Content-Language: am የሴት አርበኛ ወይዘሮ ከበደች ስዩም መንገሻ
header image




የሴት አርበኛ ወይዘሮ ከበደች ስዩም መንገሻ



የሴት አርበኛ ወይዘሮ ከበደች ስዩም
መንገሻን የአርበኝነት ታሪክ ያዳምጡ















1. ትውልድና ጋብቻ

King Tekle Haymanot of Gojam
የሴት አርበኛ ወይዘሮ
ከበደች ስዩም መንገሻ
ከበደች ስዩም ፤ የአፄ ዮሐንስ 4ኛ የልጅ ልጅ ከሆኑት ከአባታቸው ከራስ ስዩም መንገሻ እና ከእናታቸው ከወይዘሮ ጀንበር በርኸ መቀሌ ከተማ ጥቅምት 17 ቀን 1904 ዓ.ም ተወለዱ፡፡
ከበደች ስዩም በተወለዱበት አካባቢ ፊደል ከቆጠሩ በኋላ ገና በለጋ እድሜያቸው የልዑል ራስ ካሣ ኃይሉ ዳርጌ ልጅ ከሆኑት ከደጃዝማች አበራ ካሣ ጋር ጋብቻ ፈፀሙ፡፡
ልዑል ራስ ካሳ ኃይሉ የዳግማዊ አፄ ምኒልክ አጎት የሆኑት የርዕሰ መኳንንት ራስ ዳርጌ ሳሕለሥላሴ የልጅ ልጅ ናቸው፡፡
የደጃዝማች አበራ ካሳ እና የወይዘሮ ከበደች ስዩም ጋብቻ በአፄ ዮሐንስ ፬ኛ የልጅ፣ ልጅ፣ ልጅ እና በዳግማዊ አፄ ምኒልክ የአጎት የልጅ ልጅ መካከል የተደረገ የጋብቻ ትስስር ነው፡፡
ሁለቱ ጥንዶች አብረው በመኖር ሕይወታቸውን በመምራት ላይ እያሉ ነበር ፋሽስት ኢጣሊያ ኢትዮጵያን ለሁለተኛ ጊዜ ወረራ የፈፀመው፡፡

