸዋል፡፡
ጣሊያኖች ህግንና ስምምነትን ጥሰው የያዙትን የኢትዮጵያ መሬት ለቀው የማይወጡ ከሆነ ጣሊያኖችን ያለርህራሄ እንደሚደመስሷቸው ምፅዋ ለሚገኘው የኢጣሊያ ወኪል አሉላ በጽሁፍ አስጠንቅቀውታል፡፡
ይሁን እንጅ ጣሊያኖች ለአሉላ ማስጠንቀቂያ ምንም ደንታ ሳይሰጣቸው አልፈው ተርፈው፤ “እኛ ወደ ምፅዋ የመጣነው በእግዚአብሔር ፈቃድ ስለሆነ ነው፡፡” በማለት መሳለቅ ጀመሩ፡፡
ከዚህ በኋላ በ1878 ዓ.ም. አሉላ ሠራዊታቸውን በምፅዋና በሰዓጢ አካባቢ ማስጠጋት ጀመሩ፡፡
በአካባቢውም የነበሩት አርበኞች የአሉላን እርምጃ በመደገፍ፤
“…አሉላ፤ ባሕር ተሻግረው የመጡትን ባእዳን አንወዳቸውም፡፡ …ወደ ምፅዋ መተህ ይህን በአገራችን የበቀለውን ባእድ አረም ከመርፈዱ በፊት አጥፋው፡፡” በማለት ለአሉላ ነግረዋቸዋል፡፡
አሉላ ከመረብ ምላሽ ያለውን ግዛት እንዲያስተዳድሩ በአፄ ዮሐንስ መሾማቸው ይታወሳል፡፡
ራስ አሉላ ከኮፊት ጦርነት በኋላ ብዙም ሳያገግሙ ወደ አሥመራ ተመለሱ፡፡
ራስ አሉላ በአሥመራ አቅራቢያ በሚገኘው ጊንዳ ከተባለው ስፍራ የሚገኘውን ቁጥሩ 5ሺህ የሚደርሰውን ጦራቸውን ይዘው ሰዓጢ ወደተባለው ስፍራ ማምራት ጀመሩ፡፡
ራስ አሉላ ጦራቸውን ሲያንቀሳቅሱ በአፄ ዮሐንስ ፈቃድ ይሁን አይሁን በውል የታወቀ ነገር የለም፡፡
ይሁን እንጅ በዘመናዊት ኢትዮጵያ በሚገኙት ሰነዶች ላይ ሁኔታው እንደተመዘገበው ከሆነ፤ አፄ ዮሐንስ ለእንግሊዝ ንግሥት ቪክቶሪያ መጋቢት 1 ቀን 1879 ዓ.ም. በጻፉት ደብዳቤ ላይ፤
“የራሳቸው ጀነራል (ጀነራል አሉላን ማለታቸው ነው) የጣሊያኖችን ይዞታ ለመረዳት ሁለት ሳምንት ያህል ፈጅቶ የት ድረስ እንደሆነ ስለታወቀ ጣሊያኖች ከምፅዋ ምድር ለቀው እንዲወጡ፤ አለዚያ ግን በውጊያ እናሶጣቸዋለን፡፡” ብለው መጻፋቸው ተዘግቧል፡፡

