Content-Language: am ዳግማዊ አፄ ምኒልክ ገጽ ሦስት
header image



(ገጽ 3)


ዳግማዊ አፄ ምኒልክ





1. የኢጣሊያ ጦር አሰላለፍ፤

የኢጣሊያ ጦር፤ እጅግ ዘመናዊ የጦር መሣሪያ የታጠቀና እንደ አልፒኒ ያሉ በተራራ ውጊያ የሠለጠኑትን ልዩ የውጊያ ኃይል ጨምሮ በደንብ የተደራጀ ጦር ነበር፡፡ የኢጣሊያ ጦር፤ የቅኝ ግዛት ወታደሮችን ሳይጨምር፤
- 4 ብርጌዶችን የያዘ፤
- በ 4 የጦር ጀነራሎችና
- በ 3 ከፍተኛ የጦር መኮንኖች የሚመራ 17 ሺህ ወታደሮች ተሰልፈዋል፡፡
አሰላለፋቸውም፤
- በግራ በኩል፤ አራት ባታሊየን ጦር የያዘው ጀነራል አልቤርቶኒ፣
- በስተቀኝ በኩል፤ የ2ኛ ብርጌድ አዛዥ፤ ጀነራል ዳቦርሜዳ፣
- በመሐል፤ የምርጡ ብርጌድ አዛዥ፤ ጀነራል አሪሞንዲ፤
- በኋላ ደጀን የተሰለፈው የኤሌና ብርጌድ ነበር፡፡

2. የኢትዮጵያ ጦር አሰላለፍ፤

ንጉሠ ነገሥቱ ዳግማዊ አፄ ምኒልክ፤ ጦራቸው በሰፈረበት ሥፍራ በሚገኘው በቅዱስ ገብርኤል ቤተ ክርስቲያን፤ አቡነ ማቴወስ ሲቀድሱ ቆመው ያስቀድሱ ነበርና ቅዳሴ ከወጡ በኋላ ለኢትዮጵያ የጦር አዛዦች መመሪያ ሰጥተው ከዚህ በታች በተገለፀው መሠረት ሠራዊቱ እንዲሰለፍ አዘዙ፡፡
በዚህም መሠረት፤
  1. ንጉሠ ነገሥቱ ዳግማዊ አፄ ምኒልክ፤ ዐድዋ አጠገብ በተለይ ዐዲማህለያ ከተባለው በኢትዮጵያ ሠራዊት መሐል ከሚገኘው ሥፍራ 30 ሺህ ባለጠመንጃ ጦር አሰልፈዋል፡፡
  2. እቴጌ ጣይቱ ንጉሠ ነገሥቱ ካሉበት ሥፍራ ሆነው 3 ሺህ ባለጠመንጃ ጦር አሰልፈዋል፡፡
  3. ከንጉሠ ነገሥቱ በስተቀኝ፤ ፊታውራሪ ገበየሁ የአሰምን ወንዝ ተሻግረው 6 ሺህ ጦር አሰልፈዋል፡፡
  4. ልዑል ራስ መኮንን ወልደ ሚካኤል የሚመራው 15 ሺህ የሐረርጌ ጦር፤ አድዋ ከተማን ይዟል፡፡
  5. ንጉሥ ተክለሐይማኖት የሚመራው የጎጃም 3 ሺህ ጦር፤ ፊት ለፊት ወደሚገኘው የኢጣሊያ ጦር እንዲያመራ ተደረገ፡፡
  6. በራስ መንገሻ ዮሐንስ፣ በራስ አሉላ አባነጋና በራስ ሐጎስ የሚመራው የትግራይና የሐማሴን 3 ሺህ ጦር አዲ አቡን ላይ ተሰልፏል፡፡
  7. ራስ ሚካኤል የወሎን ሠራዊት እየመሩ 6 ሺህ ባለጠመንጃና 3 ሺህ ፈረሰኛ ጦር አሰልፎ ሶሎዳ ተራራን ይዟል፡፡
  8. ራስ ወሌና ዋግሥዩም ጓንጉል የኋላ ደጀን ሆነው 6 ሺህ ባለጠመንጃ አሰልፈዋል፡፡
  9. ራስ መንገሻ አቲከም 3 ሺህ ባለጠመንጃ አሰልፈዋል፡፡
  10. የኦሮሞ ፈረሰኞች ደግሞ፤ በ13 ኪሎ ሜትር ክልል የሚገኘውን የውሀ ምንጮች ሁሉ እየፈለጉ ከበው ይዘዋል፡፡

በዐድዋ ጦርነት የተሠለፈው የኢትዮጵያ ሠራዊት፤ ዘር፣ ቀለምና ሐይማኖት ሳይለይ ከሁሉም የኢትዮጵያ ምድር ማለትም፤ ከሰሜን፣ ከደቡብ፣ ከምሥራቅና ከምራብ አቅጣጫ ከሚገኙ ብሔሮችና ነገዶች የተውጣጣ፤ የኢትዮጵያን ሉዓላዊነት ለማስከበር ሲል በኢትዮጵያ መሪ በዳግማዊ አፄ ምኒልክ በታወጀው የጦርነት የክተት አዋጅ ጥሪ መሠረት ለአንድ ብሔራዊ ዓላማ በአገር ወዳድነት ፈቃደኛ ሆኖ የተሰለፈ ሠራዊት ነበር፡፡፡

