Content-Language: am ራስ መኰንን ወልደ ሚካኤል
header image


ልዑል ራስ መኰንን ወልደ ሚካኤል (አባ ቃኘው)



የልዑል ራስ መኮንን ወልደ ሚካኤል
(አባ ቃኘው) የአርበኝነትና የሕይወት ታሪክ













1. ትውልድና የሕይዎት ጉዞ

Leul Ras Mekonnen Woldemikael
ልዑል ራስ መኮንን ወልደ ሚካኤል
በጣሊያን ናፖሊ ከተማ የተነሱት ፎቶ
ልዑል ራስ መኮንን ወልደ ሚካኤል ወልደ መለኮት በመንዝ አውራጃ በአንኮበር ወረዳ ውስጥ ደረፎ ማርያም በምትባል ስፍራ ግንቦት 2 ቀን 1844 ዓ.ም. ተወለዱ፡፡
እናታቸው ወይዘሮ ተናኝወርቅ ሳህለ ስላሴ፤ የዳግማዊ ምኒልክ አክስት ናቸው፡፡
አባታቸው ደጃዝማች ወልደ ሚካኤል ወልደ መለኮት ይባላሉ፡፡
አባታቸው ደጃዝማች ወልደ ሚካኤል፤ እንደ ሸዋው ንጉሥ ኃይለ መለኮት እና እንደ ንጉሥ ሳህለ ስላሴ ያሉ ታዋቂ አርበኛ ሲሆኑ የወግዳ እና የዶባ ባላባት ነበሩ፡፡
አባታቸው ደጃዝማች ወልደ ሚካኤል ልጃቸውን መኮንንን በ14 ዓመታቸው በወቅቱ የሸዋ ንጉሥ ለነበሩት ለንጉሥ ምኒልክ ወስደው አስረከቧቸው፡፡
መኮንን ወልደ ሚካኤልም ቀስ በቀስ የምኒልክ ልዩ ጓደኛ ሆኑ፡፡
የሐረር ግዛት ወደ ኢትዮጵያ ግዛት ከተካተተ በኋላ በአጎታቸው ልጅ በሆኑት በዳግማዊ ምኒልክ በ1879 ዓ.ም. እንዲያስተዳድሩት ተሰጣቸው፡፡
የትግራይ ገዥ የነበሩት ራስ መንገሻ ዮሐንስ ከዳግማዊ ምኒልክ ጋር ግጭት ውስጥ በመግባታቸው የትግራይ አስተዳደርም በተጨማሪ ተሰጥቷቸው ነበር፡፡
ልዑል ራስ መኮንን በለንደን የንጉሥ ኤድዋርድ ስምንተኛን የዘውድ ክብረ በዓል ላይ ተገኝተዋል፡፡
እግረ መንገዳቸውንም፤ ጣሊያንን፣ ፈረንሳይን፣ ቱርክንና ጀርመንን ጎብኝተዋል፡፡
በ1898 ዓ.ም. ተፈሪ መኮንን ከመወለዳቸው አስቀድሞ የተወለዱት ደጃዝማች ይልማ መኮንን የሐረር ገዥ ሆነው አባታቸውን ልዑል ራስ መኮንን ተክተው ነበር ፡፡
Ras Makonnen and His Son Teferi
ራስ ምኮንን እና ልጃቸው ተፈሪ መኮንን
ይልማ መኮንን የተወለዱት፤ ልዑል ራስ መኮንን የተፈሪ መኮንን እናት ከሆኑት ከወይዘሮ የሺማቤት አሊ ጋር ከመጋባታቸው በፊት ነበር ፡፡
ራስ መኮንን፤ በ1865 ዓ.ም. አካባቢ የደጃዝማች አሊ እና የወይዘሮ ወለተ ጊዮርጊስ ልጅ የሆኑትን ወይዘሮ የሺመቤት አሊን አገቡ፡፡
ሐምሌ 16 ቀን 1884 ዓ.ም. ተፈሪ መኮንን ተወለዱ፡፡
በኋላም የይልማ መኮንን ታናሽ ወንድም የሆኑት ተፈሪ መኮንን በተራቸው የሐረር ገዥ እንዲሆኑ ሥልጣን ተሰጣቸው፡፡
የወይዘሮ የሺምቤት አሊን ህልፈት ተከትሎ በ1893 ዓ.ም. ራስ መኮንን ከእቴጌ ጣይቱ ብጡል የእህት ልጅ ከሆኑት ከወይዘሮ ምንትዋብ ወሌ ጋር ለአጭር ጊዜም ቢሆን ከተጋቡ በኋላ ብዙም ሳይዘልቅ ተፋተዋል፡፡
ልዑል ራስ መኮንን አውሮፓን በጎበኙበት ወቅት በፓሪስ ውስጥ ካለው የፈረንሳይ የሾፌርነት ማሰልጠኛ ትምህርት ቤት ተምረው የመንጃ ፈቃድ ያገኙ የመጀመሪያው ኢትዮጵያዊ ነበሩ፡፡