6. የዶጋሊ ጦርነት

Ras Mulugeta Yigezu
የዶጋሊ ጦርነት በ1879 ዓ.ም. በሰዓሊው እይታ
ጣሊያኖች በአሰብና በምፅዋ ወደብ ብቻ ተወስነው መቅረት ስላልፈለጉ ይልቁንም ወደ መሀል ኢትዮጵያ ዘልቀው ለማያዝ ከፍተኛ ፍላጎት አደረባቸው፡፡
በጥቅምት ወር 1878 ዓ.ም. የራስ አሉላ ጦር በሰዓጢና በምፅዋ አካባቢ መታየቱ ተረጋገጠ፡፡
በራስ አሉላ ጦር እና በጣሊያኖች ጦር መካከል የመጀመሪያው ግጭት የተደረገው ጥር 18 ቀን 1879 ዓ.ም. ሰዓጢ በተባለው ስፍራ ሲሆን ጣሊያኖች የራስ አሉላን ጦር ተቋቁመው መልሰውታል፡፡
በሰዓጢ በተደረገው ውጊያ የራስ አሉላ ጦር ላይ ከበድ ያለ ጉዳት ደርሷል፡፡
ራስ አሉላ የተጎዳውን ጦራቸውን መልሶ በማቋቋምና በማደራጀት ከጣሊያን ጦር ጋር በድጋሚ ውጊያ ገጠሙ፡፡
ጀግናው ራስ አሉላ ፈረሳቸውን ጭነው ጥር 20 ቀን 1879 ዓ.ም. መሽጎ በተቀመጠው የኢጣሊያ ጦር ላይ በመዝመት ዶግአሊ በተባለው ስፍራ ላይ መሽጎ የነበረውን 500 የኢጣሊያ ጦር ገድለው ድልን በመቀዳጀት ስፍራውን ከጠላት ለማስለቀቅ ችለዋል፡፡
በዚህም ሽንፈት የተነሳ በኢጣሊያ አገር ታላቅ ሽብር ሆነ፡፡
በሁለተኛው ዙር የዶጋሊ ውጊያ ላይ የጣሊያን ጦር አዛዥ ጀነራል ክሪስቶፎሪስ ሲገደል፤ 400 የጣሊያን ወታደሮች እና 22 የጣሊያን የጦር መኮንኖች ተገድለዋል፡፡
ይህን የተፈጠረውን ጠብ በሰላማዊ መንገድ ለመፍታት አፄ ዮሐንስ እና የኢጣሊያ መንግሥት በየግላቸው የእንግሊዝን እርዳታ ጠየቁ፡፡
እንግሊዞች የላኩት አስታራቂ ሀሳብም በምላሹ ዮሐንስ በዶግአሊ ላደረሰው እልቂት ኢጣሊያ ይቅርታ እንዲጠይቁ ሆኖ ጣሊያኖች የያዙዋቸውም የኢትዮጵያ ግዛቶች ፀንተው እንዲቀጥሉና ይህንኑ እንዲቀበል የሚል ሆኖ አረፈው፡፡
ይሁን እንጅ እነደዚህ ዓይነቱን ሀሳብ ማንም የተቀበለው አልነበረም፡፡
በዚህን ወቅት ነበር ጀግናው ራስ አሉላ፣ ለተላከው አስታራቂ መልክተኛ፤
“ጣሊያኖች ኢትዮጵያ ምድር ላይ የሚሰፍሩት፤ እኔ የሮማ አገረ ገዥ መሆን የቻልኩ እንደሆነ ብቻ ነው፡፡”
በማለት በታሪክ ሲታወስ የሚኖረውን ድንቅ ንግግር የተናገሩት፡፡

አፄ ዮሐንስ ከማህዲስቶች ጋር መተማ ላይ በተደረገው ጦርነት ቆስለው በማጣጣር ላይ እያሉ የእርሳቸው አልጋ ወራሻቸው ራስ መንገሻ ዮሐንስ መሆናቸውን በተናዘዙበት ወቅት፤ ራስ አሉላ እና የእርሳቸው መኳንንቶች ራስ መንገሻ ዮሐንስን እንዲደግፏቸው ተማፅነዋል፡፡
ከዚያ በኋላ አሉላም አለቃቸው በሞት ሲለዩአቸው ብቸኝነት እየተሰማቸው ከመሄዱም በላይ የጣሊያኖች ከባሕር በር ባሻገር የጣሊያኖች ግስጋሴ እና መስፋፋት የእርሳቸውን የመረብ ምላሽ ግዛታቸውን እያሳጣቸው መጣ፡፡