የአድዋ ጦርነት ተጀመረ

Ethiopian Painting about Battle of Adwa
በዐድዋ ጦርነት ወቅት
የምኒልክ እና የጣይቱ ምስል

Image credit to: ReviewEthio
የኢጣሊያው ጦር ጠቅላይ አዛዥ ጀነራል ባራቲየሪ፤ የካቲት 23 ቀን 1988 ዓ.ም. ማለዳ በ 11 ሰዓት የኢጣሊያ ጦር ለውጊያ እንዲንቀሳቀስ አዘዘ፡፡
የራስ መንገሻ ዮሐንስ ሠራዊት በያዘው ቦታ በኩል፤ በጀነራል አልቤርቶኒ የሚመራው የኢጣሊው ጦር ሊያልፍ ሲል ተገናኝተው፤ ተኩስ ተከፍቶ ውጊያ ተጀመረ፡፡

ከጧቱ 12 ሰዓት ከሩብ ሲሆን፤ በጀነራል አልቤርቶኒ የሚመራው የኢጣሊያ ብርጌድ ጦር በሙሉ በኢትየጵያ ሠራዊት ስለተቋረጠ፤ የጀነራል ዳቦርሜዳ ብርጌድ እንዲረዳው ታዘዘ፡፡
ነገር ግን፤ እንዲረዳ የታዘዘው የጀነራል ዳቦርሜዳ ጦር፤ 800 ሜትር ያህል እንደተጓዘ እርሱም በኢትየጵያውያን ጦር ተያዘ፡፡
ሌላ መንገድ ቀይሮ ለመጓዝ ቢያስብም፤ ደራርና ናስራይ የተባሉ ሁለት ተራራዎች ፊት ለፊቱ እንደአጥር ሆነው ተገትረው ሊያሳልፉት አልቻሉም፡፡
ከጧቱ 2 ሰዓት ተኩል ሲሆን፤ የኢጣሊያው ጦር ጠቅላይ አዛዥ ጀነራል ባራቲየሪ፤ ፈረስ ላይ ተቀምጦ ጦሩን ለማበረታታት ሲንቀሳቀስ፤ ከውጊያው ሜዳ ቆስለው የተመለሱና የሸሹ ወታደሮች ሜዳውን ሞልተው በማየቱ በጣም ደነገጠ፡፡

የሸሹትንም ወታደሮች እንደገና ወደ ጦር ሜዳ እንዲመለሱ አዘዘ፡፡
Alpini Regiment
በተራራ ውጊያ የሠለጠነውና ልዩ የጦር መሣሪያ ታጥቆ
በዐድዋው ጦርነት ሽንፈትን የተከናነበው የጣሊያን
7ኛው ሬጅመንት ልዩ የአልፒኒ ጦር ይህን ይመስል ነበር
የኢጣሊያ ጦር፤ የጠመንጃ፣ የመትረየስና የመድፍ ጥይት በኢትዮጵያ ሠራዊት ላይ ሲያዘንብ ሜዳው ተናወጠ፡፡

ይህ ሁሉ ተኩስ እየተተኮሰ ግን፤ የኢትዮጵያ ሠራዊት በውጊያ መሀል ሰንጥቆ እየገባ የኢጣሊያንን ጦር ፈጀው፡፡
ይሁን እንጅ የጣሊያን ጦር ተስፋ በቆረጠ ኃይል እስከ ምሽቱ 12 ሰዓት ድረስ ሲዋጉ ከቆዩ በኋላ በመጨረሻ አዛዣቸው ጀነራል ዳቦርቤዳ በጥይት ደረቱን ተመቶ ወድቆ ትንሽ እንደቆየ ሞተ፡፡
የኢጣሊያ ጦር የመድፍ ተኩስም ከአንድ ሰዓት በኋላ ፀጥ አለ፡፡
ኢትዮጵያውያኑ ዝም አሰኙት፡፡
በጥቂት ሰዓታት ውጊያም፤ 81 የኢጣሊያ መኮንኖችና 48 የኢጣሊያ ወታደሮች ተገደሉ፡፡
የተረፉት የጠላት ወታደሮች በኢትዮጵያ ጦር ሲማረኩ፤ ቀሪዎችም ሸሽተው አመለጡ፡፡
Italian soldiers at Adwa
በኢጣሊያዊው ሰዓሊ የተሳለው
የአልፒኒ ወታደሮች በአድዋ ውጊያ ላይ
ሲጨፈጨፉ የሚያሳይ ስዕል
በዚህ የዐድዋ ጦርነት ቆራጡ ጀግና ተዋጊ ፊታውራሪ ገበየሁ (አባ ጎራው)፤ ከጠላት ጋር ከሚዋጋው ሠራዊታቸው ተለይተው እጠላት መሐል ገብተው ከቀኛዝማች ታፈሰ ጋር እየፎከሩ የጠላትን አንገት በጎራዴ ሲቆርጡ በድንገት በጥይት ተመተው ወደቁ፡፡
የጦር ምኒስትሩ ቆራጡ ጀግና ፊታውራሪ ገበየሁ፤ በዚሁ በዐድዋው ጦርነት በፈፀሙት ጀብዱ፤ ጠላት የዐድዋን ታሪክ በጻፈው መጽሐፍ ሳይቀር ጉብዝናቸውን ሳይደብቅ በገሀድ አረጋግጧል፡፡
የጦር መሪው ፊታውራሪ ገበየሁ በዐድዋው ጦርነት ወቅት በፈፀሙት አኩሪ ተግባር ስማቸው እስከ ዛሬ ድረስ በትወልድ ሁሉ ሲወሳ ይኖራል፡፡
ስለ ፊታውራሪ ገበየሁ፤ ከመሞታቸው አስቀድሞ ከዚህ የሚከተለው ግጥም ተገጥሞላቸዋል፡፡