2. የአምባላጌ ውጊያና የዐድዋ ጦርነት

ራስ መኮንን የጦር አበጋዝ (የጦር አዛዥ) ሆነው፤
  • ራስ አሉላን
  • ደጃዝማች ወልዴን፤
  • ፊታውራሪ ተክሌን፣
  • ሊቀ መኳስ አድነውን
  • ቀኛዝማች ታፈሰን
ይዘው ወደፊት ሲጓዙ ወዲያው የፋሽስት ኢጣሊያ ወታደሮች በመሸጉበት በአምባላጌ ተራራ አጠገብ ደረሱ፡፡
Leul Ras Mekonnen at Amabalagie battle front
"ለፐቲት ጆርናል" የተሰኘው የፈረንሳይ ጋዜጣ የልዑል ራስ
መኮንንን የአምባለጌ ውጊያ ሥዕል በዚህ መልኩ አቅርቦታል
ይህ የተፈጥሮ ምሽግ የሆነው አምባላጌ፣ በኢጣሊያ የጦር አዛዥ በሻለቃ ቶዞሊ የሚመራ ስለነበረ፤ ደም ከመፋሰሱ በፊት ስፍራውን በሰላም ለቀው እንዲወጡ የኢትዮጵያ ጦር ጠቅላይ አዛዥ ልዑል ራስ መኮንን ደብዳቤ ጻፉለት፡፡
ሻለቃ ቶዞሊ ግን ተጨማሪ የጦር መሣሪያና ወታደሮች ከተላኩለት በኋላ አለቅም የሚል መልስ ሰጠ፡፡
ከዚህ በኋላ ራስ መኮንን ወደፊት ገፍተው ህዳር 28 ቀን 1888 ዓ.ም. አምባላጌ ተራራ ጥግ ደረሱ፡፡
የቀሩትንም ራሶች ከእርሳቸው ቀኝና ግራ አሰልፈው፤ እርሳቸው እመሐል ሆነው ተራራውን ከበው ጦርነቱን ወዲያውኑ ጀመሩት፡፡
የግንባር ቀደም የጦር መሪው ጀግናው ፊታወራሪ ገበየሁ፤ የታመሙት ህመም ሳይገታቸው፤ ሠራዊታቸውን እየመሩ ሊታሰብ በማይችል ድፍረትና ወኔ የአምባላጌን አቀበት እየተዋጉ ወጥተው አምባላጌ ምሽግ ዘንድ ደረሱ፡፡
ስለምሽግም ሆነ ዘመናዊ የጦር ትምህርት የሌለው የኢትዮጵያ ሠራዊት አምባላጌ የመሸገውን የኢጣሊያ ጦር ምሽጉ ድረስ እየሄደ ባለው አሮጌ ጠመንጃ የጠላትን ወታደር ይቆላው ነበር፡፡
ከሁለት ሰዓት ውጊያ በኋላ የጠላት ጦር ድል ሆኖ መሸሽ ሲጀምር የኢትዮጵያ ወታደሮች እያባረሩ ሲዋጉ የፋሽስት ወታደሮች አለቃ የሆነው ሜጀር ቶሶሊ በ7 ጥይት ተመቶ ሲሞት የተረፈውም ፈርጥጦ ወደ መቀሌ መሸሽ ጀመረ፡፡
አንድ የኢጣሊያ የጦር አዛዥ ስለውጊያው ሲናገር፤
“...ጦርነቱ ዋጋ ያለው አይመስለኝም፡፡
...መድፎቻችን ያለማቋረጥ ሲተኮሱ፤ ጠላቶቻችን ሲወድቁ፤ ሲቆስሉና ሲሞቱ እናያለን፡፡
...ግን ጠላቶቻችን ብዛታቸው ሳይቀንስ እንዳሉ ሆነው ወደፊት ይመጡብናል፡፡
እጅግ በጣም ብዙ ናቸው፡፡ ...ግራና ቀኝ እንደቀለበት ከበውናል፡፡”