2. የወይዘሮ ከበደች ስዩም ለአርበኝነት መነሳሳት

King Tekle Haymanot of Gojam
በሰላም እጃቸውን ከሰጡ በኋላ በፋሽስት
ወታደሮች የተረሸኑት የወይዘሮ ከበደች ሥዩም
ባለቤት ልዑል ደጃዝማች አበራ ካሣ
ማይጨው ላይ የኢትዮጵያ ጦር ሽንፈት ከደረሰበት በኋላ የልዑል ራስ ካሣ ኃይሉ ዳርጌ ልጆች የሆኑት ልዑል ደጃዝማች አበራ ካሳና ወንድማቸው ልዑል ደጃዝማች አስፋወሰን ካሣ በፍቸና በሙገር ሸለቆዎች ጥቂት ጦር ይዘው ወራሪውን ፋሽስት ለመፋለም ለወራት በሽምቅ ውጊያ ተሰማርተው ጠላትን በመታገል ላይ ነበሩ፡፡
በኋላም ሁለቱ ወንድማማች አርበኞች በጠላት የቀረበላቸውን በሠላም እጅ የመስጠት ሀሳብ ተቀብለው ከገቡ፤ ምንም ነገር እንደማይደርስባቸው በራስ ኃይሉ ተክለ ሃይማኖት ማረጋገጫ ከተሰጣቸው በኋላ ወደ ፍቼ ከተማ ታህሳስ 12 ቀን 1929 ዓ.ም. እጃቸውን ሰጡ፡፡
ራስ ኃይሉ ተክለ ሃይማኖት፤ የኢጣሊያ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትርን እና የኢትዮጵያ ጠቅላይ ገዥ የነበረውን ሩዶልፎ ግራዚያኒን ወክለው ለሁለቱ አርበኞች ንግግር አድርገውላቸው ነበር፡፡
ራስ ኃይሉ ተክለ ሃይማኖት፤ የደጃዝማች አበራ ካሣ ወንድም ለሆኑት ለደጃዝማች አስፋወሰን ካሣ የሚስታቸው አባት ወይም አማቻቸው ነበሩ፡፡
ደጃዝማች አበራ ካሣም በገዛ አማቻቸው በልዑል ራስ ስዩም መንገሻ ዮሐንስ ዋስትና ተሰቷቸው ነበር።
ሆኖም ሁለቱ ወንድማማቾች ትጥቃቸውን ፈተው በምርኮ ከቆዩ በኋላ በፋሽስት ወታደሮች ፍቼ ከተማ ውስጥ ወደሚገኘው ገበያ በመውሰድ ሕዝብ በተሰበሰበበት በጥይት ደብድበው ተገደሉ፡፡
በዚህን ውቅት ነው እንግዲህ የሦስት ወር እርጉዝ የነበሩት ወይዘሮ ከበደች ስዩም፤ የባለቤታቸውን የደጃዝማች አበራ ካሣን በፋሽስቶች መገደል በሰሙ ጊዜ፤ የደረሰባቸውን ግፍ አሜን ብለው መቀበል ስላልቻሉ ቀደም ብሎ የተወለደውን የ8 ዓመት ልጃቸውን ይዘው በ25 ዓመት የወጣትነት እድሜያቸው ወደ ጫካ ገብተው ጠላትን ለመታገል የወሰኑት፡፡
ወይዘሮ ከበደች ስዩም ሀሳባቸውን ሲገልጹ፤
“...ለሀገሬ ክብርና ነፃነት ጠላትን እስከመጨረሻው ለመፋለም የነበረኝን እቅድ ወደ ተግባር ለመለወጥ ለራሴ ሙሉ ድፍረትን አላበስኩኝ፡፡
...አብረውኝ ከሚፋለሙ አርበኞች የተለየሁ ለመሆን ልክ አንድ ወንድ መደበኛ የጦር ወታደር የሚለብሰውን ልብስ ለበስኩ፡፡ መሣሪያየንም ታጠኩ፡፡
...አብረውኝ ከጠላት ጋር የሚዋደቁት አርበኞች እንደ አንድ ታላቅ የጦር መሪ ያዩኝና ያከብሩኝም ነበር፡፡”
በማለት ተናግረዋል፡፡