  የዐድዋ ሥላሴን ጠላት አረከሰው
  ገበየሁ በሞቴ ግባና ቀድሰው፣

Galiano
በጦር ሜዳ የተገደለው
የኢጣሊያ ባታሊየን ጦር
መሪ ኮሎኔል ጋሊያኖ
በዚህ ጦርነት የኢጣሊያ ጦር የባታሊየኑ ጦር መሪ የነበረው ኮሎኔል ጋሊያኖም ፊቱ ላይ በጥይት ቆስሎ በኢትዮጵያ ሠራዊት ተማረከ፡፡
ተማርኮ ሲሄድም ደክሞት ወደቀ፡፡
በወደቀበት ሆኖ፤ “ግደሉኝ እንጅ ከዚህ ቦታ አልነቃነቅም” በማለቱ ኢትዮጵያውያኑ ጊዜ ላለማባከን ብለው በወደቀበት ገድለውት፤ ሌሎች ምርኮኞችን እየነዱ ሄዱ፡፡
የኤርትራ ምክትል አዛዥ ሮም ላለው የኢጣሊያ የጦር ሚኒስቴር ስለጦርነቱ ያስተላለፈው ቴሌግራም ሲያስረዳ፤
“...ጦራችን ያለምንም ችግር አድዋ ደርሶ፤ (የሠፈረውን የኢትዮጵያ ጦር) ሊይዝ ነበር፡፡
ግን ወዲያውኑ አበሾች ተኩስ ከፍተው አባረሩት፡፡ ሠረዊታችን በሙሉ ሸሸ፡፡
ለመሸሽ እንኳን የበቀቱት የመድፍ ተኩስ ሽፋን እየተሰጣቸው ነበር፡፡
...መድፎቻችን በሙሉ በጠላት እጅ ወደቁ፡፡"

ይላል፡፡
በዚህ የዐድዋው ጦርነት ወቅት በጠቅላላው የሞቱት፣ የቆሰሉትና የተማረኩት የጣሊያን ወታደሮች ቁጥርም ሆነ የሞተውና የቆሰለው የኢትዮጵያ ወታደሮች ቁጥር በተለያዩ የታሪክ ፀሐፍያን የተለያየ ሆኖ ይገለፃል፡፡
ሆኖም በታሪክ ጸሐፊው በተክለ ጻድቅ መኩሪያ የተገለፀውን ስንወስድ፤
1ኛ፡- ከጠላት ወገን፤
  1. 5,000 የኢጣሊያን ወታደሮች ሞተዋል፣
  2. 2,000 የሚሆኑ ከሀማሴን የመጡና ከተለያዩ አገሮች የመጡ ቅጥር ወታደሮች ሞተዋል፣
  3. 2,500 የኢጣሊያን ወታደሮች ቆስለዋል፣
  4. 2,400 የሚሆኑ የጣሊያን ወታደሮች በርካታ መድፎችና ጠመንጃዎችን እንደያዙ ተማርከዋል፡፡
2ኛ፡- ከኢትዮጵያ ወገን፤
በተለይ ተኝቶ መተኮስን እንደነውር ይቆጥረው ስለነበረ፣ ቆሞ ስለሚተኩስና በጨበጣ ውጊያ ፊት ለፊት ስለሚጋፈጥ፤ የሞተውና የቆሰለው የኢትዮጵያ ሠራዊት ቁጥር ከጠላት በርካታ እንደሆነ የታሪክ ጸሐፊያን ይተርካሉ፡፡
ሆነም ቀረም የሞተውና የቆሰለው የኢትዮጵያ ሠራዊት ብዛት እስከ 10 ሺህ ይደርሳል ተብሎ ይገመታል፡፡

በጦርነቱ ወቅት ለኢጣሊያ ጋዜጦች ተወካይ የነበረው ግለሰብ አገሩ ከተመለሰ በኋላ ስለጦርነቱ በጻፈው መጽሐፍ ላይ፤
ከአሜሪካ ወደ ኢትዮጵያ የተመለሰውና ዳግማዊ
አፄ ምኒልክ አድዋ ሲዘምቱ የታጠቁት ጎራዴ

ምስጋና፤ ለአዲስ ድምፅ ዜና - አዲስ አበባ  Photo Link
“...ከጧቱ ሁለት ሰዓት ተኩል ሲሆን፤ ሠራዊታችን በሙሉ ቦታውን እየለቀቀ ሸሸ፡፡
ጠላት በመስመር፣ በመስመር እየሆነ ይመጣብን ጀመር፡፡
...14 መድፎቻችን በጥድፊያ ይተኩሳሉ፡፡
ጀነራል አልቤርቶኒ፤ ማጥቃታችንን ትተን እንድንከላከል ትእዛዝ ቢሰጥም፤ የጠላት ጦር ግን በግምት 15,000 ሆኖ መጣብን፡፡
ንጉሡም ቀይ ጃንጥላቸውን አስይዘው በወታደሩ መሀል ነበሩ፡፡
...የጀነራል አልቤርቶኒ ወታደሮች በሙሉ ተያዙ፡፡
ጠላትም ቦታውን እያለፈ ወደፊት ገሠገሠ፡፡
ከጧቱ 3 ሰዓት ተኩል ሲሆን ሁሉም ተስፋ ቆረጠ፡፡
...ብዙ መኮንኖች አለቁብን፡፡
...የጀነራል አሪሞንዲም ጦር ብትንትኑ ወጣ፡፡
በያለበት ሩጫና መበታተን ሆነ፡፡
...3 መድፎች ለእኩል ሰዓት ያህል እንደተኮሱ በአበሾች እጅ ወደቁ፡፡
...የደጀኑ ተጠባባቂ ጦር ከጧቱ 4 ሰዓት ሲሆን ደርሶልን በአዲስ ጉልበት እየተዋጋ ሳለ፤ የአበሾቹ (የኦሮሞ) ፈረሰኛ ጦር መጣና ወረረው፡፡
ከዚህ በኋላ የኛ ወታደሮች ጸጥ አሉ፡፡ በሠፈራችንም ፀጥታው ነገሠ፡፡”