በማለት ጽፏል፡፡
Captured Italian at Amabalagie
ከአምባላጌ ምሽግ የተማረኩ የፋሽስት ወታደሮች
ጣሊያኖች የሚቆስሉባቸውን ወታደሮች ወደ መቀሌ ማጓጓዝ ቀጥለዋል፡፡
ራስ አሉላ ጦር የተወሰነውን የጣሊያኖች ምሽግ በመቆጣጠሩ፤ የጣሊያኖች ስቃይ እየበዛ ሄዶ ወደ መቀሌ የመሸሻ መንገዳቸውም ተዘጋ፡፡
ከአምባላጌ ምሽግ የጣሊያኖችን ሽሽት በተመለከተ፤ መሐመድ የተባለው ሶማሊያዊው የኢጣሊያ ወታደር ሲናገር፤
“...በቅሎ ጭነው ከሚጓዙ ሰዎች ጋር ተደባልቄ ስጓዝ፤ ...አበሾች በጥይት ተቀበሉን፡፡
ከየድንጋዩ ኋላ አበሾች ተደብቀው ኖሮ፤ ከላያችን ይተኩሳሉ፡፡ ከፊታችንም ይተኩሳሉ፡፡ ከጎናችንም ይተኩሳሉ፡፡ መድረሻ አሳጡን፡፡
በዚያ ላይ በቅሎዎች እየረጋገጡን ያልፋሉ፡፡
በግራና በቀኝ የኛ ወታደሮች ሬሳና ቁስለኛ ተከምሯል፡፡
የቆሰሉት ሰዎቻችን እርዱን! እርዱን! እያሉ ይጮሃሉ፡፡ ግን የሚሰማቸው የለም፡፡
በየትኛውም ቦታ አበሾች እየተከታተሉ ያለማቋረጥ ይተኩሱብናል፡፡
የእኛ መድፍ ተኳሾች ከእኛ ጋር ሲሸሹ ሳይ ተሰፋ ቆረጥኩ፡፡
...በጉዞዬ ላይ አንድም የኛን መኮንኖች አላየሁም፡፡
እኔም አንድ ቦታ ተደብቄ ራሴን አዳንኩ፡፡”