3. የወይዘሮ ከበደች ስዩም የአርበኝነት ዘመን አጀማመር

ወይዘሮ ከበደች ስዩም የአርበኝነት ተግባራቸውን የጀመሩት፤ ባለቤታቸው ደጃዝማች አበራ ካሣ በሰሜን ጦር ግንባር እየተዋጉ ባለበት ወቅትና ፋሽስት ኢጣሊያ አዲስ አበባን ከመቆጣጠሩ በፊት ነበር፡፡
ወይዘሮ ከበደች ስዩም፤ ባለቤታቸውን ተክተው የሰላሌን ግዛት ሠላምና ፀጥታ ከማስከበራቸውም በላይ የእርሳቸው ተከታዮች በጠላት ፕሮፓጋንዳ እንዳይታለሉ ፀረ ፋሽስት ቅስቀሳ አድረገዋል፡፡
ጠላትም አገሪቱን የራሱን መሣሪያ ማከማቻ በማድረግ አገር አፍራሽ ተግባራትን እንዳይፈጽም ሕዝቡ እንዲታገል ቀስቅሰዋል፡፡
ባለቤታቸው ደጃዝማች አበራ፤ ከሰሜን ጦር ግንባር ከተመለሱ በኋላ ባለቤታቸውን እና ቆስሎ የተመለሰውን የወገን ጦር በመንከባከብ እና ስንቅ በማቅረብ ረገድ ከፍተኛ አስተዋጽዖ አበርክተዋል፡፡
በ1928 ዓ.ም. አዲስ አበባን የተቆጣጠረውን የፋሽስት ጦር ለማሶጣት ተካሂዶ በነበረው ውጊያ (ኦፐሬሽን)፤ ወይዘሮ ከበደች ስዩም ከባለቤታቸው ሳይለዩ ከፍተኛ የአርበኝነት ተሳትፎ አድርገዋል፡፡
አዲስ አበባን ከጠላት ይዞታ ለማስለቀቅ የተካሄደው ውጊያ ውጤት ሳያስገኝ በመቅረቱ፤ በውጊያው ላይ የተካፈሉት የአርበኞች መሪወች እጃቸውን በሠላም እንዲሰጡ ፋሽስት ተደጋጋሚ ጥሪ ማቅረቡን ቀጠለ፡፡
ደጃዝማች አበራ፤ ጠላት ያቀረበላቸውን ጥያቄ ከመቀበላቸው በፊት ከወንድማቸው ከደጃዝማች አስፋወሰን ጋር ለመማከር ባለቤታቸውን ወይዘሮ ከበደች ስዩምን አዲስጌ ወደተባለ አገር ልከዋቸው ነበር፡፡
በኋላም ደጃዝማች አበራ ለባለቤቱ በጻፈው ደብዳቤ፤ “የጠላትን ጥሪ ሳልቀበል ብቀር በወገኖቸ ላይ እልቂት ይደርሳል ብየ በመፍራት ለጠላት እጀን መስጠት አልፈልግም፡፡” ብለው ነበር፡፡
የኋላ ኋላ ግን ሁለቱም ወንድማማቾች እጃቸውን ለጠላት አሳልፈው ቢሰጡም ከሞት ሊተርፉ አልቻሉም፡፡
ወይዘሮ ከበደች ስዩምም በባለቤታቸውና በባለቤታቸው ወንድም ላይ የተፈፀመውን ግድያ ሲሰሙ ከፍተኛ ቁጭትና ሐዘን ስለተሰማቸው የባለቤታቸውን ደም ለመበቀል ቆርጠው ተነሱ፡፡
ጠላትም ወይዘሮ ከበደች ስዩምን በተደጋጋሚ በማስጠንቀቅ እጃቸውን ለመያዝ ሙከራ ቢያደርግም አልተሳካለትም፡፡
ወይዘሮ ከበደች ስዩም የንጉሣዊ ቤተሰብ አባል በመሆናቸው በአጭር ጊዜ ውስጥ ከፍተኛ ቁጥር ያለው ተዋጊ ጦር ለማሰለፍ ችለዋል፡፡
እርሳቸው ካሰለፉት ጦር ጋር የባለቤታቸው ተዋጊ ጦር፣ ሁለቱ ልጆቻቸው እና አሽከሮቻቸው የሚገኙበት ቁጥሩ የማይናቅ ተዋጊ ሠራዊት አደራጅተው ስለነበር ለጠላት አስጊ ሆነው ተገኙ፡፡
ወይዘሮ ከበደች ስዩም በእንሳሮ፣ በመረሀቤቴ፣ በሜዳና በዓለም ከተማ አካባቢ በመዘዋወር የአካባቢው ሕዝብ በጠላት ፕሮፓጋንዳ ተታሎ ትጥቁን እንዳይፈታ በመቀስቀስ በአጭር ጊዜ ውስጥ በርካታ ተከታዮችን አፈሩ፡፡
የፋሽስት ኢጣሊያ የጦር ሾማምንቶች “ይህች ጥቁር ደም ሴት” ብሎ ወደሚጠራት እና አለች ወደተባለችበት ሥፍራ ሁሉ ዘመናዊ የጦር መሣሪያ የታጠቀ የጠላት ጦር ደጋግሞ በማዝመት ከበደች ስዩምን በምርኮ ለመያዝና የአርበኞችን ሞራል ለመስበር ቢፍጨረጨርም አልተሳካለትም፡፡
ይሁን እንጅ ጀግናዋ አርበኛ ከበደች ስዩም ጠላት በሚያደርስባቸው ከባድ ውጊያ ሳይደናገጡ ከበርካታ ተከታይ አርበኞቻቸው ጋር በመሆን ጠላትን መግቢያ መውጫ በማሳጣት ለሀገራቸው ነፃነት የማይጨበጡ ቆራጥ ጀግና ሴት ሆኑበት፡፡
ጀግናዋ አርበኛ ከበደች ስዩም ሲናገሩ፤
“እኔ ሴት አርበኛዋ ከበደች ስዩም ለጠላት አልበገርም፡፡ እናንተ ጀግኖች አርበኞች ደግሞ ከጎኔ ከሆናችሁ የበለጠ ታሪክ እሠራለሁ፡፡”
በማለት ለአርበኞቻቸው የማነቃቂያ ንግግር በማድረግ ትግላቸውን ይበልጥ እያፋፋሙ ቀጠሉ፡፡
Woizero Kebedech Seyoum