በማለት ገልጾታል፡፡
የኢጣሊያ ጦር ጠቅላይ አዛዥ ጀነራል ባራቲየሪ በኢትዮጵያ ጦር ተማርኮ ነበር፡፡
በኋላ ግን ተለቆ ወደ አገሩ ከተመለሰ በኋላ በሰጠው ጋዜጣዊ መግለጫ፤
Dabormeda
በአድዋ ጦርነት በጥይት ተመቶ
በትግራይ ምድር አስከሬኑ የተቀበረው፣
ስለጦርነት ጥበብ በርካታ መጻህፍትን
የጻፈውና የኢጣሊያ ጦር ትምህረት ቤት
ፕሮፌሰር የነበረው የ 53 ዓመቱ
ሜጀር ጀነራል ዳቦር ሜዳ
“...ጀነራል አሪሞንዲ ጉልበቱን ተመቶ ወደቀ፡፡
ኢትዮጵያውያኑ ሊማርኩት ሲመጡ በጎራዴው እየተከላከለ አልማረክ ቢላቸው ገደሉት፡፡
...እኛ ሥልጡን ነን የምንለው ወታደሮች ከኢትዮጵያውያን የምንማረው ትምህርት አለ፡፡
አበሾች ለባሩዱና ለጥይት ይሳሳሉ፡፡
ለመግደል ካልሆነ በስተቀር አይተኩሱም፡፡
ተደባልቀው በጎራዴ መምታት ይመርጣሉ እንጅ ጥይት ማበላሻት አይወዱም፡፡
ይህም በማስጮህ ብቻ ጥይት ለምናባክነው ለሰለጠነው ለእኛ ወታደር ጥሩ ትምህርት ነው፡፡
30 ኪሎ ሜትር ያህል ተጉዞ ከጦር ሜዳ የገባው መድፍ ተኳሽ፤ ገና አንድ ጥይት እንደተኮሰ ተገደለ፡፡
ይህም የሆነው ኢትዮጵያውያኑ በንዴት ተሞልተውና በብዛት መጥተው ስለወረሩት ነው፡፡
የተመካንባቸው ደጀን የነበሩት መድፎቻችንም ከአንድ ጥይት ተኩስ በኋላ ተማረኩ፡፡”

በማለት ተናግሯል፡፡


አለቃ ተክለሥላሴ ባልታተመው መጽሐፋቸው ስለ ኢትዮጵያ ሠራዊት ሲጽፉ፤
“...ያን ጊዜ መንገዱ ባይከፋና ሠራዊቱ በረሀብ ባይጎዳ ኖሮ ጣሊያን አንድም ለዘር አይተርፍም ነበር፡፡
...የብርታቱ ብርታት፤ ...በሌሊት ጨረቃ በዚያ በከፋ በትግራይ መሬት፤ በጠጠር፣ ባቀበት፣ በቁልቁለት፣ የጥይት ኮሮጆውንና የውሀ ታኒካውን ተሸክሞ፣
እንቅልፍ አጥቶ ሁለት ሌሊትና አንድ መዓልት ሲጓዝ አድሮ ሲነጋ ተኩስ ተጀመረ፡፡
ሲዋጋ ውሎ ማታ ተመልሶ ሲሄድ አድሮ አገሩ መግባቱ ያስደንቃል፡፡"
በማለት ገልጸውታል፡፡

ፕሮፌሰር አፈወርቅ ገብረየሱስም፤ “ዳግማዊ አፄ ምኒልክ” በሚለው መጽሐፋቸው ሲጽፉ፤
“...ጦርነት ተጀመረ፡፡ የኢጣሊያ መድፍ ነው በማለዳ የቀሰቀሰው፡፡
...ኢትዮጵያዊው አደጋ እንደተጣለበት ባየ ጊዜ፤ ...እየፎከረ ገባበት፡፡
(ጣሊያንን) ...ከቦ ፈጀው፡፡
...ወደ ኋላ ቀርቶ የነበረው (የጣሊያን) ወታደር ነገሩን ሳያውቅ ወደ ጦርነቱ ሲጓዝ ነበር፡፡
ነገር ግን የጀነራል ባራቲየሪን መሸሽና የጦሩን መፈታት ባየ ጊዜ፣
...መድፉን እየጣለ በአጋሰሱ እየጋለበ አስመራ ገባ፡፡
...18 መድፍ ሳይተኮስ ከነጥይቱ ወድቆ የተገኘ ተያዘ፡፡”
በማለት ገልጸውታል፡፡