በማለት ገልጾታል፡፡
Leul Ras Mekonnen Woldemikael
ልዑል ራስ መኮንን ነሐሴ
ወር 1894 ዓ.ም. የተነሱት ፎቶ
በዚህ አይነት የአምባላጌው ጦርነት በኢትዮጵያውያን ድል አድራጊነት ተፈፀመ፡፡
በአምባላጌው ጦርነት ራስ መኮንን፤ ከራስ አሉላ፣ ከራስ ወሌ፣ ዋግሹም ጓንጉልና ፊታውራሪ ገበየሁ ጋር በአንድነት ሆነው በአካሄዱት ውጊያ፤ የኢጣሊያ ጦር አዛዡን ሻለቃ ቶሴሊን ጨምሮ፤
  • 19 የኢጣሊያ መኮንኖች፣
  • ሌሎች 20 የሚሆኑ የኢጣሊያ ባለሌላ ማዕረጎች እና
  • 1,500 ከአካባቢው የተመለመሉ የጣሊን ጦር ተዋጊዎች ተገድለዋል፡፡
  • እንዲሁም 3 መኮንኖችና እና
  • 300 ከአካባቢው የተመለመሉ የጣሊን ጦር ተዋጊዎች ቆስለዋል።
  • 1,300 የኢጣሊያ ጥቁር ወታደሮችና
  • 20 የጦር መኮንኖች መሞታቸውን ራሳቸው ጣሊያኖቹ አምነዋል፡፡
በሕይወት የተረፉት የጠላት ወታደሮች ወደ ሰሜን አቅጣጫ 35 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ ወደነበረው ከተማ እና መቀሌ ወደሚገኘው ምሽግ ሲሸሹ፤ የቀሩት በየስፍራው ተበታትነዋል።
ከአምባላጌ መሽግ ከሞት የተረፈው የኢጣሊያ ጦር ከ 15 ቀናት በኋላ መቀሌ ላይ ተሰበሰበ፡፡
ከተረፉትም መሀል፤ አንዳንዱ፤ ራሱ በሰይፍ የተገመሰ፣ ትከሻው የተቆረጠና በጥይት የቆሰለ ይገኙበታል፡፡

ልዑል ራስ መኮንን፤ ከራስ አሉላ፣ ከየጁው ራስ ወሌ ብጡል (የእቴጌ ጣይቱ ወንድም)፣ ከዋግሹም ጓንጉልና ከፊታውራሪ ገበየሁ (የዳግማዊ ምኒልክ የክብር ዘብ አዛዥ) ጋር በመሆን አምባላጌን ምሽግ ሰብረው በሚያስደንቅ የውጊያ ጥበብ ጠላትን ድል አድርገዋል፡፡
ከአምባላጌ ጦርነት የተረፈው የኢጣሊያ ሠራዊት ወደ መቀሌ በመሸሽ በቀላሉ የማይበገር ጠንካራ ምሽግ ሰርቶ ታጎረ፡፡
ራስ መኮንን ከአጋሮቻቸው ጋር ሆነው ወደፊት እየገፉ መቀሌ ምሽግ ደረሱ፡፡
ወዲያውኑ የመቀሌን ምሽግ ከበው በውጊ እያጣደፉ እጁን እንዲሰጥ ቢላክበትም እጀን አልሰጥም በማለቱ ራስ መኮንን ወደ ምሽጉ ተጠግተው ውጊያውን አፋፋሙት፡፡
ኢትዮጵያውያን በጀግንነት ቢዋጉም ቅሉ ምሽጉ በጣም የተደራጀ ስለነበረ ጦርነቱ ጊዜ ወሰደ፡፡
በዚህ መሐል በእቴጌ ጣይቱ ብልሐት የጣሊያኖቹ የመጠጥ ውሀ ጉድጓድ እንዲያዝ ስላደረጉ የኢጣሊያ ወታደሮች ጦርነቱን መቋቋም ስላልቻሉና ብዙ ሰው ስላለቀባቸው ምሽጉን ለመልቀቅ ፈቃደኛ ስለሆኑ፤ ዳግማዊ አፄ ምኒልክም፤ ለቅቄ እሄዳለሁ ካለ ይሂድ እንጅ አትንኩት ብለው ትእዛዝ ሰጡ፡፡
የኢትዮጵያ ወታደሮችም ብዙ መሣሪያዎችንና መድፎችን ለመማረክ ቻሉ፡፡
ልዑል ራስ መኮንን ከዳግማዊ ምኒልክ በተሰጣቸው የጦር አሰላለፍ መሠረት፤ የዐድዋ ከተማን ከተቆጣጠሩ በኋላ የመጨረሻው የዐድዋ ጦርነት ሲጀመር፤ ከራስ መንገሻ ዮሐንስ፤ ከወሎው ንጉሥ ሚካኤል፤ ከራስ ወሌ ብጡልና ከዋግሹም ጓንጉል ጋር በመሆን ቁጥሩ 18 ሺህ የሚጠጋውን ተዋጊ ጦር ይዘው ጉሶሶ በተሰኘው ተራራ ላይ አሰፈሩ፡፡
Statue of Leul Ras Mekonnen Woldemikael
በቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ ዘመነ መንግሥ በ 1951 ዓ.ም.
ራስ መኮንን አደባባይ የቆመው የልዑል ራስ መኮንን ሀውልት