7. የራስ አሉላ በአድዋ ጦርነት የነበራቸው ተሳትፎ

አድዋ ላይ ከጣሊያኖች ጋር የነበረው እውነተኛው ግጭት ከመጀመሩ በፊት በኢትዮጵያ ግዛት በስተግራ በኩል የአዲ አቡንን ኮረብታ የተቆጣጠረው የአሉላ ሠራዊት ነበር፡፡
የአሉላ ሠራዊት፤ በዳግማዊ አፄ ምኒልክ፣ በልዑል ራስ መኮንን እና በወሎው ራስ ሚካኤል ወታደሮች እየታገዙ ነበር።
የራስ ስብሃት እና የደጃዝማች ሀጎስ ተፈሪ ጦርም ከራስ አሉላ እና ከራስ መንገሻ ጦር ጋር ተቀላቅለዋል፡፡
በጦርነቱ መሀል ራስ አሉላ ከጀነራል ዳቦርሜዳ ጋር በመዋጋት ላይ ሳሉ የወሎው ራስ ሚካኤል ወታደሮች ራስ አሉላን ለማገዝ ተንቀሳቅሰዋል፡፡
ከዚህም በላይ የኦሮሞ ፈረሰኞችም ራስ አሉላን ለመርዳት ከአዲኋላ አቅጣጫ የሚጠበቀውን የጣሊያን ጦር እንዳይጠናከር በመግታት ረገድ በብቃት ተወተዋል።
የአድዋ ጦርነት በዕለተ ሰንበት ዕሁድ ቀን የካቲት 23 ቀን 1988 ዓ.ም. ከጠዋቱ 12 ሰዓት ላይ የጀመረ ሲሆን ጦርነቱ እስከ እኩለ ቀን ድረስ ቀጥሎ ከሰዓት በኋላ በ10 ሰዓት አካባቢ የኢትዮጵያውያን ድል ማድረግ እርግጠኛ ሆነ፡፡
በዚህን ወቅት ከጦርነቱ የተረፉት የኢጣሊያ ወታደሮች ማፈግፈግ ሲጀምሩ ራስ አሉላ የሚያፈገፍጉትን የጣሊያን ወታደሮች ማርኮ ለመያዝ እንዲቻል የኦሮሞ ፈረሰኞች እንዲላኩላቸው ለአፄ ምኒልክ መልእክት ልከው ነበር፡፡
ኢትዮጵያውያን ከያሉበት በአንድነት በመሰባሰብ አድዋ ላይ ተሰልፈው የጋራ ጠላትን ድል ለማድረግ መቻላቸው በዘመናዊቷ የኢትዮጵያ ታሪክ ውስጥ የመጀመሪያው የታሪክ ምዕራፍ ሆኖ ሊመዘገብ ችሏል፡፡
ይህን ገሀድ እውነታ መሰረት በማድረግ፤ ራስ አሉላ የአፄ ምኒልክን ንጉሠ ነገሥትነት ከልባቸው ለመቀበል አንገራግረው የነበረ ቢሆንም፤ ከዐድዋ ድል በኋላ ግን ምኒልክ ለኢትዮጵያ አነድነት መረጋገጥ ዋስትና መሆኑን በማመናቸው የአፄ ምኒልክን ሉዓላዊ ንጉሠ ነገሥትነት ሙሉ በመሉ አምነው ተቀብለዋል፡፡
አውጉስቶስ ዋይልድ የተባለው በጦርነቱ ግንባር የነበረ ዘጋቢ፤ ራስ አሉላ ስለነበራቸው የውጊያ ስልትና የጦር አመራር ብቃት ሲናገር፤
“…አሉላ በራስ መንገሻ ዮሐንስ ጦር የታገዘ ጦሩን ይዞ ጣሊያኖች ወደተቆጣጠሩት የኢትዮጵያ ሰሜን አቅጣጫ መዝመት ቢፈቀድለት ኖሮ፤ የሐማሴንን አምባ እና የቦጎስን ግዛት በሙሉ፣ ከአዲ-ኡግሪ፣ አስመራ እና ከረን ከመሸጉት የኢጣሊያ ምሽጎች በስተቀር ሙሉ በሙሉ በውጊያ አሸንፎ በመቆጣጠር አብዛኛው ይዞታ በአቢሲኒያ ስር መውደቁ ጥርጥር የለውም ነበር።” በማለት አስተያየቱን ሰቷል፡፡
ራስ አሉላ በዐድዋ ድል ከፍተኛ ደስታ የተሰማቸው ቢሆንም ቅሉ፤ ጠላትነቱ ለኢትዮጵያ ብቻ ሳይሆን በግላቸውም ጠላታቸው የነበረውን ጀነራል ባራቲየሪን ከነሕይወቱ ማርከው ባለማያዛቸው ፀፀት ይሰማቸው እንደነበረ ይነገራል፡፡

8. ሕልፈተ ሕይዎት

ራስ አሉላ በመጨረሻ የሕይዎት ዘመናቸው ጡረታ በመውጣት በአንፃራዊነት የተረጋጋ ህይወትን ለመምራት መርጠው እንደነበር ቢታወቅም ቅሉ፤ በሚያሳዝን ሁኔታ የተረጋጋ ህይወትን መምራት ግን አልቻሉም።
ይልቁንም ከተምቤኑ ራስ ሐጎስ ጋር ሲዋጉ ራስ ሐጎስ በጦርነቱ ሲሞቱ፤ ራስ አሉላ ግን እግራቸው ላይ በጠና ቆስለው ስለነበር ልክ ከአድዋ ድል አሥራ አንድ ወራት በኋላ የካቲት 9 ቀን 1889 ዓ.ም. ሕይወታቸው ሊያልፍ ችሏል፡፡






ምንጭ፤
  1. "የኢትዮጵያ ታሪክ ከ 1847 እሰከ 1983"  ደራሲ፡- ፕሮፌሰር ባሕሩ ዘውዴ 2003 ዓ.ም.
  2. Credit to: Ghelawdewos Araia  africanidea.org
  3. Credit to: Haggai E rlicfi 1875 - 1897  A Political Biography of Ras Alula
  4. ከዊኪፒዲያ የተተረጎመ
  5. የትረካው አጃቢ ሙዚቃ፣ ዋሽንት - በአንሙት ክንዴ   ዩቲውብ