“በጦርነቱ ወቅት የነበሩት ጸሐፊ ትእዛዝ ገብረ ሥላሴ ስለጦርነቱ ሲጽፉ፤
“... ከሌሊቱ 11 ሰዓት የጀመረ እሰከ ጧቱ 4 ሰዓት ድረስ ተኩሱ አላባራም ነበር፡፡
... የተኩሱም ድምፅ እነደ ሐምሌ ዝናብ ነበር፡፡
... የተኩሱም ጢስ ብዛት ለሰልፈኛው ሁሉ እነደ ዛፍ ጥላ ሆኖለት ዋለ፡፡
... (የኢትዮጵያ ሠራዊት) መድፉ ይመታኛል፣ ነፍጡም ይጥለኛል፣ እሞታለሁ ብሎ ልቡ አይፈራም፡፡
... የቆሰለውም ሰው፤ በኋላ ስትመለስ ታነሳኛለህ፡፡ በመሀይም ቃሌ ገዝቸሀለሁ፡፡ ይለው ነበር፡፡
... (ጥይቱም) ያለቀበት እንደሆነ፤ ከቆሰለው ሰው ዝናሩን እየፈታ (ጠላትን) እያባረረ ወደፊት ይተኩስ ነበር፡፡
... አፄ ምኒልክ የፊተኛውን ጦር ድል ካደረጉ በኋላ ጦር እየጨመሩ ወደፊት ተጓዙ፡፡
... (ከቀኑ) 9 ሰዓት ሲሆን የአፄ ምኒልክ ሠራዊት ቁስለኛውንና የማረከውን ጣሊያን እየያዘ ተመለሰ፡፡
አፄ ምኒልክ ግን ከጦሩ ጋር አልተመለሱም፡፡
... አፄ ምኒልክ ቆይተው ሲመለሱ መሽቶ ለዓይን አይታይም ነበር፡፡”
በማለት ገልጸውታል፡፡

“…እኛ ግን፤ እንኳን ለእልፍና ለሁለት እልፍ ሰው፤ የኢጣሊያ አገር ሰው ሁሉ ቢመጣ፤ የኢጣሊያንን ጥገኝነት ይቀበላሉ ብለህ አትጠርጥር፡፡”
….አፄ ምኒልክ ነሐሴ 23 ቀን 1887 ዓ.ም.

“በጥጋባቸው አድዋ ላይ ተዋግተው ድል ሆኑ፡፡
እኔ ግን በድንቁርናቸው ብዛት የእነዚያን ሁሉ ክርስቲያን ደም በከንቱ መፍሰሱን እያየሁ ድል አደረግኋቸው ብየ ደስ አይለኝም፡፡”
….አፄ ምኒልክ መጋቢት 23 ቀን 1888 ዓ.ም.

“...የተተከለው ድንኳን ሲታይ፤ ከብዛቱ የተነሳ አፍሪካ አውሮፓን ለመጠራረግ የተነሳች ይመስላል፡፡
የጦርነቱ ዕለት፤ ኢትዮጵያውያን ደማቅ ቀለም ያለው ካባ ለብሰው፣
ጠመንጃና ጦር ይዘው፣ ጎራዴ ታጥቀው፣ የነብርና የአንበሳ ቆዳ ለብሰው፣ አዝማሪዎች እየዘፈኑ፣ ቄሶች፣ ሴቶች፤ ልጆችም ሳይቀሩ፤ ፀሐይዋ ፈንጠቅ ስትል በተራራው ላይ በታዩ ጊዜ የኢጣሊያንን ጦር አሸበሩት፡፡”
... በርክሌይ

“...20 ሺህ ያህል ወታደሮች ያሉበት የአውሮፓ ጦር፤ በአፍሪካ ሰዎች ለመጀመሪያ ጊዜ ተሸነፈ፡፡
በእኔ እምነት በዘመናችን ታሪክ ውስጥ እንደ አድዋው ያለ ጦርነት የለም፡፡
...25 ሺህ ሰዎች በአንድ ቀን ጀምበር የሞቱበትና የቆሰሉበት ነው፡፡
...ፖለቲካና ታሪክ አበቃ፡፡
በአፍሪካ ውስጥ ...ታላቅ ኃይል መነሳቱ ታወቀ፡፡
የአፍሪካ ተወላጆች ታሪክ ተለወጠ፡፡
ጥቁር ዓለም በአውሮፓውያን ላይ ሲያምፅና ሲያሸንፍ የመጀመሪያ መሆኑ ነው፡፡
አበሾች አደገኛ ሕዝቦች መሆናቸው ከኦሪት ዘፍጥረት ጀምሮ ተጽፎላቸዋል፡፡
የኛ ዓለም ገና ቶር እና ኦዲዮን በሚባሉ ዓማልክት ሲያመልክ በነበረበት ጊዜ፤ አበሾች የክርስቲያን ታሪክ የተቀበሉ ሕዝቦች ናቸው፡፡
አሁን የሁሉንም ፍላጎት አድዋ ዘጋው፡፡”
... በርክሌይ  ... (“አጤ ምኒልክ” ከተሰኘው የጳውሎስ ኞኞ መጽሐፍ የተወሰደ)

“ኢትዮጵያ የጥቁር ህዝቦች ሐውልት፤ ኃያል የሆነች የጥቁር ዘር አብሪ ኮኮብ፣ የነጭ ዘር ሊቋቋሟት ያልቻላት፣ ፈጣሪ አምላክ ያልተለያት የአፍሪካ ሕዝቦች ሕያው የነፃነት ተምሳሌት”
... ዳንኤል ትዋይት  (ከዐድዋ ድል በኋላ ስለ ኢትዮጵያ አሸናፊነት የተናገረው)