የኢጣሊያ ፋሽስት ጦር ቁጥሩ እስከ 40 ሺህ የሚደርስ ተዋጊ ኃይል በአርበኛዋ ከበደች ስዩም ላይ በተደጋጋሚ አዝምቷል፡፡
ወይዘሮ ከበደች ታዋቂ ከሆኑት የሸዋ አርበኞች መሪዎች ማለትም፤ ከራስ አበበ አረጋይ፣ ከደጃዝማች ዘውዴ አስፋው እና ከሻለቃ መስፍን ስለሺ ጋር ተደጋጋሚ ግንኙነት በማድረግና በጋራ በመሰለፍ ብዙ ጊዜ በጠላት ላይ ተደጋጋሚ ጥቃቶችን ያደርሱ ነበር።
በአርበኛዋ ከበደች ስዩም የሚመራው ጦር፤ መንዝ፣ ተጉለት፣ ይፋት፣ ሰላሌ፣ መረሐቤቴ፣ ጃርሶ፣ ቢሻንጆሊ እና ግንደ ብረት፣ በተባሉ ሥፍራዎች እየተዘዋወሩ በጠላት ጦር ላይ ድንገተኛ ጥቃት በመሰንዘር በርካታ የኢጣሊያ ወታደሮችንና ከጠላት ጦር ጋር ወግነው የተሰማሩትን ባንዳዎችን ሙትና ቁስለኛ በማድረግ በርካታ የጦር መሣሪያዎችን በመማረክና የጠላትን የስንቅና ትጥቅ ክምችቱን በማውደም በጠላት ላይ ከፍተኛ ጉዳት አድርሰዋል፡፡
በጥቂት ወራት ውስጥ አርበኛዋ ከበደች ስዩም የፈፀሙትን የጀግንነት ተጋድሎ የሰሙ አርበኞች እና ሌሎች ነዋሪዎች በጀግነዋ ቆራጥ ተግባር በመነሳሳት እነርሱም ጠላትን በቆራጥነት ለመፋለም ትልቅ የሞራል ስንቅ ሆኗቸዋል፡፡
አርበኛዋ ከበደች ስዩም እርግዝናቸው እየገፋ ቢያስጨንቃቸውም ፍጹም ጤነኛ በመምሰል ከወታደሮቻቸው ጋር በአይበገሬነት ጠላትን ይፋለሙ ነበር፡፡
አርበኛዋ ከበደች ስዩም ለአርበኞቻቸው አመራር በመስጠት በተከታታይ ድል ሲያስመዘግቡ ቆይተው ሐምሌ 1 ቀን 1929 ዓ.ም. ዱላ ቀርቻ በተባለ በርሀ ከጠላት ጦር ጋር ከባድ ውጊያ በተካሄደበት ወቅት በውጊያ መካከል ልጃቸውን ተገላገሉ፡፡
ልጃቸውንም በሰላም የተገላገሉት በሚዋጉበት በርሃ ውስጥ ሲሆን ስሙንም ታሪኩ ብለው ሰይመውታል፡፡
ልጃቸውን ከተገላገሉ በኋላም፤ የጦር አጋሮቻቸው፤ አርበኛ ከበደች ስዩምን የአራስነት ጊዚያቸውን ጥቂት ጊዚያት ተኝተው እንዲያሳልፉ በማሰብ ወደ አንድ ደሳሳ ጎጆ አስገድደው በመውሰድ አራስ ልጃቸውን ይዘው እንዲተኙ አደረጓቸው፡፡
ሆኖም የጠላት አይሮፕላኖች ደርሰው እርሳቸው በተኙበት አካባቢ በቦምብ መደብደብ ሲጀምሩ አርበኛዋ ከበደች ስዩም ለጥቂት ሲተርፉ ከእረሳቸው ጋር የነበሩ የተወሰኑት አርበኞቻቸው ላይ የሞትና የመቁሰል አደጋ ደርሶባቸዋል፡፡
Ethiopian Woman Patriot Kebedech Seyoum
የአርበኛዋ የከበደች ስዩም ልጆች