Photo credit to:  equestrianstatue.org
ወታደሮቻቸውን በግማሽ ጨራቃ ቅርጽ በማሰለፍ፤ የአልቤርቶኒንና የዳቦር ሜዳን ጦር እንዳይገናኝ ቆርጠውና ከበው በመዋጋት በጠላት ላይ ከፍተኛ ጉዳት በማድረስ ለአድዋ ድል መገኘት ከፍተኛ የጀግንነት ሥራ ሠርተው ከዳግማዊ ምኒልክ ጋር ወደ አዲስ አበባ የተመለሱ እውቅ የጦር መሪ ነበሩ፡፡
ሐረር ከተማ ውስጥ በልዑል ራስ መኮንን አደባባይ እንዲቆም የተደረገው የልዑል ራስ መኮንን የነሐስ ሐውልት የተሰራው በተዋቂው ሰዓሊ ሜትር አርቲስት አፈዎርቅ ተክሌ የስዕል ንድፍ አውጭነትና በሁለት እውቅ የክሮሽያ የቅርፃ ቅርፅ ባለሙያዎች አማካኝነት ሲሆን፤ ሐውልቱ በስፍራው የቆመው በ1951 ዓ.ም. ነበር፡፡

ሆኖም የልዑል ራስ መኮንን የነሐስ ሐውልት በሰኔ ወር 2012 ዓ.ም. በአካባቢው ወጣቶች በተፈጠረው ረብሻና ሁከት ምክንያት ጥቂት ግለሰቦች በቡድን ተሰባስበው ሐውልቱን አፍርሰው ከቦታው ማንሳታቸው እጅግ አሳዛኝ ተግባር ሆኖ አልፏል፡፡

3. የልዑል ራስ መኮንን ሕልፈተ ሕይወት

ልዑል ራስ መኮንን ባደረባቸው ድንገተኛ ህመም ምክንያት በተወለዱ በ 53 ዓመታቸው ከዚህ ዓለም በሞት ተለይተዋል፡፡

ልዑል ራስ መኮንን በተፈጥሮ የታደሉት ዲፕሎማሲያዊ ስብዕና የነበራቸው ብልህ ሰው ነበሩ፡፡



ምንጭ፤
  1. "አጤ ምኒልክ"  ደራሲ፡- ጳውሎስ ኞኞ የካቲት ወር 1984 ዓ.ም.
  2. "የኢትዮጵያ ታሪክ ከ 1847 እሰከ 1983"  ደራሲ፡- ፕሮፌሰር ባሕሩ ዘውዴ
  3. "የኢትዮጵያ ታሪክ - ከአፄ ልብነ ድንግል እስከ አፄ ቴዎድሮስ"  ደራሲ፡- ተክለ ጻድቅ መኩሪያ 1961 ዓ.ም.
  4. ከዊኪፒዲያ የተተረጎመ
  5. የትረካው አጃቢ ሙዚቃ፣ ዋሽንት - በአንሙት ክንዴ   ዩቲውብ
  6. courtesy of: Rare WW2 Footage - German Infantry - No Music, Pure Sound  ዩቲውብ