“…አንዱ ባንዱ ምቀኝነት ይቅር፡፡
…እኔ እስካሁን በፍቅር እንዳኖርኳችሁ፤ እናንተም ተስማምታችሁ በፍቅር እንድትኖሩ እለምናችኋላሁ፡፡
…እናንተ አንድ ልብ ከሆናችሁ፤ በምቀኝነት እርስ በርስ ተዋግታችሁ ካላለቃችሁ በቀር፤ አገራችንን ኢትዮጵያን ለሌላ ባዕድ አትሰጧትም፡፡ ክፉም ነገር አገራችንን አያገኛትም፡፡
…አገራችሁን በያላችሁበት በርትታችሁ ጠብቁ፡፡
…የኢትዮጵያ ጠላት፤ ባንድ ወገን ትቶ ባንድ ወገን ቢሄድና ድንበር ቢገፋ፤ በእኔ ወገን ካልመጣ ምንቸገረኝ ብላችሁ ዝም አትበሉ፡፡
በአንድነት ተጋግዛችሁ ጠላታችሁን መልሱ፡፡
…የደጊቱ አገራችን የኢትዮጵያ አምላክ ያግዛችሁ፡፡ ይጠብቃችሁ፡፡”
….ዳግማዊ አፄ ምኒልክ የመጀመሪያ ኑዛዜአቸውን አስጽፈው ከሰጡ በኋላ ሕዘቡና መኳንንቱ ጃንሜዳ ተሰብስቦ፤ ግንቦት 10 ቀን 1901 ዓ.ም. የተነበበው የኑዛዜ ቃል፡፡

Adwa Warriors
ኢትዮጵያውያን የአድዋ ወዶ ዘማቾች በአድዋ ምድር ይህን ይመስሉ ነበር

በርካታ የታሪክ ጸሐፊዎች እንደሚስማሙበት ከሆነ፤ ወደ አድዋ የዘመተው የኢትዮጵያ ጦር፤ 120 ሺህ እግረኛና 28 ሺህ ፈረሰኛ ጦር እንደነበረ ተገምቷል፡፡
የኢትዮጵያን ዘማች ጦር ያበዛው፤ የሰለጠነ ወታደር ሳይሆን፣ ተከታዩ ወይም የጀሌው ጦር ነበር፡፡
በኢትዮጵያ በኩል ወደ አድዋ ከዘመቱት መካከል፤ ሴቶች፣ ሽማግሌዎች፣ ቄሶችና ሕፃናት ሳይቀሩ ተገኝተዋል፡፡
ይህ በብዙ ኢትዮጵያውያን አዕምሮ ውስጥ ሲመላለስ ለብዙ ዘመናት የኖረውን ጥያቄ ዳግማዊ አፄ ምኒልክ ከኢጣሊያ ንጉሥ ኡምቤርቶ ለተጻፈ ደብዳቤ በሰጡት የጽሁፍ ምላሽ፤

“ጥንት ከአሕዛብ ከአረመኔ አገራችንን ጠብቋት የሚኖር አምላክ ከኛ ባይለይ በእግዚአብሔር ኃይል ድል አደረኳቸው፡፡
ከዚህ ሄጄ አሥመራንም የእኔን አገር ሁሉ አስለቅቃለሁ ብዬ ተጉዠ ሳለሁ ጀነራል ባልዲሴራ በኢጣሊያ ሠራዊት ሁሉ ላይ ተሹሜ መጥቻለሁ፡፡
ንጉሥ ኡምቤርቶም (ሲልከኝ) እርቅ ነውና የምፈልገው እርቅ አድርግ ብሎኛል ብሎ …ወረቀት ቢልክብኝ፤
እኔ በወደድኩት ከታረቃችሁ፤ የሚስማማኝም ቃል ከሆነ እውነተኛ ሰው አዲስ አበባ ከተማዬ ድረስ ይምጣና ይጨርስ ብዬ እኔም ወደ ከተማዬ ተመለስኩ፡፡”
በማለት ገልፀውታል፡፡

ዳግማዊ አፄ ምኒልክ፤ የአድዋ ጦርነት ከመጀመሩ በፊትም ቢሆን፤ ወደ ኤርትራ ተጉዘው ጣሊያኖችን ለማባረር ወስነው ነበር፡፡
ፕሮፌሰር አፈወርቅ ገብረ እየሱስ እነደጻፉት፤ ጣሊያኖች ከአድዋ ጦርነት በፊት ከምሽጋቸው አንወጣም ብለው ባስቸገሩ ጊዜ፤
“... ከአድዋ ወደ አሥመራ ለመሄድ ለዛ ሁሉ ሠራዊታቸው የሚበቃ ቀለብ ባለመገኘቱ አድዋ ላይ ...ዝም ብለው ተቀመጡ፡፡”
በማለት ጽፈዋል፡፡

ከአድዋ ድል በኋላም ቢሆን ወደ ሐማሴን የመዝመቱ ሀሳብ አልቀረም ነበር፡፡
ወደ ኤርትራ የመዝመቱ ሀሳብ የቀረበትን ምክንያት ፕሮፌሰር አፈወርቅ ገብረ እየሱስ ሲያስረዱ፤
“...(አፄ ምኒልክ) ያዲግራትን ምሽግ ሰብረው (መረብን በመሻገር) አሥመራ ያለውን የጣሊያን ጦር እስከባሕር ድረስ ለማባረር አስበው ነበር፡፡
በኋላ ግን ሠራዊታቸው ሁሉ ሦስት ወር ሙሉ ትግራይ ላይ በረሀብ ተጎድቶ ነበርና ወደ ሸዋ ተመለሱ፡፡”
ብለዋል፡፡