Photo link
አርበኛዋ ከበደች ስዩምም ወዲያውኑ አራስ ልጃቸውን ይዘው የሸዋን ጠቅላይ ግዛት ለቀው በጊዜው ወለጋ ላይ በሆለታ የዘመናዊ ውትድርና ሳይንስ የተማሩ የክቡር ዘበኛ አባላት “የጥቁር አነበሳ ጦር” የተሰኘ ተዋጊ ጦር እያደራጁ መሆኑን ስለሰሙ ጦራቸውን ይዘው ወደ ሥፍራው አመሩ፡፡
በአርበኛዋ ከበደች ስዩም የተመራው ጦር ወደ ወለጋ ዘልቆ በመግባት በሆሮ ጉድሩ፣ በቡዬ፣ በሊሙ እና በደረሱበት ስፍራ ሁሉ ከፋሽስት ጦር ጋር ባደረጓቸው ውጊያዎች ከፍተኛ ጀብዱዎችን በመፈፀም ከበባ ውስጥ አስገብቷቸው የነበረውን የጠላት ጦር ሰብሮ በመውጣት እና በምትኩ ጠላትን ከበባ ውስጥ በማስገባት የጠላትን ጦር ቀጥተው ከፍተኛ ጀብዱ ፈጽመዋል፡፡
ከበደች ስዩምን ማሸነፍ ያቃተው የጠላት ጦር የሚያደርገው ሲያጣ፤ ከበደች ስዩም በሠላም የሚገቡ ከሆነ ምህረት እንደሚያደርግላቸው መልእክት ቢልክም ከበደች ስዩም ግን አርበኛው ባለቤቴ እና የየልጆቸ አባት በግፍ ተገድሎ፣ እናት ሀገሬ በጠላት እጅ ወድቃ፣ ወገኔ በባርነት ቀንበር ተጠምዶና ይህ ሁሉ ግፍና መከራ እየተፈጸመ እኔ ከጠላት ጋር ታርቄ በፍጹም ልገባ አልችልም በማለት በቆራጥነት የአርበኝነት ትግላቸውን ቀጠሉበት፡፡