አለቃ ተክለ ሥላሴም ሲጽፉ፤
“... ያን ጊዜ (አፄ ምኒልክ) የጣሊያን ጦር እስከ ምጽዋ ለማባረር ሞክረው ነበር፡፡ ነገር ግን ሠራዊታቸው ሦስት ወር ሙሉ በረሀብ የተጎዳ ስለነበረ ተቸገሩ፡፡”
በማለት ጽፈዋል፡፡

ጣሊያኖች የኤርትራ ቅኝ ግዛታቸውን መመሥረት የቻሉት በአፄ ዮሓንስ ሞትና በወቅቱ ተከስቶ የነበረው “ክፉ ቀን” ተብሎ የተጠራው የረሀብ መቅሰፍት ባስከተለው ኢኮኖሚያዊና ማህበራዊ መናጋትን እንደ ጥሩ አጋጣሚ ተጠቅሞ ሲሆን፤ ዳግማዊ አፄ ምኒልክም ከአድዋ ድል በኋላ ጣሊያኖችን ከኤርትራ ለማሶጣት ያልቻሉበት አንዱና ዋነኛው ምክንያት ይህ የተከሰተው ከባድ ረሀብ ነበር፡፡
በእርግጥም ዳግማዊ አፄ ምኒልክ ጣሊያኖችን ከኤርትራ ምድር ለማሶጣት ያልቻሉበት አንደኛውና ዋነኛው ምክንያት የታሪክ ፀሐፍት እንዳስረዱን፤ በዚያን ዘመን ተከስቶ የነበረው የረሃብ መቅሰፍት ባደረሰው ከፍተኛ ጉዳት ምክንያት ሠራዊቱ የነበረውን ስንቅ አሟጦ ጨርሶ ነበር፡፡
በደረሰውም ድርቅ ሳቢያ በርካታ ሰዎች የከብት ሀብታቸውን ከማጣታቸውም በላይ በአንዳንድ አካባቢ ከመቶ ዘጠና የሚደርሰው ከብት አልቆ ነበር፡፡
በዚህም የከፋ የድርቅ ወቅት፤ ገበሬው ዋነኛ የምርት መሣሪያውን በማጣቱና በተፈጠረው ችግር ምክንያት ዳግማዊ አፄ ምኒልክ በጦርነቱ ገፍተው በመሄድ ፋሽስት ኢጣሊያን ከኤርትራ ምድር ለማሶጣት የማይችሉበት ሁኔታ ተፈጠረ፡፡

ተክለጻድቅ መኩሪያ፤ “ከአፄ ቴዎድሮስ እሰከ ቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ” በተሰኘው መጽሐፋቸው ላይ፤
“... ንጉሠ ነገሥቱ ጠላታቸውን ከአስመራ አስወጥቶ ባሕርን አሻግሮ ማባረር በሀሳባቸው መጥቶ ነበር፡፡
... ነገር ግን የኢጣሊያ መንግሥት፤ ምንም እንኳን አድዋ ላይ ድል ቢሆን እስከ ምጽዋ ድረስ አባረው ከአስመራ ሊያሶጡኝ የፈለጉ እንደሆነ፤
አንድ ጊዜ ሳልዋጋ አሥመራን አለቅም በማለት፤ ስመ ጥር በሆነው በጀነራል ቤልዲሴራ የሚመራ 15‚000 አዲስ ጦር ወደ አሥመራ መላኩ እርግጥ ነበር፡፡
... ከአዲሱ የጣሊያን ጦር ጋር ቢዋጉ ድል ያደርጉ ነበርን ?”
በማለት አስፍረዋል፡፡
የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ ባሮን ብላንክ፣ የአድዋ ጦርነት በተደረገ ማግሥት ሮም ውስጥ ለኢጣሊያ ፓርላማ ካቀረበው ሪፖርት ውስጥ በኤርትራ ውስጥ የተደራጀ ጠንካራ ኃይል እንዳላቸው የገለጸበትን መንገድ ሲያብራራ፤
“...ወታደሮቻችን አፍሪካ ውስጥ መሸነፋቸውን የሚገልጽ ቴሌግራም ደርሶናል፡፡ ቢሆንም በቅኝ ግዛታችን ውስጥ የሚያስተማምን በቂና ጠንካራ ኃይል ልከናል፡፡ ጠቅላላው ኃይላችንም በአኩሪው ጀነራላችን ጀነራል ባልዲሴራ የሚመራ መሆኑን ለመግለጽ እወዳለሁ፡፡
...ጠላት አድዋን የወሰደው በዕድል ነው፡፡ ይህ በኤርትራ እንደማይደገም ለምክር ቤቱ ቃል እገባለሁ፡፡
...ቅኝ ግዛታችን ኤርትራ በሚያስደንቅ ሁኔታ በሶስት ማእዘን እንድትጠበቅ አድረገናል፡፡
...የእንግሊዝ መንግሥትም በዘይላ በኩል ምንም ዓይነት የጦር መሣሪያ ወደ ኢትዮጵያ እንዳይገባ እንደሚያደርግ ቃል ገብቶልናል፡፡
...የሩስያ መንግሥትም ቢሆን ከሐይማኖት ጉዳይ በስተቀር በኢትዮጵያ የውስጥ ጉዳይ ጣልቃ እንደማይገባ ቃል ገብቶልናል፡፡
...ከፈርንሣይም ጋር በጥሩ ግንኙነት ላይ መሆናችንን ይህ ምክር ቤት ያውቃል፡፡”
የሚል ይገኝበታል፡፡



Menelik at Battle-of Adwa
የፈረንሳዩ ለፕቲት ጆርናል የተሰኛው
የፈረንሳይ ጋዜጣ የአድዋ ድልን ለማብሰር
ነሐሴ 23 ቀን 1891 ዓ.ም.
ከዐድዋ ድል ከ3 ዓመት በኋላ
የዳግማዊ ምኒልክን ስዕል ይዞ ወጥቷል
ብዙ ፀሐፊያን እንደጻፉትና እንደተስማሙበት፤ በአፍሪካ የጦርነት ታሪክ፣ ሁለት የተከበሩና የተደነቁ ጦርነቶች ውስጥ አንደኛው ከ2 ሺህ ዓመታት በፊት ሀኒባል አውሮፓውያንን ድል ያደረገበት ጦርነት ሲሆን፣
ሁለተኛው ከ2 ሺህ ዓመታት በኋላ ኢትዮጵያውያን አውሮፓውያንን አድዋ ላይ ድል ያደረጉበት ጦርነት መሆኑ ይጠቀሳል፡፡
“... የአድዋ ጦርነት ኢትዮጵያን በዘመናዊ የዓለም ካርታ ላይ ስሟን አስገባት...፡፡”

.... ማርጀሪ ፕርሃም
የዐድዋን የድል ዜና የዓለም ዋና ዋና የዜና ጋዜጦችና እና መጽሔቶች በሽፋን ገጾቻቸው ላይ የምኒልክንና የጣይቱን ፎቶግራፍ አወጡት፡፡
ከሀንጋሪ እስከ ፈረንሳይ ድረስ ወላጆች የልጆቻቸውን ስም፤ ምኒልክ ፣ ጣይቱ ፣ ባልቻ እና አሉላ እያሉ መሰየሙን ተያያዙት፡፡
የኒውዮርክ ታይምስ፣ የፈርንሳዩ ጋዜጣ ለፐቲት ጆርናል፣ እና ሐርፐርስ ዊክሊ የተባሉት ዓለም አቀፍ ጋዜጦች የአድዋን ድል በድሉ ማግስት ባሉት ቀናት በሰፊው ከመዘገባቸውም በላይ፣
ሰለ ጣይቱ ሲተርኩ፤
ከኢጣሊያ ንግሥት ከዜኖቢያ፣ ከ ግብጻዊቷ ንግሥት ከ ክሊዎፓትራና ከ ታላቋ ካትሪን ጋር እያመሳሰሉ ኃያልነቷን እየገለፁ ዘግበዋል፡፡
በኢጣሊያም፤ ሁለት ዓመት ሙሉ በተከታታይ በየቀኑ በሚወጡት ጋዜጦች ስለ አድዋ ድል ሲወራና ስብሰባ ሲካሄድ ከርሟል፡፡
Victory of Adwa
ስዕሉ በድረ ገጽ አዘጋጁ ተስተካክሏል

ምስግና ለ፤   ኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት
በሮም ከተማ ታላላቅ ጎዳናዎች ላይ ሰላማዊ ሰልፍ እየበዛ ሲሄድ፣ ዩኒቨርሲቲዎችና የትያትር ቤቶች ላልተወሰነ ጊዜ እንዲዘጉ ታዟል፡፡
በአድዋ ጦርነት ጣሊያን በመሸነፏ የጣሊያን ሕዝብ በነቂስ ወጥቶ ጠቅላይ ሚኒስትር ወደ ነበረው ወደ ክሪሰፒ መኖሪያ በመሄድ ድንጋይ በመወርወር ትልቅ ጉዳት በማድረሳቸው ፖሊሶች ደርሰው ጠቅላይ ሚኒስትሩን ከአደጋ አድነውታል፡፡
ጠቅላይ ሚኒስትሩም ወዲያውኑ ስንብት ጠይቆ ከሥልጣኑ ለቋል፡፡
የኢጣሊያው ንጉሥ ኡምቤርቶም የልደት ቀናቸው የሐዘን ቀን ሆኖ እንዲውል አወጁ፡፡
በፈርንሳይ፣ በጀርመን፣ በሩሲያና በአሜሪካ ታላላቅ የሆኑ የደስታ መግለጫ ስብሰባዎች ተካሂደዋል፡፡







ምንጭ፤
  1. "አጤ ምኒልክ"  ደራሲ፡- ጳውሎስ ኞኞ የካቲት ወር 1984 ዓ.ም.
  2. "የኢትዮጵያ ታሪክ ከ 1847 እሰከ 1983"  ደራሲ፡- ፕሮፌሰር ባሕሩ ዘውዴ
  3. "የኢትዮጵያ ታሪክ - ከአፄ ልብነ ድንግል እስከ አፄ ቴዎድሮስ"  ደራሲ፡- ተክለ ጻድቅ መኩሪያ 1961 ዓ.ም.
  4. "መራራ እውነት በኢትዮጵያ ታሪክ "  ደራሲ፡- ታዬ ቦጋለ አረጋ 2011 ዓ.ም.