እስከ 1931 ዓ.ም. ድረስ በጎጃም ጠቅላይ ግዛት ከጦር አርበኞቻቸው ጋር ሆነው በተለያዩ ሥፍራዎች እየተዘዋወሩ ጠላትን ሲዋጉና ሲያዋጉ ከቆዩ በኋላ ከጥቂት የአርበኞች መሪዎች እና ከሁለት ልጆቻቸው ጋር ሆነው ወደ ሱዳን ተሰደዱ፡፡
በካርቱም ለወራት ከቆዩ በኋላ በለንደን በስደት ላይ ከሚገኙት ከግርማዊ ቀዳማዊ አፄ ኃይለ ሥላሴ ጋር ተላልከው ወደ ካይሮ ግብፅ እንዲያመሩ በታዘዙት መሠረት ወደ ካይሮ አመሩ፡፡
በኋላም፤ ፋሽስት ኢጣሊያ ከኢትዮጵያ ተሸንፎ እስኪወጣ ድረስ በካይሮ ከቆዩ በኋላ፤ በደቡብ ኢትዮጵያ አቅጣጫ በሱማሊያ በኩል የዘመተው የእንግሊዙ የጦር መሪ ጄኔራል ካኒንግሀም፤ በኢትዮጵያ አርበኞች በመታገዝ አዲስ አበባን መቆጣጠር በመቻሉ የኢጣሊያ ፈሽስት ጦር ከመዲናዋ ከአዲስ አበባ ከተማ መጋቢት 28 ቀን 1933 ዓ.ም. ለቆ ሲወጣና የኢትዮጵያ ድል አድራጊነት ሲረጋገጥ ወይዘሮ ከበደች ስዩም ወደ ሀገራቸው ወደ ኢትዮጵያ ለመመለስ ቻሉ፡፡
ወደ ሀገራቸው ከተመለሱም በኋላ ለፈፀሙት ታላቅ የአርበኝነት ጀብዱ ከንጉሠ ነገሥቱ አምስት ከፍተኛ ኒሻንና ሜዳሊያዎችን ተሸልመዋል፡፡
ወይዘሮ ከበደች ስዩምም የልዑል ሚስት በመሆናቸው “እመቤት ሆይ” ተብለውም የልዑላን ሚስቶች በሚጠሩበት መጠሪያ እንዲጠሩ የማዕረግ ሥም ተሰቷቸዋል፡፡
አርበኛዋ ከበደች ስዩም በታህሳስ ወር 1971 ዓ.ም. በተወለዱ በ67 ዓመት እድሜያቸው ከዚህ ዓለም በሞት ተለይተዋል፡፡
በየካቲት ወር 2000 ዓ.ም. በሮም ከተማ የተቋቋመው የሴቶች ላቦራቶሪ በተለይ የሴቶችን የጸረ ፋሽስት ትግልን በመወከል ለቆራጧ የሴት አርበኛ ለወይዘሮ ከበደች ስዩም መታሰቢያነት ሲባል፤ በአርበኛዋ በከበደች ስዩም ስም እንዲጠራ ተደርጓል፡፡

አገር ወዳድ እና ቆራጥ አርበኛዋ ከበደች ስዩም፤ ሴት መሆናቸው ሳያግዳቸው ለእናት አገራቸው ነፃነት ሲሉ ለአራት ዓመታት ያህል በዱር በገደሉ ከአገር አገር በመዘዋወር ተከታይ አርበኞቻቸውን እየመሩ ጠላትን መግቢያ መውጫ በማሳጣት ያበረከቱት የአርበኝነት ተጋድሎ ለአገር ወዳድ ሴቶች ሁሉ አርዓያና ተምሳሌት ሆኖ በትውልድ ሁሉ ሲዘከር ይኖራል፡፡




ምንጭ፤
  1. “ቀሪን ገረመው የአርበኞች ታሪክ”  ደራሲ፤ ቀኛዝማች ታደሰ ዘወልዴ 1960 ዓ.ም.
  2. Africaportal   ምስጋና፤ ለምናለ አዱኛ  africaportal.org
  3. 623 channel   ዩቲውብ ሊንክ
  4. Addis 1879/አዲስ 1879   ዩቲውብ ሊንክ
  5. የትረካው አጃቢ ሙዚቃ፣ ዋሽንት - በአንሙት ክንዴ   ዩቲውብ